
7 የካቲት 2024, 14:48 EAT
በአሜሪካ ሚቺጋን በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ ተኩሶ አራት ተማሪዎችን የገደለው እናት የልጇን ጥፋት መከላከል ባለመቻሏ ጥፋተኛ ተባለች።
የ45 ዓመቷ ጄኔፈር ክረምብሌይ በልጇ በተፈጸመ የጅምላ ግድያ ወንጀል ተከሳ ጥፋተኛ የተባለች የመጀመሪያዋ አሜሪካዊት ወላጅ ናት።
ልጇ ሽጉጥ እንዲኖረው በመፍቀድ ቸልተኝነት አሳይታለች እንዲሁም አንዳንድ ማስጠንቀቂያዎችንም ማየት ተስኗታል ሲሉም ነው አቃብያነ ህግ የከሷሷት።
ባለቤቷ ጄምስም በተመሳሳይ ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በተለየ ችሎት እየታየ ይገኛል።
ግለሰቡም ጥፋተኛ አይደለሁም ሲልም አስተባብሏል።
በአሁኑ ወቅት 17 ዓመቱ የሆነው ልጃቸው ከሶስት ዓመታት በፊት ኦክስፎርድ በተሰኘው ትምህርት ቤት አራት የክፍል ጓደኞቹን በመግደልም ጥፋተኛ ተብሎ የእድሜ ልክ እስራት ላይ ይገኛል።
በዚህ ትምህርት ቤት ላይ በተከፈተው ተኩስ ሰባት ሰዎችም ቆስለዋል።
ማክሰኞ እለት በኦክላንድ ግዛት በሚገኘው ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ላይ ብያኔው ሲገለጥ ግለሰቧ ስሜት አልባ ሆና ታይታለች ተብሏል።
እያንዳንዳቸው እስከ 15 ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት በሚያስፈርዱ አራት የግድያ ወንጀሎች ክስም ነው የተከሰሰችው።
ብይኑንም ተከትሎ በዚህ ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ግለሰቦች ደስታቸውን ገልጸዋል።
“ህዝብ ወስኗል” ሲልም የ16 ዓመት ልጁን በዚህ ጥቃት ያጣው በክ ማይሬ ለቢቢሲ ተናግሯል።
- አዋሽ 40 ፡ “በቂ ምግብ ፣ ውሃ እና በቂ እንቅልፍ በስለትም ቢሆን የማይገኝበት ቦታ”7 የካቲት 2024
- አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ቃለ-መጠይቅ ሊያደርግ ነው7 የካቲት 2024
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አቡነ ጴጥሮስ ወደ አገር እንዲገቡ እንዲፈቀድ ጠየቀች6 የካቲት 2024
“ከህዝብ ብያኔ ጋር መስማማት ወይም አለመስማማት ይቻላል። ነገር ግን ስርዓቱ በዚህ መንገድ ነው መስራት ያለበት” ብሏል።
በዚህ የፍርድ ሂደት ወቅት ዋነኛ ጥያቄ የነበረው የልጇን ወንጀል አስቀድማ ማየት እንዲሁም መከላከል ትችል ነበር ወይ የሚለው ነበር።
ጥፋተኛ የተባለችው እናት እና አባትየው ጄምስ ልጃቸው አራት ተማሪዎችን የገደለበትን ሽጉጥ በስጦታ ገዝተውለታል ተብሏል።
ሽጉጡንም የገዙለት ከጥቃቱ ከቀናት በፊትም መሆኑ ተገልጿል።
ግድያው በተፈጸመ በቀናት ውስጥም ነው በፖሊስ ሲፈለጉ የነበሩት።
ጥንዶቹ ከህዝብ በተሰጠ ጥቆማ በዲትሮይት በሚገኝ አንድ ህንጻ ውስጥ ፖሊስ አግኘቷቸዋል ተብሏል።
ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ቆይተዋል።
የታዳጊው ወላጆች ክስ አንድ ላይ ይመሰረትባቸዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በህዳር ወር በተለያየ ችሎት እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
አባትዮው ጄምስ ክረምብሌይ በመጋቢት ወር የፍርድ ሂደቱ እንደሚጀምርም ተጠቁሟል።