
ከ 3 ሰአት በፊት
በቅርቡ ከሥልጣን የተሰናበቱትን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን በመተካት አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ተሾሙ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ባደረገው 15ኛ መደበኛ ስብሰባው የአቶ ተመስገን ጥሩነህ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመትን አጽድቋል።
በሌላ በኩል በዛሬው የምክር ቤት ውሎ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
በቅርቡ ከሥልጣን የተሰናበቱት ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነትን ደርበው በመያዝ ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን በዛሬውም በምክር ቤቱ ውሎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ተችሯቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቀድሞ ምክትላቸው አቶ ደመቀ ጋርም በምክክር እና በውይይትም የአሁኑ ውሳኔ ላይ እንደተደረሰ ገልጸዋል።
“ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ ስልጣን መረካከብን እና ኢትዮጵያን ላገለገሉበት እናመሰግናለን ተብሎ መሄድ ተጨማሪ ክብር ነው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነግረዋል።
ዐቢይ አቶ ደመቀ መኮንን ለባለፉት 32 ዓመታት ኢትዮጵያን በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ማገልገላቸውን አውስተው “በብልጽግና በነበረው የመተካካት አሰራር መሰረት ላሳደጉት ለመሩት ሰው ስልጣናቸውን በፓርቲም በመንግሥትም አስረክበው በፍቅር እና በክብር ዛሬ ከአስፈጻሚነት ኃላፊነታቸው ተሸኝተዋል” ብለዋል።
ምክር ቤቱም ለቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ምስጋና እንዲያቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ አጋጣሚ ጠይቀዋል።
በዛሬው የምክር ቤት ውሎ የሶስት ሚኒስትሮች ሹመት የጸደቀ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታን የተረከቡት አምባሳደር ታዬ እና አዲሷ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የብልጽግና አባላት እንዳልሆኑ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአቶ ተመስገንን፣ የአምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የዶክተር መቅደስ ዳባ የትምህርት እና የሥራ ዝግኙነትን ዘርዝረው ለምክር ቤቱ ካቀረቡ በኋላ በሙሉ ድምጽ ተሹመዋል።
- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከብልጽግና አመራርነት ተሰናበቱ26 ጥር 2024
- የአቶ ደመቀ ስንብት እና የሁለት አስርታት ሚናቸው27 ጥር 2024

የደኅንነቱ ሰው ተመስገን ጥሩነህ አዲሱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር
አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመንግሥት ሥራ ውስጥ በቆዩባቸው በርካታ ዓመታት ውስጥ በአመዛኙ ያገለገሉት በወታደራዊ እና በደኅንነት ዘርፎች ውስጥ ነው።
በአገር መከላከያ ውስጥ ባገለገሉበት ጊዜ እስከ ሻለቃነት የደረሱ ሲሆን፣ በወታደራዊ ተቋሙ ውስጥ የመረጃ ክፍል ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ሰርተዋል።
በአማራ ክልል ጎጃም ደብረ ወርቅ ውስጥ ተወልደው ያደጉት አቶ ተመስገን በኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በአመራር እና አስተዳደር ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።
አቶ ተመስገን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በመሆን የአገሪቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከመሰረቱ አመራሮች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያላቸው ቅርርብ እና የሥራ ግንኙነት የተጠናከረው በዚህ ተቋም ውስጥ እንደሆነ ይነገራል።
በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ውስጥም በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች የሰሩ ሲሆን፣ በተቋሙ ውስጥ በሰሩባቸው ጊዜያት ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነት ባሉ ቁልፍ ቦታዎች ላይ አመራር ለመሆን ችለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ክልል ውስጥም በተለያዩ ተቋማት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የፀጥታ አማካሪነት እስከ ዞን አስተዳዳሪነት ባሉ የኃላፊነት ቦታዎችን ይዘው ሰርተዋል።
ከእነዚህም መካከል የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ምክትል እና ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር እና የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን መሥራታቸው የሚጠቀሱ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሆነው የሰሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ በአማራ ክልል የተከሰተውን የአመራሮች ግድያን ተከትሎ ወደ ክልሉ መመለሳቸው ይታወቃል።
