ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ዜና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታጣቂ ኃይሎች ትጥቃቸውን አስቀምጠው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያደርጉ ጠየቁ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: February 7, 2024

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች፣ መሣሪያቸውን አስቀምጠው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ማድረግ እንዲችሉ፣ መንግሥት ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌዴራል መንግሥትንም ሆነ የክልል መንግሥታትን ዝግጁነት የገለጹት ትናንት፣ ማክሰኞ ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ ነው፡፡

የሰላም ጥሪው በተደጋጋሚ መደረጉን አስታውቀው፣ ‹‹አሁንም በድጋሚ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት በአገሪቱ ችግር እየፈጠሩ በሚገኙ አካላት ላይ ሕግ ማስከበሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

‹‹የምንፈልገው ሰላም ነው፣ የምንፈልገው ውይይት ነው፣ የምንፈልገው አብረን አገራችንን ወደ የሚቀጥለው ደረጃ ማሸጋገር ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ሳይነሳ ቀርቶ ሳይሆን፣ በተደጋጋሚ እየቀረበ ያለው አሁንም ያለው ፍላጎት ይኼው በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ሒደት ሁሉም ወገን ለሰላም ሚናውን እንዲጫወት ጠይቀው፣ የፌዴራል መንግሥትም ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡ የሚደገፍበትን ቢያውቅ ጥሩ ነው፡፡ ጉም ምንም ያህል ተራራ ቢያክል፣ ምንም ያህል ክምር ድንጋይ ቢያክል አትንተራሰውም፣ ጉም ጉም ነው፡፡ መንተራስ ያለብን ነገር ደገፍ የሚያደርገንን ነገር ነው፡፡ ዝም ብሎ የማያዛልቀንን ነገር ተንተርሰን ወደ ጥፋት እንዳናመራ፣ በተቻለ መጠን ሰላም ሰላማዊ ንግግርና ውይይት የሚለውን አማራጭ መከተል ይሻላል፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ሰላም፣ ደኅንነትና የፀጥታ ጉዳዮች የሚያውኩ ያሏቸውን ሦስት ጉዳዮች ገልጸዋል፡፡ እነሱም የፖለቲካ ፍላጎት የማሳኪያ ልምምድና ሥልት ችግር መኖር የመጀመሪያው ሲሆን፣ ይህ መንገድ የተለያዩ አካላት ፍላጎታቸውን በሐሳብ ሳይሆን በጠመንጃ ማሳካት የሚፈልጉበት አደገኛ ስብራት ነው ብለዋል፡፡

ሁለተኛው አዋኪ ጉዳይ የችግር መፍቻ መንገድ መሆኑን፣ ይህ ማለት በሰዎች ወይም በማኅበረሰብ ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር አለመግባባት ሲፈጠር ችግሩን ለመፍታት የመነጋገር፣ የመወያየትና በሽምግልና የማየት ልምምድ እየቀነሰ መምጣት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሦስተኛ ደረጃ ያስቀመጡት አዋኪ ጉዳይ የሰላም ጅማሬ በግራም በቀኝም ወጥመድና እንቅፋት በማስቀመጥ፣ ወደኋላ እንዲመለስ የማድረግ ልምምዱ የሰፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ያከናወነው ድርድር ግልጽ አልተደረገም ተብሎ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ መንግሥት ምንም እንኳ ድርድሩ ሊጀመር መሆኑን ቢገልጽም ድርድሩ ተካሂዶ ውጤቱ ሲጨመቅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን አሳካን ብሎ ለመናገር የሚያስችል ድምዳሜ እንዳልነበረ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ ወደፊት ተደራዳሪዎቹ ልቦና ሰጥቷቸው የኢትዮጵያን ሕግና ሥርዓት አክብረው በውይይት አምነው ድርድሩ ሲካሄድ፣ በግልጽ ለተከበረው ምክር ቤትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቀርባል፤›› ብለዋል፡፡

ኦነግ ሸኔ በአስመራ በተደረገው ድርድር አማካይነት አገር ቤት ሲገባ በድርድሩ መሠረት ለመንግሥት ሳይሟላ ቀርቶ ወይም እታገልልሃለሁ ለሚለው ሕዝብ ልማት ተጨንቆ ከሆነ በረሃ የገባው፣ የሚታገልለትን ሕዝብ እያገተ ልማት እንዳያከናውን በማድረግ ዘረፋ መፈጸም ለኦሮሞ ሕዝብ ምንም ፋይዳ የለውም ብለዋል፡፡

‹‹ሸኔ ተሰማርቶ ያለው ግለሰቦችን ማገት፣ መኪና ማቃጠልና ልማት እንዳይሠራ ማድረግ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ በማንኛውም የትግል መሥፈርት ለሆነ ዓላማ ማሳኪያ የሚደረግ የትግል ሥልት ተደርጎ ሊወሰድ የማይችል ጥፋት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እንበልና ሥልጣን እንኩ ውሰዱ ቢባሉ በምን ሞራልህ ነው የገደልከውን የዘረፍከውን፣ ያገትከውን ሕዝብ ልምራህ የምትችለው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) በአማራ ክልል ከከሚሴ ዞን በስተቀር በሁሉም ዞኖች ከሕዝብ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ከሚገኙ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶችና ወጣቶች ጋር አካሄድኳቸው ባሏቸው ውይይቶች ከሞላ ጎደል በሁሉም አካባቢዎች ተነሱ ያሏቸው፣ የልማት፣ ሕገ መንግሥቱ አግሎናል የሚሉና የወሰን ይገባኛል፣ የመልካም አስተዳደር፣ እንዲሁም እንደ አካባቢው የሚነሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት 3,700 ኪሎ ሜትር መንገድ፣ እንዲሁም በአፍሪካ ደረጃ በግዝፈት፣ በውበትና በጥራት አይቼው የማላውቀው የጎርጎራ ቱሪስት መዳረሻ ተገንብቷል፤›› ብለዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ ጥያቄውን የሚቀበል አካል እንዳለ፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በምክክር ውጤት ለማምጣት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን ገልጸው፣ በኮሚሽኑ አማካይነት በውይይት ዘላቂ መፍትሔ ያገኛል ብለዋል፡፡

የወሰን ይገባኛል ጥያቄው ከዚህ በፊት ይነሳ እንደነበረና ነገር ግን የሚያነሱ አካላት ይታሰሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን መንግሥት ጥያቄው ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ በሰላማዊ መንገድ በሕዝብ ውይይት ተደርጎ በሕዝበ ውሳኔ እስኪወሰን የተፈናቀሉ ዜጎች መመለስ እንዳለባቸው አክለዋል፡፡ በተመሳሳይ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ በፓርቲ ደረጃ ተወስኖ የሁለቱ ክልል አመራሮች ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሰሞኑ የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ አማራ ክልል በመሄድ የሕዝቡን ብሶትና ችግር እንዲያዳምጡ መደረጉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የውይይቱን ውጤትና የተነሱ ጉዳዮችን በፓርቲያቸው በቅርቡ ተመክሮና መንግሥት ያጎደለው ሥራ ተሞልቶ፣ ለጊዜው ያልተቻለ ካለ ደግሞ ታገሱን ተብሎ፣ ‹‹ከሕዝቡ ጋር ውይይት መቀጠል እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