ልናገር ድርድር የሚያስፈልገው ሕዝባችን “እንደ ገና ዳቦ ማረሩ” እንዲያበቃ ነው

አንባቢ

ቀን: February 7, 2024

በገለታ ገብረ ወልድ

ተወደደም ተጠላም ጦርነት አውዳሚና አክሳሪ ነው። ያውም የእርስ በርስ ጦርነት ተያይዞ መተላለቅን የሚያስከትል፣ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት ፍልሚያ መሆኑን የመስኩ አጥኝዎች  ደጋግመው ያስረዱት እውነት ነው። እንኳንስ በጦርነት ተሠርተን በጦርነት ለቆምነው ኢትዮጵያውያን ይቅርና ለየትኛውም አገር ቢሆን ጦርነትን የሚያስቀር ንግግርና መደማመጥ ከሌለ ትርፉ ጥፋት ነው፡፡

በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት (በካድሬ ቋንቋ ግጭት) ክልሉን ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡን ክፉኛ እያዳከመው ነው። መንግሥት በትግራይ ክልል ብዙ ዋጋ አስከፍሎ በተጠናቀቀው ጦርነት ማብቂያ (የሰላም ስምምነት) ላይ፣ ከአማራ ክልል ታጣቂዎችና ሕዝብ ጋር የሚያግባባ ውሳኔ አለመወሰኑ የቅራኔው መንስዔ እየተደረገ ይነሳል፡፡

በተለይ በሰላምና ድርድሩ ላይ የክልሉ ወጣቶች ጥያቄዎች (የወልቃይታና የራያ የወሰን ጉዳዮች) አለመነሳታቸውና በይደር የተያዘ አጀንዳዎች ዕልባት አለማግኘታቸው፣ ከዚያም አልፎ ወዲያው በክልሉ ያሉ ኢመደበኛ ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ የሚያደርግ እንቅስቃሴ መጀመሩ (ትጥቅ ማስፈታቱ ከሕወሓት ጋር የተደረገ ስምምነት እንደነበር ልብ ይሏል) አለመግባባቱን ቀስቅሷል፡፡ የፌዴራል መንግሥትና የአማራ ክልል ሕዝብ (ፅንፈኛ ብሎ ማቃለሉ አይጠቅምምና) ሁኔታም ፍጥጫ ውስጥ ሊገባ ችሏል፡፡

እሱ ብቻ ሳይሆን ከለውጡ ወዲህ በአገሪቱ በተፈጠሩት አለመረጋጋቶችና ማንነት ተኮር ግጭቶች በየአካባቢው በታሪክ አጋጣሚ ተበታትኖ የሚኖረው የአማራ ሕዝብ የጥቃት ሰለባ መሆኑ ገፊ ፖለቲካዊ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች መሰል መድረኮች አጀንዳውን የፖለቲካ መነገጃ ለሚያደርጉ ኃይሎች ገበያውን ማድሪያ የሆነው ይህ ጉዳይ፣ መንግሥት ሆን ብሎ በቸልተኝነት ሕዝቡን እያስጠቃ ተደርጎ መተረኩ ነበር፡፡ ማፈናቀሉ፣ ቤት ማፍረሱ፣ ከተማ አትግባ መባሉ ሁሉ ባለመግባባቱ እሳት ላይ ቤንዚን ረጩበት፡፡

እዚህ ላይ የፌዴራል መንግሥት ረጋና ሰከን ብሎ፣ የክልሉ መንግሥትም በተለያየ መንገድ እንደ ምሥለኔ የሚታይና ቅቡልነቱ የተሸረሸረ አካል መሆኑን አጢኖ፣ ፅንፈኝነትና የፖለቲካ ጥላቻ አካሄዶች አየሩን እንደሞሉት መርምሮ ማስተካከያ ለመውሰድ መጣር ሲገባው፣ በፀጥታና በደኅንነት ግብረ ኃይል አማካይነት የኃይል አማራጭን መፍትሔ አድርጎ መውሰዱ ትክክል እንዳልነበር የሚተቹ በርካታ ነበሩ፡፡

ለውጡን ከቀየሱ ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክር ቤት ደረጃ አስቸኳይ ጊዜውን እስከ መቃወም ያደረሳቸውም ይኼው ነበር፡፡ ያም ሆኖ በግብታዊነት የተገባበት የአማራ ክልል ትጥቅ ማስፈታትና አማፅያንም ይባሉ ተቃዋሚዎችን የማንበርከክ ዕርምጃ እነሆ ከሰባት ወራት በኋላም መቋጫ አላገኘም፡፡ ሕዝብና አገር ግን ክፉኛ እየተጎዱና ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡

እንዲያውም አሁን በተጨባጭ እየታየ እንዳለው በክልሉ አብዛኛው አካባቢ መንግሥታዊ መዋቅሩ ፈርሷል፣ ወይም  ከገጠሩ ክፍል ጋር ተበጣጥሷል። ትምህርት፣ ጤና፣ ሕዝባዊ አገልግልቶች ከመኖር ወደ አለመኖር ተቀይረዋል። ጦርነት በሚካሄድባቸው ቀጣናዎች ሁሉ ልማት የሚባል ነገር የለም። ፋኖ የተባለው ኃይል ዘመቻው በተጀመረባቸው ቀናት በቁጥጥሩ ሥር አድርጓቸው የነበሩ የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች እስካሁን ይዟቸው ባይቆይም፣ አሁን በሰው ኃይልና በሎጂስቲክስ ራሱን እያሳደገ ወደ አንድ ዕዝ የመምጣት ጥረት እያደረገ መሆኑ ይነገራል፡፡

በጦርነቱ/ግጭቱ ግን አማራ ክልል ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል፣ እየከፈለም ነው፡፡ በዚያም በዚያም የታጠቁ ተፋላሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ንፁኃን ሞተዋል፣ ቆስለዋል። አሁንም ችግሩ ዕልባት ባለማግኘቱ ጉዳቱ ቀጥሏል። ሕዝቡም በርከት ባሉ አካባቢዎች ከመሳቀቅ አልወጣም። ሕግና ሥርዓት እየተዳከመ ታጣቂዎች በአፈሙዝ  የሚነጋገሩበት ሁኔታ ሄዶ ሄዶ የሚያስለቅሰው መከረኛውን ደሃ ሕዝብ ነው፡፡

በቅርቡ መከላከያ  ከገባባቸው አካባቢዎች እንደሚሰማው፣ ‹‹ለፋኖ የመንግሥት ትጥቅህን ሰጠህ›› በሚል የሚታሰሩና የሚከሰሱ ሚሊሻዎች አሉ። ተገድደው የተገፈፉ አመራሮች ሳይቀሩ ተጠያቂ ሆነዋል ሰሜን ሸዋና አካባቢውን ልብ ይሏል፡፡ ፋኖም  በደፈጣም ተዋጋ፣ በፊት ለፊት  አነስተኛ ከተሞችን ሲይዝ፣ ‹‹የመንግሥት ሚሊሻ ነህ፣  ለመከላከያ መረጃ ሰጠህ ወይም ሽምግልና ላይ ተሳተፍክ እያለ ያስራል፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም እስከ መግደል የሚደርስ ዕርምጃ ይወስዳል፤›› የሚሉ ወገኖች አሉ።

መከላከያ በበኩሉ ከተፋላሚዎቹ ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ በሚያምናቸው ላይ ዕርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም። እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ አብዛኛውን አቅም ያለውን ሰው፣ ‹‹እዚያም ሞት እዚህም ሞት›› እንዲል እያደረጉት ሲሆን፣ እጅ አጣጥፎ መቀመጥ ወይም ሰላማዊነት ትርጉም የለውም ወደ የሚል መንገድ እንዳይወስዱት ነገሩን መፈተሸ ይገባል። ቆም ብሎ መመልከትም ብልህነት ነው፡፡

በክልሉ በየትኛውም አካባቢ ተገዶና በተፅዕኖ  ምክንያት ጭምር፣ በአንድም በሌላም ከአንዳቸው ጋር የተገናኘ ሰው ለከፋ ችግር እየተጋለጠ  መሆኑም የሕዝቡን እረፍት የለሽ ኑሮ ያሳያል። አብሮ በኖረ መስተጋብር ውስጥ ከማንም ጋር አልገናኝም ብሎ መቀመጥ ደግሞ እንደሚታሰበው ቀላል አልሆነም። ይህ መሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው ከመነጋገርና ከመደራደር የተሻለ የትኛው አማራጭ የክልሉንም ሆነ የአገሪቱን ችግር ሊፈታው ይችላል የሚያስብለው፡፡ ሕዝብ እኮ ተቸገረ፣ ተንገፈገፈ፡፡

እውነት ለመናገር ሕዝቡስ ምን ይሁን!?  ባልተገባ መንገድ እንደ ገና ዳቦ ከላይም ከታችም እየተጠበሰ የሚኖረውስ እስከ መቼ ነው የሚሉ ጥያቄዎች እየበረቱ መጥተዋል። በክልሉ አንድ አነስተኛ ወረዳ በመምህርነት ሙያ አገሯን ስታገለግል የነበረችው መምህር ሳምራዊት በ. ከላይ የተነሳውን ሐሳብ ጨምራ ‹‹ታደጉን!! እባካችሁ መንግሥትና ተፋላሚዎች ብቻ ሳትሆኑ መላው የሕዝብ ደኅንነት ጉዳይ የሚመለከታቸው አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት ድረሱልን›› በማለት ጥሪ ያቀረበችው ለዚሁ ይመስለኛል፡፡ መፍትሔ እንዲመጣ አግዙን በማለት ተማፅናለች።

በመሠረቱ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡ በእነዚህ ወቅቶች በጨቋኝና በተጨቋኝ ትርክት፣ በአሸናፊና በተሸናፊ ፍልሚያ ውስጥ የኖሩ የአገሪቱ አገዛዞች ወደ ሕዝቦች ወርደው አገራችን ኢፍትሐዊነት፣ ፀረ ዴሞክራሲና ድህነትን የመሳሰሉ ፅልመቶችን ተከናንባ ቆይታለች፡፡ የአሁኑ ትውልድም ቢሆን ለዘመናት በሕዝብ ውስጥ ሲብሰከሰኩ የኖሩ ችግሮችን በጋራና በሚዛናዊነት ለመፍታት፣ ብሎም ከልዩነትና ከመካረር ይልቅ አንድነትና አብሮነትን የሚያጎሉ ተግባራትን ለመሥራት ጥረት ያድርግ፡፡ ነገር ግን የተጠመደው በነባሩ ትርክት ውስጥ ነበር፣ እውነት ለመናገር ጊዜም አላገኘም፡፡

ያለፈው መንግሥት አሁን ለምንገኝበት የቀውስ አስተዳደር ካድሬዎቹንና ከፊል የአመራር ሥልቶቹን ብቻ ሳይሆን ያስተላለፈው ቂምና ቁርሾን፣ ያልተፈቱ የወሰን፣ የማንነትና የፖለቲካ ውዝግቦችን ብሎም ፅንፈኛ የፖለቲካ ዕይታዎችን ጭምር ነው የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡ በዚህም የሕዝብን የተከማቹ ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ መመለስ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ባላንጣዎችና የፖለቲካ ነጋዴዎች እንዲሁም ፅንፈኛ ሴራቸውን እንደ ምቹ አጋጣሚ የተጠቀሙበት ኃይሎች በፈጠሯቸው ተደጋጋሚ ቀውሶች፣ የአገር ህልውናን ከመፈታተን ጀምሮ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ የአገር ገጽታ እያጠቆረ ተስፋንም እያጨለመ ነው።

በእርግጥም ትናንት በትግራይና በኦሮሚያ፣ አሁን ደግሞ በአማራ ክልል ከሞላ ጎደል  ወደ ሙሉ ጦርነት ያደገ ውጊያ እየተካሄደ በሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ልጆች እየተላለቁ መሆኑ የሚያስቆጭ ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ንፁኃን በድሮንና በከባድ መሣሪያ ሳይቀር እየረገፉ መሆናቸው ይነገራል፡፡ የመንግሥት ተሿሚ በመሆናቸው ብቻ በደፈጣ የሚገደሉ የቤተሰብ ኃላፊዎች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ የእምነት ተቋማትና መሪዎቻቸው ይፈርሳሉ፣ ይገደላሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ወደ ሰላም ካለመምጣት፣  ካለመነጋገርና ካለመደማመጥ የሚመጡ ቀውሶች ናቸው፡፡

