
ከ 5 ሰአት በፊት
ማዳጋስካር ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናትን በመድፈር ጥፋተኛ የተባሉ ወንዶች ብልት እንዲሰለብ ያወጣችው ሕግ እንዲሻር ተጠየቀ።
አገሪቷ ህጻናትን በመድፈር ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ግለሰቦች በኬሚካል እና ቀዶ ህክምና ብልታቸው እንዲሰለብ ሕግ ማውጣቷ ተቀባይነት እንደሌለው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም አምነስቲ አስታውቋል።
ሕጉንም “ኢ ሰብዓዊነትን የተላበሰ፣ ጭካኔ የተሞላበት እና የሰውን ልጅ የሚያዋርድ ነው” ሲል አምነስቲ ፈርጆታል።
ባለፈው ወር የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አንድሪ ራጆሊካ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ ላይ ማሻሻያዎችን አቅርበዋል።
በዚህም ማሻሻያ መሰረት ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናትን በመድፈር ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ግለሰቦች በኬሚካል እና በቀዶ ህክምና ብልታቸው እንዲሰለብ የሚጠይቅ ቅጣት ነው።
እነዚህ ማሻሻያዎችም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተዋል።
በማዳጋስካር የመደፈር ወንጀሎች በአብዛኛው ሪፖርት እንደማይደረጉ አምነስቲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
- ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት ብሪክስ ተግባራዊ ማድረግ የሚፈልገው ምንድን ነው?ከ 6 ሰአት በፊት
- አራት ተማሪዎችን ተኩሶ የገደለው አሜሪካዊ ታዳጊ እናት ኃላፊነቷን ባለመወጣቷ ጥፋተኛ ተባለች7 የካቲት 2024
- “ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የመዋጋት ፍላጎት የላትም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ6 የካቲት 2024
ይህም ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው የበቀል ጥቃት ይደርስብናል በሚል ስጋት፣ ማኅበረሰቡ ያገለናል እንዲሁም በፍትህ ሥርዓቱ ላይ እምነት በማጣት እንደሆነም የአምነስቲ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ቲገሬ ቻጉታህ ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ወንጀለኞች ነጻ የሚሆኑበት ሁኔታ መንሰራፋቱን አውስተዋል።
ሆኖም ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህጻናትን በመድፈር ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ግለሰቦችን በኬሚካል እና በቀዶ ህክምና ብልታቸውን በመስለብ መቅጣት “ኢ ሰብዓዊነትን የተላበሰ፣ ጭካኔ የተሞላበት እና የሰውን ልጅ የሚያዋርድ እና ችግሩንም የማይቀርፍ ነው” ሲሉም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ዳይሬክተሩ አክለውም “ይህ ሕግ ማሰቃየትን እና ሌሎች እንግልቶችን ተግባራዊ በማድረግ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎችን የሚጥስ ነው” ብለዋል።
“የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚጣረስ እንዲሁም ከማዳጋስካር ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ጋር የሚቃረን ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተውታል።