አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
የምስሉ መግለጫ,

8 የካቲት 2024, 14:22 EAT

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ።

አምባሳደር ሬድዋን የአገሪቱ የደኅንነት ተቋምን እንዲመሩ የተሾሙት በዛሬው ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑትን አቶ ተመስገን ጥሩነህን በመተካት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ጥር 30/ 2016 ዓ.ም ከአምባሳደር ሬድዋን በተጨማሪ ትዕግሥት ሐሚድን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አድርገው መሾማቸውን ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው መረጃ ያመለክታል።

በባለፉት ጥቂት ዓመታት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የትግራይን ጦርነት ለመቋጨት በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ በተካሄዱት ድርድሮች ላይ የፌደራሉ መንግሥት ዋነኛ ተደራዳሪ ነበሩ።

በተጨማሪም ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በታንዛንያ በተደረጉት ሁለት ዙር ድርድሮች ላይም መንግሥትን ወክለው መደራደራቸው ይታወቃል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታን ጨምሮ በባለፉት ዓመታት በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ የኃላፊነት ስፍራዎች ላይ አገልግለዋል።

ከደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ሲመለስም የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ለተወሰነ ጊዜ በአሥመራ ቆይተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን የኤርትራ አምባሳደር ከመሆናው በፊት በአየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንደነበሩ ይታወሳል።

በተጨማሪም የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር በመሆን ከማገልገላቸውም በላይ በሌሎች የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሠርተዋል።