

ቀን:
በየመን ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት የሃውቲ ታጣቂዎች ከሁለት ወራት በፊት በቀይ ባህር ላይ ስትጓዝ የነበረችና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላት የተባለቸውን መርከብ መምታታቸውና በጥቃቱም መቀጠላቸው፣ በዓለም ዋና የመርከብ መጓጓዣ ከሆኑት አንዱ የሆነውን የቀይ ባህር ስዊዝ ካናል የባህር መንገድ አስተጓጉሏል፡፡እስራኤል በፍልስጤም ጋዛ እየፈጸመች ያለውን ወታደራዊ ዕርምጃ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ የመናውያን ጋር በመሠለፍ ተቃውሞ ያሰማው የሃውቲ ታጣቂዎች ቡድን፣ እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ እያደረሰች ያለውን ስቃይ እንደሚቃወም በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡15 በመቶ የዓለም መርከቦች የሚጓጓዙበትና ከእስያ ወደ አውሮፓ ለማቅናት አጭር ነው የሚባለው የቀይ ባህር ስዊዝ ካናል መንገድ፣ መርከቦች ላይ በሚደርስ ጥቃት ምክንያት ከአገልግሎት መስተጓጎሉ፣ የመንገዱ ተጠቃሚ የጭነት መርከቦች አቅጣጫ እንዲቀይሩ አስገድዷል፡፡
ቢቢሲ እንደሚለው፣ እስከ 300 ሜትር ርዝማኔ ያላቸውን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መርከቦች፣ በአፍሪካ የሚገኙ ረዣዥም የባህር መንገዶችን እንዲጠቀሙም እያደረገ ነው፡፡በኅዳር 2016 ዓ.ም. አጋማሽ የተጀመረው የሃውቲዎች የመርከብ ጥቃት፣ ከአልባሳት እስከ ቡናና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች የዋጋ ንረትን እንደሚያስከትልም ታይም አሥፍሯል፡፡ የጭነት ማቅረቢያ ጊዜ የሚራዘም በመሆኑም ተፅዕኖው በተጠቃሚው ዘንድ በቅርብ መታየት ይጀምራል፡፡እስከ ታኅሣሥ መጀመሪያ የሃውቲ ታጣቂዎች በ25 የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ሃውቲ ጥቃት እየፈጸመበት የሚገኘው የባህር መንገድ በአብዛኛው እስያንና የአፍሪካን የተወሰኑ ክፍሎች ከአውሮፓ የሚያገናኝ ነው፡፡ ነዳጅ ከባህረ ሰላጤው አገሮች ወደ ደቡብ አሜሪካ ለማጓጓዝም ያገለግላል፡፡በዓለም አቀፍ ደረጃ በባህር ላይ ተጓጉዘው ለንግድ ከሚውሉ ምርቶች 15 በመቶ ያህሉን በሚያስተናግደው በዚሁ መስመር፣ ስምንት በመቶ የሰብል ንግድ፣ 12 በመቶ የነዳጅ ንግድ፣ ስምንት በመቶ የዓለም የቀዘቀዘ/የረጋ የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ የመርከብ ጭነቶችን ያስተናግዳል፡፡30 በመቶ የዓለም ሸቀጣ ሸቀጦች በስዊዝ ካናል እንደሚያልፉ ያስታወሰው ታይም፣ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት ሃውቲዎች በጀመሩት የመርከብ ላይ ጥቃት የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁሟል፡፡የቀይ ባህር የመርብ መጓጓዣ መንገድ በስዊዝ ካናል የሚያልፍ መሆኑ፣ አጭርና ርካሽ እስያን፣ አፍሪካንና አውሮፓን ለማገናኘት በጣም አዋጭ መንገድ እንደሆነም አክሏል፡፡በርካታ መርከቦች መንገድ ለመቀየር በመገደዳቸው ጉዟቸው ለሁለት ሳምንታት የሚዘገይና የዋጋ ጭማሪ የሚያስከትልም ይሆናል፡፡ ከእስያ ወደ አውሮፓ ኮንቴይነር ለመጫንም ከ175 እስከ 250 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡እስራኤል በፍልስጤም ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ ዕርምጃ በመቃወም፣ በደቡባዊ እስራኤል የሚሳየልና የድሮን ጥቃት ሰንዝሮ ዒላማውን መምታት ያልቻለው የሃውቲ ቡድን፣ በመርከብ ላይ ጥቃት መሰንዘር የጀመረው እስራኤል በፍልስጤም ጋዛ የምታካሂደውን ጦርነት እንድታቆም ዓለም አቀፍ ጥሪ ሲቀርብላት አሻፈረኝ ማለቷን ተከትሎ ነው፡፡በርካታ መርከቦችን በመያዝ በወደቦች ያስቀመጡት ሃውቲዎች፣ ከእስራኤል ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መርከቦች እሚያሠጋቸው ነገር እንደሌለ፣ ዕርምጃ የሚወስዱት በእስራኤል መርከቦች፣ ወደ እስራኤልና ከእስራኤል ቁሳቁሶችን በሚጭኑት ብቻ ነው ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡የሃውቲ ታጣቂዎች የቀይ ባህር ስዊዝ ካናልን የሚጠቀሙ መርከቦችን ማጥቃታቸው ማንን ይጎዳል?እስራኤል የመጀመሪያ ተጎጂ ስትሆን፣ ተፅዕኖውም አሁን መታየት ጀምሯል፡፡ ከእስራኤል የፍልስጤም ጋዛ ጦርነት በፊት ኢኮኖሚያዊ ችግር ገጥሟት የነበረችው ግብፅ፣ የስዊዝ ካናል የንግድ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ ተጎጂ ትሆናለች፡፡ ግብፅ በአብዛኛው የምትመረኮዝበት ከስዊዝ ካናል መተላለፊያ የሚገኝ ገቢ መቀነሱም፣ አብዝቶ የሚጎዳት ይሆናል፡፡የሃውቲ ታጣቂዎች በመርከቦች ላይ የሚያደርጉን ጥቃት ለረዥም ጊዜ የሚቀጥሉ ከሆነ፣ በአውሮፓና በሜዲትራንያን አካባቢ ያሉ አገሮች ይጎዳሉ፡፡