የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ

ከ 4 ሰአት በፊት

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሐማስ ያቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሃሳብ በወራት ውስጥ በጋዛ “ሙሉ ድል መቀዳጀት” ይቻላል በማለት ሳይቀበሉት ቀሩ።

ኔታንያሁ ይህን ያሉት አዲስ ለቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ምላሽ ለመስጠት ሐማስ ጥያቄዎች ማቅረቡን ተከትሎ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቡድኑ ጋር የሚካሄድ ድርድር “የትም አይደርስም” ያሉ ሲሆን ሐማስ ያቀረበውን ጥያቄም “አስገራሚ” ብለውታል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ አሁንም ንግግሮች እንደቀጠሉ ነው።

ሆኖም ኔታንያሁ ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ ከድል ውጭ ሌላ አማራጭ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

“ሐማስ በጋዛ ነፍስ እንዲዘራ የምንፈቅድ ከሆነ በቀጣይ ለሚፈፅመው ጭፍጨፋ ጥያቄው የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው የሚሆነው” ብለዋል።

እስራኤል ሐማስ ላቀረበው ሃሳብ አዎንታዊ ምላሽ ትሰጣለች ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ሳትቀበለው ቀርታለች።

የእስራኤል ባለሥልጣናትም ሐማስ በራሱ ጊዜ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያደርገውን ጥረት ተቀባይነት የሌለው አድርገው ተመልክተውታል።

የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሳሚ አቡ ዙሁሪ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የኔታንያሁን ንግግር “ “ፖለቲካዊ ድፍረት” ያሉ ሲሆን ይህም በቀጠናው ያለው ግጭት እንዲቀጥል ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አንድ ግብጻዊ ባለሥልጣን በግብፅ እና በኳታር አደራዳሪነት በአዲስ ዙር የሚካሄዱት ድርድሮች በካይሮ እስከ ሐሙስ ድረስ እንደሚቀጥሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግብፅ ሁለቱ ተፋላሚ አካላት ስምምነት ላይ ለመድረስ ግትርነታቸውን እንዲተው ጥሪ ማቅረቧንም እኝሁ የቢቢሲ ምንጭ ገልጸዋል።

ኔታንያሁ “ ቅዠት” ያሉትን እቅድ ሳይቀበሉት መቅረታቸው የሐማስ ምላሽ ‘አዎንታዊ’ መሆኑን ከገለጸችው የኳታር አስተያየት ጋር ተቃርኗል።

ሐማስ ለቀረበለት የተኩስ አቁም ስምምነት ቅድመ ሁኔታውን ያስቀመጠው ማክሰኞ ዕለት ነበር።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የተመለከተው የሐማስ ረቂቅ ሰነድ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች በምዕራፍ ከፍሎ አስቀምጧል።

የቀረበው ረቂቅ ስምምነት ለጋዛ የሚቀርበው ምግብ እና ሌሎች ሰብዓዊ እርዳታዎች አቅርቦት እንዲጨምርም ይጠይቃል።

በ135 ቀናቱ የተኩስ አቁም ፋታም ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው ድርድር እንደሚጠናቀቅም ሐማስ ገልጿል።

ሐማስ ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በደቡባዊ እስራኤል በፈፀመው ጥቃት ወደ 1 ሺህ 300 የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።

እስራኤል ለዚህ ጥቃት የአጸፋ እርምጃ መውሰድ ከጀመረች በኋላም ከ27 ሺህ 700 በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን ቢያንስ 65 ሺህ ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።