– Advertisement –spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. በታኅሳስ 2019 በአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ኮንግረስ) ውሳኔ ቁጥር/ኤችአር 1158 ለውሳኔ ቀረበ፡፡ ይህ የውሳኔ ሐሳብ ለሶማሊያ የዕዳ ማቃለል ዕቅድን የያዘ ነበር፡፡ በምክር ቤቱ የምትገኘዋ ትውልደ ሶማሊያዊት ኢልሀን ኦማር ዕቅዱን ደግፋ ድምፅ እንደምትሰጥ ተገምቶ ነበር፡፡ የውሳኔ ሐሳቡ በ280 ድጋፍና በ138 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ ፀደቀ፡፡ ይሁን እንጂ ለትውልድ አገሯ ሶማሊያ የዕዳ ጫና የሚያቃልል የተባለውን ውሳኔ ትደግፋለች ተብላ የተጠበቀችው ኢልሀን ኦማር፣ ከተቃወሙት 75 የዴሞክራት ተወካዮች አንዷ ሆና አረፈችው፡፡

የታላቋ ሶማሊያ ትርክት ከዚያድ ባሬ እስከ ኢልሀን ኦማር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ከኢትዮ ሶማሌላንድ የመግባቢያ ስምምነት በኋላ በሶማሊያ የታየው ተቃውሞ

ይህ ጉዳይ ማስገረሙ ሳያበቃ ኢልሀን በጊዜው 1.7 ሚሊዮን ተከታዮች በነበሩት በትዊተር (ኤክስ) ገጿ ላይ የለጠፈችው ነገር ተጨማሪ ግርታን ፈጠረ፡፡ ለሶማሊያ ጠቃሚ የሆነ ሕግ በኮንግረሱ አፅድቀናል ስትል እሷ ድምፅ ነፍጋ፣ የፀደቀውን የውሳኔ ሐሳብ ስታወድስ ታየች፡፡ ለምን የውሳኔ ሐሳቡን የሚደግፍ ድምፅ እንዳልሰጠች ስትጠየቅ ግን መልስ ለመስጠት ዝግጁ አልነበረችም ተብሏል፡፡ኢልሀን በውዝግብ የተሞላች ፖለቲከኛ ናት ይባላል፡፡ ይህን የሚሉ ሰዎች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አቧራ ማስነሳት የሚቀናት ናት ይሏታል፡፡ መድረክ ስትይዝና ንግግር ስታደርግ በስሜታዊነት የምትዋጥ ፖለቲከኛ ናት ሲሉ ብዙዎች ይተቿታል፡፡ ከአፍሪካ ወጥታ በአሜሪካ ፖለቲካ እስከ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተመራጭነት የደረሰችው ኢልሀን አሜሪካ በአፍሪካ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ ለማስተካከል ብዙ ትሠራለች ሲባል ቢቆይም በመጨረሻ ግን ለትውልድ አገሯ ሶማሊያ ዕዳ የሚያቃልል ውሳኔ እንዳይተላለፍ ድምፅ ስትነፍግ መታየቷ፣ ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነ ጉዳይ ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡በዚህና በሌሎችም ዕርምጃዎቿ ሌላው ቀርቶ ከትውልደ ሶማሊያዊያን ጋር ዓይንና አፍንጫ ሆና ነው የኖረችው ይባላል፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 2022 ሱልዳን ሲራር የተባለው ታዋቂ የሶማሊያ ዘፋኝ በሚኒያፖሊስ ከተማ በአንድ አዳራሽ ጢም ብለው ለተሰባሰቡ ትውልደ ሶማሊያዊያን ኮንሰርት ያቀርብ ነበር፡፡ በዚያ ምሽት በአዳራሹ ከባለቤቷ ጋር የተከሰተችው ኢልሀን በመሀል ወደ መድረኩ እንድትወጣና አጭር ንግግር እንድታደርግ ተጋበዘች፡፡ ይህን ጊዜ ግን ኮንሰርቱን የሚታደሙ ትውልደ ሶማሊያዊያን የማያባራ ጩኸትና ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ፡፡ ከዚህ ጥፊልን የሚል በጩኸት ብቻ ሳይሆን በእጅ ጭምር ፀያፍ ስድብ የተቀላቀለበት ተቃውሞ የሚያቀርቡ ታዳሚዎች በርካታ ነበሩ፡፡ኢልሀን ማይክ እንደጨበጠች ተረጋጉ ብትል የሚሰማ ጠፋ፡፡ ተወዳጁ ድምፃዊ ሱልዳን ጭምር ጉዳዩን ለማብረድ ተቸገረ፡፡ ለአሥር ደቂቃ ያህል ተቃውሞው በመቀጠሉ ኢልሀን የእኔ ወገን ከምትላቸው ትውልደ ሶማሊያዊያን ጭምር ተቃውሞ ተበርክቶላት ከመድረኩ ተሸኘች፡፡ ይህ የትውልደ ሶማሊያዊያን ቁጣ የተስተጋባው ያለምክንያት አለመሆኑን የቪዲዮ መረጃ ጭምር አስደግፈው በወቅቱ ጉዳዩን የዘገቡ ሚዲያዎች ይፋ አድርገዋል፡፡ ሴትየዋ በሶማሊያ ምርጫ ጣልቃ ገብታ በመፈትፈቷ ያገኘችው አፀፋ ነበር ተብሏል፡፡ከእሷ ጎሳ ውጪ የሆኑትን ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ (ፋርማጆ) እንዳይመረጡ ጣልቃ ገብታለች በሚል ነው ትውልደ ሶማሊያዊያኑ አምርረው የተቃወሟት፡፡ ኢልሀን በሶማሊያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ፖለቲካም ጣልቃ መግባቷን ከዚያም ወዲህ ያቆመች አይመስልም ይላሉ አንዳንድ ሪፖርቶች፡፡ ከሰሞኑ በሚኒያፖሊስ አንድ ሆቴል ለተሰበሰቡ ትውልደ ሶማሊያዊያን አደረገችው የተባለው ንግግር ደግሞ ኢልሀን ከውዝግብ ያልተላቀቀች ፖለቲከኛ ናት የሚለውን የሚደግፍ ነው ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችውን የወደብ ስምምነት አስታካ ስለሶማሊያ ብዙ ጉዳዮችን በዚህ ንግግር አንስታለች፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መሬት እንደዘረፈችና የሶማሊያን ግዛት እንደወረረች አስመስላ በመድረኩ ያቀረበችው ኢልሀን፣ ታላቋን ሶማሊያ ስለመፍጠር ስትናገርም ተደምጣለች፡፡የአሜሪካ ኮንግረስ (ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት) የሶማሊያን ፍላጎት እንደሚያስፈጽም አስመስላ ያቀረበችው ኢልሀን፣ ኢትዮጵያና ኬንያ የዘረፉትን የታላቋ ሶማሊያ መሬት ገና እናስመልሳለን ብላ ስትፎክር ተደምጣለች፡፡ አንዳንዶች በተለይም ዴሞክራቶችና ሚዲያዎቻቸው የኢልሀን ንግግር በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሞ ስለመቅረቡ በመጥቀስ ሊከላከሉላት ቢጣጣሩም፣ ንግግሩ ያስነሳው ውዝግብ ቀላል አይደለም፡፡ ኢልሀን ከኢትዮጵያዊያንም ሆነ ከኬንያ ወገን ጠንካራ የሚባል ተቃውሞና ውግዘት እስካሁን ባይገጥማትም፣ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ግን ንግግሯን በቀላሉ ሊያልፉት አልፈለጉም፡፡ አሜሪካንን እወክላለሁ ብላ ቃል ገብታ በአሜሪካ ምክር ቤት ወንበር የያዘች ሴት የሶማሊያን ጥቅም አስቀድማለሁ ማለቷ በአገር ክህደት ወንጀል ነበር የታየባት፡፡ አንዳንድ የኮንግረስ አባላት ኢልሀን ኦማር ከምክር ቤቱ እንድትባረር ጥረት መጀመራቸው ታውቋል፡፡በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ በተለቀቀው ቪዲዮ የኢልሀን የሶማሊኛ ንግግር ውስጥ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት በተመለከተ ብዙዎች እየደወሉ ጉዳዩን ለማስቆም ጥረት እንዳደርግ ጠይቀውኛል፡፡ ለአሜሪካ መንግሥት ጉዳዩን እንዳስረዳም ይጠይቁኛል፡፡ ስምምነቱ ወደ መደበኛ የሁለትዮሽ ስምምነት እንዳይሸጋገር ለማድረግ የአሜሪካ መንግሥት ሊወስድ የሚችለውን ዕርምጃ ብዙዎች ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ እኔ ለሶማሊያዊያን የምሰጣቸው መልስ ግን የአሜሪካ መንግሥት በአሜሪካ የምንኖር ሶማሊያዊያን የምንፈልገውን ከማድረግ ውጪ ምንም ምርጫ የሌለው መሆኑን ነው፡፡ የምንላቸውንና የምናዛቸውን መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ ነው የሶማሊያን ጥቅሞች ማስጠበቅ የምንችለው፡፡ እኛ ሶማሊያዊያን በአሜሪካ የፈለግነውን ማስፈጸም እንደምንችል በራስ መተማመን ሊሰማን ይገባል፡፡ በአሜሪካ ነው የምንኖር ታክስ ከፋይ ነንና ልንደመጥ ይገባል፡፡ በአሜሪካ ኮንግረስ የተቀመጥኩት የእናንተን ጥቅም ለማስጠበቅና እናንተን ወክዬ ነው፡፡ በዚህ ኮንግረስ እስካለሁ ድረስ ሶማሊያን አንዳችም ክፉ ነገር አይነካትም፡፡ ኢትዮጵያ በህንድ ውቅያኖስ የሚገኝ ጠረፋችንን አትሰርቀንም፤›› የሚል ይዘት ያለው መልዕክት እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ይህን የንግግር ክፍል በአሜሪካ ምክር ቤት የሶማሊያን ጥቅም አስፈጽማለሁ እንደማለት ነው ብለው የወሰዱት አንዳንድ የኮንግረስ አባላት፣ ኢልሀን በዚህ ንግግሯ ከኮንግረስ እንድትባረር እየጠየቁ ነው፡፡ ንግግሩ በአገር ክህደት ወንጀል መታየት እንዳለበትም እየተከራከሩ ነው፡፡ኢልሀን እ.ኤ.አ. በ2016 ነበር ለሚኒሶታ ግዛት ምክር ቤት እንደራሴነት የተመረጠችው፡፡ በ2018 ደግሞ ለአሜሪካ ኮንግረስ ተወዳድራ አሸነፈች፡፡ ፈጣን የፖለቲካ ዕድገት በማሳየት በኮንግረሱ ውስጥ ብዙ ኃላፊነቶችን ለመያዝና ተፅዕኖዋን ለማሳደግ በቃች፡፡ በዓለም አቀፍ ጤና፣ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ እንዲሁም በውጭ ግንኙነት ኮሚቴዎች አባልነት መሥራት ጀመረች፡፡ በውጭ ግንኙነቱ በተለይም በአፍሪካ ፖሊሲ ግሩፕ ውስጥ ቁልፍ ሚናም አገኘች፡፡ ይህ ሁሉ ግን ብዙም አልዘለቀም፡፡ ኢልሀን በማኅበራዊ ትስስር ገጿ በምትለጥፋቸው ሐሳቦች፣ በምክር ቤቱና በየመድረኩ በምታቀርባቸው ንግግሮች ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥማት ጀመር፡፡ ከአፍሪካ የወጣች ጥቁር ሙስሊም በመሆኗ በዘርም በሃይማኖትም ጥላቻ የጥቃት ሰለባ ስለመሆኗ ደጋግማ ትናገራለች፡፡ ይህን በመረዳት ብዙዎች የሚደርስባትን ትችትና ነቀፌታ ሲከላከሉላት መቆየታቸው ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ ኢልሀን በተደጋጋሚ በምታነሳቸው ሐሳቦች ውዝግብ ማስነሳቷን እንደገፋችበት ነው የሚነገረው፡፡እ.ኤ.አ. በ2019 የአሜሪካ ፖለቲከኞች በአይሁዶች የውትወታ ቡድን (ሎቢ ግሩፕ) ገንዘብ የተገዙ ናቸው የሚል ይዘት ያለው መልዕክት በማኅበራዊ ትስስር ገጿ መለጠፏ ከባድ ቁጣን ቀሰቀሰ፡፡ በ2021 ደግሞ ልክ እንደ ሀማስና ታሊባን ሁሉ የአሜሪካ መንግሥትም ብዙ ጭፍጨፋዎችን ሲያደርግ ኖሯል የሚል መልዕክት ያለው ሐሳብ በማኅበራዊ ገጿ አሰፈረች፡፡ ይህኛውም ቢሆን አሜሪካንን ወክላ የአሜሪካ መንግሥትን ከአሸባሪዎች ጋር አነፃፀረች በሚል ከባድ ተቃውሞ አስነሳባት፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በምትሰነዝራቸው ሐሳቦች አይሁዶችን ጠል የሆነ፣ እንዲሁም ፀረ አሜሪካ አቋም ታራምዳለች በሚል በአሜሪካ ፖለቲካ ውዝግብ ስታስነሳ መቆየቷ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ኢልሀን በተደጋጋሚ ለሚነሱባት ወቀሳዎች ጥቁር ጠልና ሙስሊም ጠል ወገኖች እንደተነሱባት አድርጋ በማሳመን ብዙዎች ከጎኗ እንዲቆሙ ማድረግ መቻሏ ይጠቀሳል፡፡ ይሁን እንጂ እስራኤል አፓርታይዳዊ አገዛዝ የምታራምድ አገር ናት፣ እንዲሁም የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እስራኤልን ደጋፊ ነው የሚል ይዘት ያለው መልዕክት አሠራጭታለች ተብላ በእስራኤልና በአሜሪካ ጠልነት ተወነጀለች፡፡ እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ 2023 ከአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ አባልነት እንድትባረር የውሳኔ ሐሳብ ቀረበ፡፡ ብዙ ዴሞክራቶች ቢቃወሙትም አንዳንዶቹ ግን ከሪፐብሊካኑ እኩል ደግፈው የውሳኔ ሐሳቡን አፀደቁ፡፡ በውሳኔውም 218 ለ211 በሆነ ድምፅ ኢልሀን ከምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ አባልነት እንድትባረር መደረጓ በጊዜው ይፋ ሆኗል፡፡ይህ ከተፈጠረ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ኢልሀን በአዲስ ውዝግብ ከሰሞኑ ተከስታለች፡፡ ጉዳዩ በአሜሪካ ፖለቲካ የፈጠረውን ውዝግብ ወደገን ብለው የኢልሀን ሰሞነኛ ንግግር በወቅቱ ባለው የሶማሊያና የኢትዮጵያ ውጥረት ላይ ተጨማሪ ቤንዚን የሚነሰንስ መሆኑን በርካቶች እየገጹ ነው፡፡ ኢልሀን በዚህ ንግግሯ ስለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ስለኢትዮጵያና ሶማሊያም ብዙ ነጥቦችን አንስታለች፡፡ከንግግሯ መካከልም፣ ‹‹ሶማሊያዊያን ወንድማማቾች ነን፡፡ እርስ በርስ እንዋደዳለን፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች እስከ መጋጨትና እስከ መገዳደል የደረስንባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ምንም ቢሆን ግን ኅብር ያለን አንድ ማኅበረሰብ ነን፡፡ አንዳችን ለሌላችን እህትና ወንድማማቾች ነን፡፡ አንድ ደም ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ እኛ ሁሌም የምናውቀው መጀመሪያ ሶማሊያዊያን ነን፣ ሁለተኛም ሙስሊሞች ነን፡፡ አንዳችን ሌላኛችንን የምንጠብቅና እርስ በርስ የምንረዳዳ ብቻ ሳይሆን፣ እንደኛው ሙስሊም የሆኑ ሌሎች ሰዎችን የምንረዳም ነን፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት ሶማሌላንዶች ነን ብለው የሚናገሩ ሰዎችን ሰምቻለሁ፡፡ ራሳቸውን እንደ ሶማሊያዊያን ቆጥረው ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ሲፈራረሙም አይቻለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ የባህር በር ለመስጠት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ብዙ ሶማሊያዊያን እየደወሉ በዚህ ጉዳይ እንድናገር ጠይቀውኛል፡፡ ለአሜሪካ መንግሥት እንዳቀርብ ወትውተውኛል፡፡ ሆኖም አሜሪካ የእኛን