የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ፉአድ ሁሴን
የምስሉ መግለጫ,የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ፉአድ ሁሴን

10 የካቲት 2024, 10:57 EAT

ኢራቅ በግዛቷ ላይ ከአሜሪካ ጦር እና በኢራን በሚደገፉ ሚሊሻዎች በሚፈጸምባት ጥቃቶች ምክንያት ወደ ግጭት ልትገባ እንደምትችል አስጠነቀቀች።

ሁለቱ ኃይሎች በሚያደርጓቸው ፉክክርም ግዛቷ ላይ ጥቃት እየተፈጸመ እንደሆነም የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ፉአድ ሁሴን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት በጣም ከፍተኛ ነው”

“ሁለቱም ወገኖች ጥቃታቸውን እንደሚያቆሙ ተስፋ አደርጋለሁ። በኢራቅ ምድር ችግራቸውን ሊፈቱ አይችሉም። ከፍተኛ ዋጋ ከፍለናል” ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት አሜሪካ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 17 በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ተገድለዋል። በመቀጠልም የሚሊሻ አዛዥ የሆኑት አቡ ባከር አል ሳዲ ላይ በኢራቋ መዲና ባግዳድ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ላይ በተፈጸመ የሚሳኤል ጥቃት የመኖሪያ ሰፈር ላይ ጉዳት ደርሷል።

ጥቃቱንም ሰላማዊ ዜጎችንም ሆነ ዓለም አቀፍ ሕግን ግምት ውስጥ ያላስገባ “በግልጽ የተፈጸመ ግድያ” ነው ስትል ኢራቅ የአጋሯን አሜሪካን ጥቃት አውግዛለች።

አሜሪካ እነዚህን ጥቃቶች የፈጸምኩት በዮርዳኖስ ውስጥ ለተገደሉት ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች አጸፋዊ ምላሽ እንደሆነም ነው የምትገልጸው። የአሜሪካ ጦር ሕዝቡን ለመጠበቅ “አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል” ብሏል።

በሁለቱ ወገኖች ፍልሚያ ኢራቅ እየነደደች ትገኛለች።

ሚኒስትሩ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በኢራቅ የተሰማሩትን 2 ሺህ 500 የአሜሪካ ወታደሮችን ማስወጣት ላይ ንግግር መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።

ወታደሮቹ በኢራቅ የሰፈሩት እስላማዊ መንግሥት እየተባለ የሚጠራው ቡድን ዳግም እንዳያንሰራራ ለማድረግም ነው ተብሏል። ወታደሮቹ በኢራቅ ከተፈለገው በላይ እንደቆዩም መንግሥታቸው እንዲሁም ሕዝቡ እንደሚያምንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

አብዛኛው የኢራቅ ሕዝብ በኢራቅ ምድር የውጭ ኃይሎች እንዲኖሩ እንደማይፈልጉም ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በግብዣ መሬታችን ላይ የመጡት ኃይሎች [አሜሪካውያን] በድርድር መውጣት አለባቸው። ያልተጋበዙትም ኃይሎች መውጣት አለባቸው። ይህም በድርድር እንደሚቋጭ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

በእሳቸው መንግሥት ያልተጋበዙ ያሏቸው ኃይሎች በኢራቅ ግዛት ላይ ባሉ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የሚፈጽሙ የኢራን ደጋፊ ሚሊሻዎች ናቸው። እነዚህ ሚሊሻዎች አብዛኛዎቹ የኢራቅ የጸጥታ ኃይሎች አካል መሆናቸው የሚነገር ሲሆን ተቺዎችም ለኢራን ፍላጎት ማስፈጸሚያ የቆሙ ወታደሮች ናቸው ይሏቸዋል።