የወቅቱ የብሪክስ ፕሬዝዳንት የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን
የምስሉ መግለጫ,የወቅቱ የብሪክስ ፕሬዝዳንት የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን

ከ 6 ሰአት በፊት

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤምረትስ ዋነኛ ከሚባሉት የዓለማችን የአገራት ስብስብ መካከል አንዱ የሆነውን፣ የአምስት መሥራች አገራት ጥምረቱን ብሪክስን እንደሚቀላቀሉ ባለፈው ዓመት ታውቋል።

በዚህም አዲሶቹ የብሪክስ አባል አገራት በተጀመረው የአውሮፓውያኑ 2024 በይፋ የጥምረቱ አባል መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ የሳዑዲ አባልነት በዚህ ወቅት መጀመሩ እስካሁንም አልተረጋገጠም።

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የመሠረቱት ይህ ስብስብ በዓለም አቀፉ ፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት ላይ የበለጠ ተጽኖ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ።

ብሪክስ እና አዲሶቹ አባላቱ

በ2006 ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና “ብሪክ” የተባለውን ቡድን ፈጠሩ። ደቡብ አፍሪካ የተቀላቀለችው እአአ በ2010 ሲሆን ስያሜያቸውም “ብሪክስ” ተሰኘ።

ቡድኑ የሰሜን አሜሪካ እና የምዕራብ አውሮፓ የበለጸጉ አገራትን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኃይል ለመቋቋም እና ለመገዳደር በዓለም ላይ በጣም ወሳኝ የሚባሉ በመልማት ላይ ያሉ አገራትን አንድ ላይ ለማሰባሰብ ያለመ ነው።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከአውሮፓውያኑ ጥር 1/2024 ጀምሮ አባል እንዲሆኑ ተጋብዘዋል።

አንድ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ሚኒስትር እስከ ጥር ወር አጋማሽ ድረስ አገራቸው ስብስቡን እንዳልተቀላቀለች ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግስት ግን ሳዑዲ አባል መሆኗን አረጋግጧል።

የሳዑዲው ንጉሥ ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ቤይጂንግ ውስጥ (እአአ 2017)
የምስሉ መግለጫ,የሳዑዲው ንጉሥ ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ቤይጂንግ ውስጥ (እአአ 2017)

አርጀንቲና ብሪክስን እንድትቀላቀል ግብዣ ቀርቦላት ነበር። አዲሱ ፕሬዝዳንት ሃቪየር ሚሌ ሥልጣን በያዙ ማግሥት አገራቸው ወደ ጥምረቱ እንደማትገባ አሳውቀዋል።

ቡድኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች አዘጋጅቶ በዓመታዊ ስብሰባው ላይ ውሳኔ ይሰጥበታል። ሁሉም አባል አገራት በዙር ለአንድ ዓመት ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለግላሉ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ተጨማሪ አምስት አባል አገራትን ያካተተው ቡድን ስም እስካሁን በይፋ ባይገለጽም “ብሪክስ ፕላስ” ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ።

ብሪክስ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

ብሪክስ እንደ ቻይና እና ሩሲያ ያሉ ታላላቅ የዓለም ኃያላን አገራትን አቅፏል። በአህጉራቸው ላይ ተጽዕኖ ያላቸውን እንደ ደቡብ አፍሪካ እና ብራዚል ያሉ አገራትም አሉ።

የተስፋፋው ቡድን ወደ 3.5 ቢሊዮን ሕዝብን ይወክላል። ይህም 45 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ማለት ነው።

የአባላቱ ድምር ምጣኔ ሀብት ከ28.5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ አለው። ከዓለም ኢኮኖሚ 28 በመቶውን ማለት ነው።

ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን በአባልነት የሚያካትተው የብሪክስ አገራት ቡድን 44 በመቶ የሚሆነውን ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ያመርታሉ።

ቡድኑ የምዕራባውያን አገሮች እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ያሉ እንዲሁም ለመንግሥታት ብድር የሚሰጡ ጠቃሚ ዓለም አቀፍ ተቋማትን እንደሚቆጣጠሩ ይከራከራሉ።

ከዚህ አንጻር በመልማት ላይ ያሉ አገራት “የበለጠ ድምጽ እና ውክልና” እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ።

እአአ በ2014 የብሪክስ አገራት መሠረተ ልማትን ለማሳደግ የሚያግዝ ገንዘብ የሚያቀርብ አዲስ ልማት ባንክ አቋቁመዋል።

እአአ በ2022 መገባደጃ ላይ ለአዳዲስ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የባቡር መስመሮች እና የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች 32 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለአገራት አቅርቧል።

የደብሊኑ ትሪኒቲ ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ፓድራግ ካርሞዲ እንደተናገሩት ቻይና የመሠረተ ልማት ጉዳይ የብሪክስ ዋና ዓላማ እንዲሆን ትፈልጋለች።

“ቻይና በብሪክስ በኩል በተለይም በአፍሪካ ላይ ኃይሏን እና ተፅዕኖዋን ለማሳደግ እየሞከረች ነው። የደቡቡ ዓለም መሪ ድምጽ መሆንም ትፈልጋለች።”

በቡድኑ ውስጥ በአባልነት ያለችው ሌላኛዋ የዓለም ኃያል አገር ሩሲያ ደግሞ የተለየ ዓላማ አላት።

በለንደን የሚገኘው የቻተም ሐውስ የጥናት ቡድን ባልደረባ የሆኑት ክሪዮን በትለር “ሩሲያ [ብሪክስን] ከምዕራቡ ዓለም ጋር የምታደርገው ትግል አካል አድርጋ ትመለከታለች። ከዩክሬን ወረራ በኋላ የተጣለውን ማዕቀብ ለማሸነፍም ይረዳታል” ብለዋል።

የኢራን አባልነት የብሪክስን ፀረ-ምዕራባዊ ባህሪ ሊያሳድገው ይችላል ሲሉም አክለዋል።

ግራፍ

የብሪክስ ገንዘብ ዶላርን ይተካል?

መንግሥታት ብዙ ጊዜ የአሜሪካ ዶላርን በመጠቀም እርስ በርስ ግብይት ይፈጽማሉ።

በብራዚል እና በሩሲያ ያሉ ታዋቂ ፖለቲከኞች የዶላርን የበላይነት ለመቀነስ የብሪክስ ገንዘብ አንዲጀመር ሃሳብ አቅርበዋል። ይህ ግን በ2023ቱ የቡድኑ ስብሰባ ላይ አልተነሳም።

የብሪክስ አገራት ኢኮኖሚ በጣም የተለያየ ስለሆነ የጋራ መገበያያ ገንዘብ መፍጠር ተግባራዊ ሊሆን አይችልም ይላሉ ፕሮፌሰር ካርሞዲ።

ሆኖም “ለዓለም አቀፍ ንግድ ክፍያዎች የሚውል አዲስ ምንዛሪ ለመፍጠር ወይም ለዓለም አቀፍ ንግድ የሚውል ክሪፕቶከረንሲ መፍጠር ላይ ወደፊት ሊያስቡበት” እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ብሪክስ የጂ20 ተቀናቃኝ ነው?

የቡድን 20 (ጂ20) በ1999 (እአአ) በበለፀጉ እና በማደግ ላይ ባሉ አገራት ተቋቁሟል። ዓላማውም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ነው።

የብሪክስ ቡድን በጂ20 ውስጥ ያሉት በርካታ አገራትንም አካቷል።

የዓለም አቀፍ የስትራቴጂ ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር አይሪን ሚያ ወደፊት አብረው ሊሠሩ ይችላሉ ብለዋል።

“በጋራ ሆነው በማደግ ላይ ላሉ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ግፊት ሊያደርጉ ይችላሉ” ብለዋል።

ሩሲያ ምን ለማድረግ አስባለች?

ሩሲያ በሚመጣው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ካዛን ውስጥ የ2024ቱን የብሪክስ ስብሰባ ታስተናግዳለች።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሚከተሉትን ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡

“ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ብትፈጽምም አሁንም በሌላው ዓለም ወዳጆች እና አጋሮች እንዳሏት ለምዕራቡ ዓለም ማሳየት ትፈልጋለች” ይላሉ ዶክተር ሚያ።