መሬት የሚሰርቅ ኃይል ለመደገፍ በፍጹም አትሞክርም፡፡ የእናንተን ጥያቄና ጭንቀት በደንብ እረዳለሁ፡፡ ስለሶማሊያ ጉዳይ እኔም እጨነቃለሁ፡፡ በጋራ የሶማሊያን ጥቅም እናስጠብቃለን፡፡ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ በዚህ ጉዳይ ጥሩ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ክቡር ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያና ሶማሊላንድን በመታገልዎ እንኮራብዎታለን፣ እንደግፍዎታለን፡፡ ሶማሊያዊያን አገር አልባ ሆነው በመላው ዓለም ተበትነዋል፣ አገራቸው ሶማሊያን መጠበቅ አይችሉም፣ ሶማሊያም መንግሥት አልባ ሆናለች ብለው ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ሶማሊያዊያን የማንበገርና ችግሮቻችንን የምንጋፈጥ ሕዝቦች ነን፡፡ ሶማሊያዊያን አገራቸውን የሚወዱ ሕዝቦች ነን፡፡ አገራችንን ማንም እንዲዘርፍ የምንፈቅድ አይደለንም፡፡ ትውልደ ሶማሌ አሜሪካዊያንን እንዲሁም በመላው ዓለም ያሉ ሶማሌዎችን አመሠግናለሁ፡፡ በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ ስምምነት ጉዳይ ላይ ተቃውሞ ለማካሄድ አስደናቂ ትብብር አንፀባርቃችኋል፡፡ ከፕሬዚዳንታችን ጀርባ መሠለፋችሁን አደንቃለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ሶማሊያ የሶማሊያዊያን ብቻ ናት፡፡ ሶማሊያ አንዲት አገር ናት፡፡ ሁላችንም ወንድማማችና እህትማማች ነን፡፡ መሬታችን አይከፋፈልም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ኬንያ የሰረቁትን መሬታችንን እናስመልሳለን፡፡ የሶማሌ ክልል የሚባለው የሶማሊያ ግዛት ነው፡፡ ከሶማሊያ፣ ከሶማሌላንድና ከሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ ግዛት ተቆርሶ የተወሰደብንን መሬት እናስመልሳለን፡፡ የታላቋ ሶማሊያ ግዛት አካል ነው፡፡ ግዛታችን አይቆራረስም፤›› የሚል መልዕክት ያለው ሐሳብ ይገኛል፡፡ ይህ የኢልሀን ንግግር ደግሞ ሶማሌላንዳዊያንን፣ ኢትዮጵያውያንን ወይም ኬንያዊያንን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካዊያንን ጭምር ማስቆጣቱ በየማኅበራዊ ሚዲያው ከሚስተጋባው ተቃውሞ መታዘብ ይቻላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1982 በሞቃዲሹ የተወለደችው ኢልሀን ኦማር የነበረውን ጦርነት ሽሽት ያለ እናት የሚንከባከባትን አባት ተከትላ ወደ ኬንያ መሰደዷ ከዚያም ወደ አሜሪካ መግባቷ ይነገራል፡፡ ከደሃና ጎስቋላ የአፍሪካ ክፍል በመውጣት በወጣትነት ዕድሜ የአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ የነቃ ተሳትፎ እስከ ማድረግ መድረስ መቻል የኢልሀን ስኬት ጎልቶ እንዲታይ ያደረገ ነበር፡፡ ለአፍሪካዊያን፣ ለጥቁሮች ብሎም ለሙስሊም ሴቶች አርዓያና የስኬት ምሳሌ ትሆናለች በሚል በብዙ አፍሪካዊያን ዘንድ በጎ ምላሽ ስታገኝ ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ታላቁ የፖለቲካ ስኬት ስትደርስ ባራመደቻቸው አፍሪካን የተመለከቱ አቋሞች ብዙዎችን ማስቀየሟ ነው የሚነገረው፡፡እ.ኤ.