በዚህም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመገደላቸው የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ሐምሌ 15/2011 ዓ.ም. አቶ ተመስገን ጥሩነህ በአማራ ክልል ምክር ቤት የክልሉን የመሪነት ሥልጣን እንዲይዙ ተሹመው ክልሉን በማረጋጋት ወሳኝ ሚና መጫወታቸው ይነገራል።
በክልሉ ርዕሰ መስተዳደርነት ከሁለት ዓመት ላነሰ ጊዜ የቆዩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በትግራይ የተካሄደው ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድንገት ባካሄዱት ሹመት በኅዳር 2013 ዓ.ም. የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው በመሾማቸው የአማራ ክልል ሥልጣናቸውን ለቀዋል።
አቶ ተመስገን በዋነኝነት ከያዟቸው የመንግሥት የሥልጣን ኃላፊነቶች በተጨማሪ በተለያዩ ወሳኝ ቦታዎች ላይም በመሾም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቁልፍ ሰው መሆናቸው ታይቷል።
ከእነዚህም መካከል በአገሪቱ ካሉ ግዙፍ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮቴሌኮም ሥራ አመራር የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ለተወሰነ ጊዜ መርተዋል።
ከዚያ በኋላም ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን የትግራይ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲፈረም ከህወሓት ጋር ለተደረገው ድርድር ከመንግሥት በኩል ከተሰየሙት ሰባት ተደራዳሪዎች መካከል አንዱ ነበሩ።
በተጨማሪም ካለፈው ዓመት መጨረሻ ገደማ ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ክልሉን በአራት ኮማንድ ፖስቶች በማዋቀር ሕግ የማስከበር ሥራ ያከናውናል የተባለውን ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ በመሆን እየሰሩ ነው።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ አቶ ደመቀ መኮንን በመተካት የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደመረጣቸው ይታወሳል።

ጉምቱው ዲፕሎማት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዚህ ዘመን በሥራ ላይ ከሚገኙ የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው ሙያተኛ ዲፕሎማቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ መሆናቸው ይነገራል።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በዲፕሎማቲክ መስክ አገራቸውን ያገለገሉት አምባሳደር ታዬ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በተለያዩ አገራት እንዲሁም በመንግሥታቱ ድርጅት በሙያቸው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
አምባሳደር ታዬ ከአገሪቱ ዋነኛ የትምህርት ተቋም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ከእንግሊዙ ላንካስተር ዩኒቨርስቲ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና በስትራተጂክ ጥናቶች አግኝተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሆነው በመሥራት ላይ የቆዩት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የተለያዩ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩት አምባሳደር ታዬ ከአሜሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አስከ ምክትል ሚኒስትርነት ድረስ አገልግለዋል።
ከዚያ ባሻገር ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ፣ ለሁለት ዓመት ደግሞ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ለዓመታት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ ባለችው ግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሠርተዋል።
ለረጅም ዓመታት በዲፕሎማትነት ባገለገሉባት አሜሪካ ውስጥ ከተባበሩት መንግሥታት በሻገር በሎስ አልጀለስ ዋና ቆንስላ፣ በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር እንዲሁም በስዊዲን ስቶክሆልም ውስጥ ደግሞ ቆንስላ ሆነው አገለልግለዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ አገራቸውን በመወከል የተሳተፉ የካበተ ልምድ ያዳበሩ ጉምቱ ዲፕሎማት ናቸው።
አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በተለይም ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ውዝግብ በገባችበት ጊዜ እንዲሁም በትግራዩ ጦርነት ወቅት ጉዳዩ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ሲቀርብ ከፊት ቀድመው የታዩ ዲፕሎማት ናቸው።
አምባሳደር ታዬ ለዓመታት በዋሽንግተን በኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በሎስ አንጀለስ በኢትዮጵያ ቆንስላ እና በኒው ዮርክ በተባበሩት መንግሥታት አገራቸውን በመወከል ከቆዩባት አሜሪካ የወጡት ባለፈው ዓመት ወደ አዲስ አበባ ሲዘዋወሩ ነበር።
አምባሳደር ታዬ ከጥር 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።