በየክልሉ የተጀማመሩ መሠረተ ልማቶችና ኢንቨስትመንቶች እየቆሙ፣ ጭራሽ  የደሃ አገር ሀብት እሳት እንደነካው ቡቃያ በየሜዳውና በየሸንተረሩ ወደ አመድነት ይቀየራል፡፡ ተሽከርካሪዎች ከእነ ሙያተኞቹ ይታገታሉ፣ ይዘረፋሉ፡፡ በዚህም እንኳን  ሁሉ አቀፍ ዕድገት ሊመጣ ድህነትና ኑሮ ውድነት እየተባባሱ መጭውን ወቅት የመከራ ዘመን እንዳያደርጉት እጅጉን ተፈርቷል፡፡ ግን በፖለቲካ ብልሽት ምክንያት እስከ መቼ ሕዝብ የገና ዳቦ ይሆናል ብሎ በቃ ማለት ያስፈልጋል፡፡

“በቦሃ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ በፀጥታው ሥጋት የተነሳ፣ የዴሞክራሲ ንፍቀ ክበቡ ካለፉት ወቅቶች በባሰ ደረጃ መጥበቡና የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ገና እየተቃለሉ ባለመሆናቸው የመነጋገርና የመደማመጥ ባህላችንን አዳክሞት ሊሆን ይችላል፡፡ አገራችን በእንዲህ ያሉ ጫናዎች ውስጥም ሆና ግን ሜጋ ፕሮጀክቶችንና እንደ ወደብና የባህር በር ዓይነት አንገብጋቢ አጀንዳዎችን ስታነሳ፣ የብዝኃኑ ዜጋ ፍላጎት ቀዝቀዝ ያለበት ምክንያት የብሔራዊ መግባባቱ አለመጎልበት የወለደው እንቅፋት ነው ሊባል ይችላል፡፡ እባካችሁ እንቀይረው መባባል አለብን፡፡

መንግሥት በአንድም ሆነ በሌላ አገር የመምራት ዕድል አግኝቷል፡፡ በመሆኑም ከሞላ ጎደል ሕዝብ የተሳተፈበትና ያመነበትን ዕቅድና ራዕይ ሰንቆ እስከ ተወሰነለት የምርጫ ጊዜ ድረስ አገር የመምራት ሥልጣን አለው፡፡ በተገደቡት እነዚህ ዓመታት ታዲያ ማንም ቢሆን ለማደናቀፍ ያውም በኃይል ለማፍረስ ሲሞክር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዳናጋ መቆጠሩ አይቀርም፡፡ ድርጊቱ ትክክልም አይደለም፡፡ ይህን ለማስተካከል በሚል ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፀጥታ ተቋማትና አመራሮች በጭፍን ሲወስዱት የሚታየው የኃይል ዕርምጃም ቀውስ እንዳይፈጥር ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡

ሌላው ቀርቶ ለሕግ አልገዛም ያሉና ‹‹ፀረ ሰላም ድርጊት›› ውስጥ የመግባት አካሄድ የሚከተሉ አካላትን በጠንካራ ፖለቲካና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ከሕዝብ ነጥሎ መታገል እንደ አንድ ሥልት መወሰድ አለበት፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ተፋላሚዎች በሕዝብ ስም ያነሱት ጥያቄ በሚዛን ማየትና እንደ በአመንክዮ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ጉልበትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መዘመትም ያልተጠበቀ ውድ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑ መጤን ነበረበት፡፡ አሁንም የሕዝቡ መከራና ሥቃይ ሰሚ ሊያገኝ ይገባል፡፡

ትናንት ሕዝብና መንግሥትን ያጋጩ በርካታ ጉዳዮች በአጭር የሥራ ዘመን መፍትሔ ያገኛሉ ማለት አይቻልም፡፡ ቢያንስ ግን ጥያቄዎች የሚመለሱባቸው ምልክቶች፣ የጋራ ችግሮች የሚቀረፉባቸው አቅጣጫዎች፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ጭላንጭሎች መታየት አለባቸው፡፡ ትናንትም ሆነ አሁን ሕዝብ ለመንግሥት ያቀረባቸው በርካታ ጥያቄዎች በተቻለ መጠን በውይይት፣ በሕግና በሥርዓት መመለስ ሲችሉ ነው የሕዝቡ ዕንባ የሚታበሰው፡፡

በእርግጥ በተፈጠረው የፖለቲካ አለመደማመጥና ቀውስ ምክንያት በአምስት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ስድስት ጊዜ ያህል አስቸኳይ አዋጅ ታውጆ ችግሮችን ማርገብ ባያስችልም፣ በርካታ አገራዊ ጫናዎችን ሲፈጥር ቆይቷል። ያም ሆኖ ግን ለዘላቂ ሰላም የሚሹ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመምከር ሁነኛ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ መደበኛ ሕጎችን እየሻሩ አገር ለመምራት መሞከር ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ ሲያጋልጥ ታይቷል፡፡ የአገር ገጽታን ሲያጨልም ነው የቆየው፡፡ እናም አሁንም ከአዋጁ ይልቅ ንግግር መጀመር ነው የሚሻለው የሚሉ ሰዎች መደመጥ አለባቸው፡፡