አ. በ2019 የሎስ አንጀለስ ከተማ ከንቲባዋ ሴናተር ኬረን ባዝ በሚመሩት የአሜሪካ የኮንግረስ ልዩ ልዑክ ውስጥ ተካታ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ መምጣቷ ይነገራል፡፡ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ በፌስቡክ በወቅቱ እንዳሰፈረው የአሜሪካ ኮንግረስ ከ14 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በላከው ልዑክ ኢልሀን አባል ነበረች፡፡ ልዑኩ በአስመራና በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን፣ ኤርትራና ኢትዮጵያ የፈጠሩትን ዕርቀ ሰላም አወድሶ፣ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለውጥ እንደግፋለን ብሎ መመለሱ በጊዜው በሰፊው ተዘግቦ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 መገባደጃ በኢትዮጵያ ጦርነት ሲፈነዳና ኢትዮጵያ በቀውስ ውስጥ ስትወድቅ ግን ሴናተር ባዝም ሆኑ ኢልሀን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የከረረ አቋም ማራመድ መጀመራቸው መነገር ጀመረ፡፡ ወደ ኮንግረሱ የኢትዮጵያን ጉዳይ በቀዳሚነት ይዘው ከሄዱ ሰዎች አንዷ ኢልሀን እነደነበረች ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ አጎዋ ከሚባለው ከቀረጥ ነፃ የንግድ ዕድል ተጠቃሚነት እንድትወጣም ሆነ በተደጋጋሚ ማዕቀቦች እንድትቀጣ ኢልሀን የአንበሳውን ድርሻ መጫወቷ ይነገራል፡፡ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ በቅርቡ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የባህር በር ስምምነት መፈራረሟ ኢልሀን ወደ ጦር ቀስቃሽ የጥላቻ ንግግሮች እንድትገባ እንዳደረጋት ነው የተነገረው፡፡ ኢልሀን ያሰማችው ታላቋ ሶማሊያ የሚለው ትርክት፣ እንዲሁም በኬንያና በኢትዮጵያ የተዘረፈ መሬት ማስመለስ የሚል ቅስቀሳ በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ቁርሾና እሳት የሚፈጥር መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ለዚህ ንግግር ፈጥነው ምላሽ የሰጡት የሶማሌላንድ የውጭ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ ሮዳ ኤልሚ (አምባሳደር) ሰሞነኛውን የኢልሀን ኦማር ንግግር ዕውቀት የጎደለውና ተጨባጩን የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ ያላገናዘበ ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣናውን ወደ ቀውስ ሊከት የሚችል ታስቦበት የተወረወረ ዘረኛና ጥላቻ አዘል ንግግር መሆኑን ገልጸዋል፡፡‹‹ኢልሀን ኦማር ታላቋ ሶማሊያ (ሶማሊወይን) የሚል አደገኛ ርዕዮተ ዓለም አንስታለች፡፡ በዚህ የተሳከረ ትርክት የተነሳ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ብዙ ጦርነት፣ ግጭት፣ ሞትና ውድመት ሲያስተናግድ መቆየቱን እኛ አሳምረን እናውቃለን፡፡ በንግግሯ በቅጡ አሜሪካዊ መሆን እንኳ ያልቻለችው ኢልሀን በአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች መካከል ጠብ አጫሪ የሆነ የጥላቻ ንግግር መወርወሯ አደገኛ ነው፤›› ሲሉ አምባሳደሯ ተችተውታል፡፡በተለያዩ የመረጃ መረቦች ላይ ኢልሀን ኢትዮጵያና ኬንያ የዘረፉትን የሶማሊያ መሬትን እናስመልሳለን ማለቷ ከባድ ተቃውሞ ከአፍሪካዊያን ሲስተጋባ ነው የሰነበተው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱ አገሮች በይፋ ለዚህ ንግግር ምላሽ ሲሰጡ አልታየም፡፡ የኢልሀን ንግግር በአምባገነኑ የቀድሞ የሶማሊያ መሪ ዚያድ ባሬ ሲቀነቀን የቆየ ከቅኝ ገዥዎች የተወረሰ አፍራሽ ርዕዮተ ዓለም ማንፀባረቁ አደገኛ ነው የሚለው በብዙዎች እየተገለጸ ነው፡፡በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ሰፊ ቆይታ አድርገው የነበሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር)፣ ታላቋ ሶማሊያ የሚባለው ትርክት ከየትና እንዴት እንደተነሳ አብራርተው ነበር፡፡‹‹የፈጠሩት ጣሊያኖች ናቸው፡፡ ጣሊያኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንግሊዞችን ከሶማሌላንድ አባረው መላው ሶማሊያን ጠቀለሉ፡፡ ኢትዮጵያንም ቀድመው ወረው ነበር፡፡ የኢጣሊያ ምሥራቅ አፍሪካ የሚል ከኤርትራ ጀምሮ፣ ኢትዮጵያንና መላው ሶማሊያን የጠቀለለ ግዛት መፍጠራቸውን አወጁ፡፡ ለሰባት ወራት ቢሆንም እንግሊዞችን አሸንፈው ሶማሊላንድን ይዘው ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ሶማሌ ግዛትም ወረው ነበር፡፡ ደቡቡ የሶማሊያ ግዛት ደግሞ በቅኝ ግዛታቸው ሥር ቆይቷል፡፡ ስለዚህ በዚህ ወቅት ነው አንድ ቋንቋ ያለውን የሶማሌ ሕዝብ አንድ ላይ ጠቅልሎ ማስተዳደር ይቻላል የሚለው ጥንስስ የተፈጠረው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የጣሊያኖች ሐሳብ በጥንስስ እንዳለ ተሸንፈው ከአካባቢው ተባረሩ፡፡ በቦታቸው ደግሞ ኬንያን ጭምር ቅኝ የሚገዙት እንግሊዞች ተተኩ፡፡ እንግሊዞቹ የኬንያን ሶማሌ ግዛት ጨምሮ፣ የኢትዮጵያም፣ የጂቡቲም፣ የሶማሌላንድም ግዛት ከሶማሊያ ጋር ተደባልቆ ታላቋ ሶማሊያ የሚባል ግዛት መፍጠር እንደሚቻል ዕቅድ አወጡ፡፡ እንግሊዞች ይህን ዕቅዳቸውን በ1950ዎቹ በይፋ ለኢትዮጵያም አቅርበዋል፡፡ የኦጋዴን ግዛትን ተውልን ብለው ጠይቀዋል፡፡ እንግሊዞቹ ኢትዮጵያን ከኢጣልያ ወረራ ነፃ አወጣን በሚል ውለታ ኦጋዴንና ኤርትራን እ.ኤ.አ. ከ1941 እስከ 1948 ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ ሁለቱን ግዛቶች ላለመልቀቅ ሲታሹም ነው የቆዩት፡፡ የኢትዮጵያ በሳል መሪዎች ባደረጉት ጥረት ግዛቶቹ ተመልሰዋል፡፡ ሆኖም ሀውድ የሚባለው የግጦሽ መሬት ያለበት ከሶማሌላንድ ጋር የሚዋሰን መሬት እስከ 1954 በእንግሊዞች እጅ ቆይቷል፡፡ እንግሊዞቹ የኦጋዴንን መሬት ይዘው በቆዩበት ወቅት በደንብ የዘሩትና ያስፋፉት ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ በሶማሊያ የሚመጡ መንግሥታትም ይህን ወርሰው ባለአምስት ጫፍ ኮኮብ ምልክት ያለው ባንዲራ ሠርተዋል፡፡ አምስቱ ጫፍ የኢትዮጵያን፣ የጂቡቲንና የኬንያን የሶማሌ ግዛቶች ከሶማሊላንድና ከሶማሊያ ጋር