ዳዊት ታዬ

February 7, 2024

በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የቀድሞ 12 የቦርድ አባላት፣ በማናቸውም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ግልጋሎት እንዳይሰጡ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕግድ ጣለባቸው፡፡

የቀድሞ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የቦርድ አባላት በማንኛውም የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ታገዱ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት ለ12ቱ የቀድሞ የቦርድ አባላት በጻፈው ደብዳቤ፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ለገጠመው ችግር በጋራም ሆነ በተናጠል ተጠያቂ መሆናቸውን ባደረገው ምርመራ ማረጋገጡን በመጥቀስ፣ ከዚህ በኋላ ለስድስት ዓመታት በየትኛውም የፋይናንስ ተቋም ውስጥ እንዳይሠሩ ውሳኔ እንዳሳለፈባቸው አስታውቋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ የንብ ባንክ የቀድሞ የቦርድ አባላት በማናቸውም የፋይናንስ ተቋማት በቦርድ ኃላፊነት፣ በዋና ሥራ አስፈጻሚነትና በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች እንዳይመደቡ ወስኗል፡፡

የቀድሞዎቹን የቦርድ አባላት የሚተኩት አዲስ የተመረጡት የቦርድ አባላት ደግሞ ኃላፊነታቸውን ተረክበው ሰኞ ጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ሥራ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዛሬው ዕለትም አዲሶቹ የቦርድ አባላት ባንኩን በዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበርነትና በምክትል ሊቀመንበርነት የሚያገለግሉ አመራሮችን ይሰይማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰናዳውን ዝርዝር ዘገባ በቢዝነስና ኢኮኖሚ ገጽ ላይ ይመልከቱ፡፡