እውነት ለመናገር አሁን ካለው የተዳከመ ሁኔታ ለመውጣት ከጦርነትና ከኃይል ይልቅ መነጋገርና በሰጥቶ መቀበል መርህ መፍትሔ መፈለግ ለማንም ሆነ ለምንም የሚጠቅም ነው፡፡ የንፁኃን ሞትና መቁሰል ብቻ ሳይሆን ሕዝብ በገዛ አገሩ የባይተዋርነት ስሜት እየተሰማው፣ ተንቀሳቅሶ መሥራትና መኖር ተስኖትና ደኅንነት አጥቶ መኖር የከፋ ጉዳት ነው፡፡ ስለሆነም እንደ አገር ከገባንበት ድባቴ ውስጥ ወጥቶ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር መሞከር ነው የሚበጀው፡፡ እንንቃ ጎበዝ፡፡

ሕዝብም ዕፎይ ይበል፡፡ በማንነትና በእምነት ምክንያት መጠቃቃቱ፣ ዘረፋና ዕገታው፣ ሞትና ስደቱ ተባብሶ በሰቆቃ መኖር ካለመኖር የሚሻል አይደለም፡፡ በእነዚህና ተመሳሳይ ሳንካዎች ምክንያት የሚታየው የምጣኔ ሀብት መዳከም በተለይ ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እየደቆሰው መገኘቱ ሌላው ራስ ምታት ስለሆነ ሁላችንም በቃን እንበል፡፡ ከዚህ ሁሉ ለመውጣት ደግሞ ሆደ ሰፊ ሆኖ መነጋገርና መደራደር ነው መፍትሔ የሚያመጣው፡፡

በመጣንበት መንገድ መንግሥት ሁልጊዜም ጉልበተኛና ለየት ያሉ ጥያቄዎችንም ጨፍልቆ የሚኖር ነበር፡፡ አሁን እሱ አካሄድ እንደማያዘልቅ በየቦታው ባሉ ግጭቶችና የውስጥ መታመሶች እየታየ ነው፡፡ ስለሆነም ቁጭ ብሎ የመነጋገር መፍትሔንም መመልከት አስገዳጅ መስሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት በሆደ ሰፊነትና አንድ ዕርምጃ ቀርቦ መፍትሔዎችን በማማተር አርዓያ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚታዩት ብዙዎቹ የፖለቲካ ስብስቦችም ኋላቀር፣ ከሥልጣኔ ጋር የማይተዋወቁ፣ ለሰጥቶ መቀበል መርህ ቦታ የማይሰጡ፣ በጭፍን ጥላቻ የተዋጡ፣ ከውይይትና ከድርድር ይልቅ እልህና ጉልበት የሚበረታባቸው፣ በሸፍጥና በሴራ የተተበተቡ ናቸው፡፡ ቡድንተኝነት የሚያጠቃውን የትግል ሥልታቸውን አሽቀንጥረው መጣል አለባቸው። ግትርነቱና ያገኘሁትን ዕድል ካልሞትኩ አሳልፌ አልሰጥም ባይነትም አገር ይበትናል እንጂ አዋጭ አይደለም፡፡ እንንቃ፡፡

ዴሞክራሲ ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት፣ የማያስማሙ ጉዳዮችን እያቻቻሉ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ የሚግባቡበት፣ ከኃይል ይልቅ ውይይትን የሚያስቀድሙበትና ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ የሚሆኑበት ነፃ መድረክ እንጂ ጉልበተኞች የሚፈነጩበትና አላዋቂዎች የሚቀልዱበት መድረክ አይደለም፡፡ እናም የትኛውንም አስተሳሰብና ዓላማ የሚያራምዱ ሕዝቡን ለሚያሳርፍ አገራዊ ምክክርና የሰላም ዕድል ትኩረት ይስጡ ማለት እወዳለሁ፡፡ የሕዝብ ዕንባ ይታበስ አገርም ዕፎይ ትበል የዕለቱ መልዕክቴ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