February 7, 2024 

“የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ157 በላይ ነው”— በመርአዊ ከተማ የሚገኙ የህክምና ባለሙያ ከሰጡኝ መረጃ የተወሰደ

( ኤሊያስ መሰረት)

ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ እለት ከንጋት ጀምሮ በመንግስት ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መሀል በመርአዊ ከተማ የተካሄደን ውጊያ ተከትሎ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ በተፈፀመ ግድያ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 157 መሆኑን አንድ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውንም ሆነ የሚሰሩበትን የጤና ማዕከል እንዳልጠቅስ የጠየቁኝ የህክምና ባለሙያ አሳውቀውኛል።

ባለሙያው ሁኔታውን ሲያብራሩ “አብዛኞቹ ሟቾችን መልካቸውን እንኳን ለመለየት አልተቻለንም ነበር… በህይወቴ አይቼው የማላውቅ ከባድ ነገር ነበር” ብለዋል።

አንድ ሌላ የከተማው ነዋሪ ደግሞ የመንግስት ሀይሎችን ለድርጊቱ ተጠያቂ አድርገው ቀደም ብሎ የፋኖ ታጣቂዎች የወታደሮች መኖርያ ላይ ጥቃት አድርሰው ነበር የሚባል መረጃ በህዝቡ ዘንድ እንዳለ ጠቅሰዋል።

“የተረሸኑት ንፁሀን ከቤታቸው ጭምር ተጎትተው እንዲወጡ ተደርጎ ነው፣ እስከ እሮብ ድረስ ሬሳ ከየቦታው ሲለቀም ነበር” ብለዋል። አሁን ላይ በድንጋጤ ላይ ያለው የከተማው ህዝብ የቻለው በቅርብ ርቀት ወደምትገኘው ባህር ዳር ከተማ እየሄደ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህ ዙርያ ተጨማሪ መረጃ ከመንግስት አካላት ለማግኘት ያደረግኩት ሙከራ አልተሳካም። ተጨማሪ መረጃ ካገኘሁ እመለስበታለሁ። ኤሊያስ መሰረት