አንድ የማድረግ ምልክት ነው፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለም የተነሳ የሶማሊያ ፖለቲከኞች በኬንያና በኢትዮጵያ ላይ ብዙ ትንኮሳ አድርገዋል፡፡ ጦርነትም ከፍተው ኢትዮጵያን ወረው ብዙ ዕልቂት በአፍሪካ ቀንድ አስከትለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960 ጦርነት ከፍተውብናል፣ በ1970 ሌላ ዙር ጦረነት ውስጥ ገብተናል፤›› በማለት ርዕዮተ ዓለሙ እንዴት እንደተፈጠረና ያስከተለውን ቀውስ በሰፊው አስቀምጠዋል፡፡ታላቅ/ግሬተር ብሎ የሚነሳ ርዕዮተ ዓለም ሁሌም ጥፋት ይዞ እንደሚመጣ ምሁሩ ያወሳሉ፡፡ ታላቅ ሲባል ታናናሽ አለ ማለትን እንደሚያመለክት ያስረዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያም፣ ከጂቡቲም ሊያጋጭ እንደሚችልና አሁንም አስተሳሰቡ ጠፍቷል የሚል ግምት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ ኦጋዴን የሚባለው ግዛት ወይም ዛሬ የሶማሌ ክልል የሚባለው ከዓድዋ ጦርነት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የተቀላቀለ ወሰን መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ራስ መኮንን ሐረርን ሲያስገብሩ ወዲያው ይህን አካባቢም ወደ ኢትዮጵያ ቀላቅለውታል፡፡ አካባቢው በቅኝ ግዛት የተፈጠረ ወሰን ወይም ከሶማሊያ ተቆርሶ የመጣ አይደለም፤›› ያሉት ሳሙኤል (ዶ/ር) በታላቋ ሶማሊያ ትርክት ይህን መሬት ማንም የእኔ ነው ሊል እንደማይችል ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በዘመናዊት ኢትዮጵያ አፈጣጠር ታሪክ እንኳ ብናየው ኦጋዴን የሚባለው መሬት ከአንዳነድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቀድሞ ነው የኢትዮጵያ አካል የሆነው፤›› የሚሉት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ ይህን ክልል ኢትዮጵያ ከማንም ቆርሳም ሆነ ሰርቃ አለመውሰዷን አስምረውበታል፡፡ ከሰሞኑ ኢልሀን ያስተጋባችው ታላቋ ሶማሊያ የሚለው ትርክት የሶማሊያ የቀድሞ ፖለቲከኞች መፈክር ሲያደርጉት የኖረ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዚያድ ባሬ በኢትዮጵያ ላይ ጦር ማዝመቱና ድንበራችን እስከ አዋሽ ነው በሚል ወረራ መፈጸሙ በትውልድ ሲታሰብ የኖረ አሰቃቂ ታሪክ ነው፡፡ በውድ የኢትዮጵያ ጀግኖች ወረራው ተመክቶ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ዕብደትም ማስታገሻ እንዲያገኝ ተደርጓል ቢባልም፣ ይሁን እንጂ ለዘመናት አድብቶ በኢልሀን ንግግር ሲስተጋባ መታየቱን አንዳንዶች ገልጸውታል፡፡ ይህ የሶማሊያ ግዛት የኢትዮጵያና የኬንያ ሶማሌዎችን የሚጨምር ነው የሚል የታላቋ ሶማሊያ ትርክት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከሶማሌላንድና ከኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነት በኋላ ጮክ ብሎ መስተጋባት መጀመሩ ይነገራል፡፡ ኢልሀን ይህን የደገመችው ጉዳዩን ለማባባስና በቀጣናው እሳት ለመጫር ባላት ፍላጎት መሆኑ ነው የተነገረው፡፡