

ቀን:
በየማነ ብርሃኑመንገድ የመሠረተ ልማቶች ሁሉ ቁልፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያም ከፍተኛውን በጀት የምትመድበው ለዚሁ ዘርፍ ነው፡፡ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ በአንድ አገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳርፈው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይህ ነው ተብሎ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ታዳጊ ክልል ነው፡፡ የመሠረተ ልማት ተደራሽነቱም ውስን ነው፡፡ በተለይ በመንገድ አቅርቦት ዙሪያ ከሌሎች ክልሎች አንፃር ሲታይ ያለው ሽፋን እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም ለአያሌ ዓመታት በመንገድ ችግር እጅግ ሲፈተን ቆይቷል፡፡በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ጥናትና ዲዛይን ቁጥጥር ኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ በፈቃዱ ዮሴፍ እንደሚናገሩት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመንገድ መሠረተ ልማት አውታር ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር ሲነፃፀር ‹መንገድ አለው› ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ያሉትም ውስን መንገዶች ከደረጃ በታች ናቸው፡፡ ዞንን ከወረዳና ወረዳን ከቀበሌ የሚያገናኙና የሚያስተሳስሩ መንገዶች በተፈለገው ደረጃ ባለመኖራቸው ዛሬም ሕዝቡን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡ለሆስፒታሎችና ለጤና ጣቢያዎች መድኃኒት በወቅቱ ለማከፋፈል፣ ወላድ እናትን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ፣ የተመረተን ምርት ወደ ገበያ ማዕከል ለማቅረብና ሌሎችም ኅብረተሰቡ ሊያገኛቸው የሚገቡ አገልግሎቶች በመንገድ አለመኖርና ያሉትም በአግባቡ ባለመጠገናቸው ምክንያት ኅብረተሰቡ ለከፍተኛ እንግልትና ችግር እየተዳረገ ነው፡፡እንደ አቶ በፈቃዱ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በክልሉ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ እየገነባቸው ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች ባለመጠናቀቃቸውና በመቋረጣቸው፣ ነባር መንገዶችም ለበርካታ ለዓመታት ጥገና ሳይደረግላቸው በመቆየቱ ክልሉን አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈሉት ይገኛሉ፡፡የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በክልሉ የገነባቸውንና የሚያስተዳድራቸውን መንገዶች በወቅቱ መጠገን ባለመቻሉ፣ የክልሉ መንግሥት የማኅበረሰቡን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስና ችግሮቹን ለማቃለል ሲል ባለፉት ሁለት ዓመታት ለመንገድ ጥገና ወደ 39 ሚሊዮን ብር ለማውጣት ተገዷል ብለዋል፡፡ይህም ክልሉ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በገጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የወደሙ መሠረተ ልማቶችንና ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ለማቋቋም ሊያውል የሚገባው በጀት እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሥር የሚገኝና ላለፉት አሥር ዓመታት ወደ ታላቁ የህዳሴ ግደብ የወታደራዊና ለግድቡ ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የሚያጓጉዙ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ሲያስተናግድ የቆየው ባምባሲ – አሶሳ – ኩርሙክ መንገድ ጥገና ሳይደረግለት በመቆየቱ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን መስጠት ከማይችልበት ደረጃ መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መንገዶቹ መበላሸታቸውንና አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው በተደጋጋሚ ቢነገረውም፣ ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና መፍትሔ ማምጣት አለመቻሉን የሚገልጹት አቶ በፈቃዱ፣ መንገዶቹ ለወላድ እናቶች አገልግሎት የሚሰጡ አምቡላንሶች፣ የመድኃኒትና መሰል አቅርቦቶችን የሚያደርሱና ለሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የሚመላለሱበት ከመሆኑ አንፃር ክልሉ ሳይወድ በግድ ከራሱ ካዝና ወጪ አውጥቶ እየጠገነ ይገኛል ብለዋል፡፡በክልሉ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተጀመሩ አዲስና ነባር የመንገድ ፕሮጀክቶች ተቋርጠው ባሉበት እንደሚገኙ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ ሰላም በመስፈኑ የቆሙና የተቋረጡ መንገዶችን ወደ ሥራ ለማስገባት፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ አልታየም፡፡የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በክልሉ በአስፋልት ደረጃ እየገነባቸው የነበሩና የተቋረጡ የመንገድ ፕሮጀክቶች በቁጥር አሥራ ሁለት መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከግልገል በለስ – ድባጤ – ወንበራ፣ የመንገዱ ርዝመት 59 ኪሎ ሜትር፣ ከአይሲድ – ኮንግ – ጉባ – በጎንዲ 62 ኪሎ ሜትር፣ አሶሳ – ዳለቲ (ሎት 1) 36 ኪሎ ሜትር፣ አሶሳ – ዳለቲ (ሎት 2) 69 ኪሎ ሜትር፣ ነቀምት – ሶጌ -ከማሽ 86 ኪሎ ሜትር፣ ያሶ – ጋሌሳ – ድባጢ (ሎት 1) 100 ኪሎ ሜትር፣ ከፓዊ መገንጠያ – ህዳሴ ግድብ 70 ኪሎ ሜትር፣ ከያሶ – ጋሌሳ – ድባጢ – ቻግኒ (ሎት 2) 117 ኪሎ ሜትር፣ ከሆምሻ – ህዳሴ ግድብ (ሎት1) 98 ኪሎ ሜትር፣ ከሆሞሻ – ህዳሴ ግድብ – ጉባ (ሎት 2) 85 ኪሎ ሜትር፣ ቶንጎ – አሶሳ 68 ኪሎ ሜትር ግንባታቸው የተቋረጡ መንገዶች ናቸው፡፡የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ደጀኔ ፈቃደ (ኢንጂነር)፣ ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለከተማ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ በመላ አገሪቱ ካሉት 25 የፕሮጀክት ቢሮዎች መካከል 48 በመቶ የሚሆኑት በፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራቸውን ማከናወን አልቻሉም፡፡በፀጥታ ችግር ምክንያቶች የቆሙ ፕሮጀክቶች ብዛት 62 መሆናቸውንና ከእነዚህ መካከል በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ ቄለምና ሆሮ ጉድሩ የወለጋ ዞኖች የሚገኙ ፕሮጀክቶች፣ አዳማ፣ አዋሽ፣ ባቱ፣ አርሲ ነገሌ፣ ቢልባላ፣ ሰቆጣ፣ ክምር ድንጋይ፣ ጉና፣ እስቴ ስማዳ፣ ጊንጪ ሽኩቴ፣ ሻምቡ አጋምሳ፣ ደብረ ማርቆስ ሞጣ ይገኙበታል ብለዋል፡፡በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች ከተቋረጡ 32 ፕሮጀክቶች መካከል ደግሞ አዲአርቃይ ጠለምት፣ ጋሽና ቢልባላ፣ ጥቁር ውኃ ሐዋሳ፣ ውቅሮ አፅቢ ኩናባ፣ ኮረም ላሊበላ፣ ዓዲሸሁ ደላ ሳምረ፣ ማይጨው መኾኒ፣ ፍየል ውኃ ተከዜና ሌሎችም እንደሚገኙበት ዳይሬክተሩ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