
10 የካቲት 2024
ወ/ሮ ብርሃን መዝገበ* ለረጅም ዓመታት በመከላከያ ሠራዊት አባልነት ያገለገሉት ኮሎኔል ባለቤታቸው እና የልጆቻቸው አባት ኅዳር 12/2007 ዓ.ም. ተይዘው መታሰራቸውን ያስታውሳሉ።
ወ/ሮ ብርሃን ባለቤታቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲቀሰቀስ በቁጥጥር ስር ውለው በሽብርተኝነት መከሰሳቸውን ይናገራሉ።
“መጀመሪያ አሸባሪ ነህ፣ ባሕር ዳርን እና ጎንደርን ለማጥቃት ረድተሃል፣ ሰዎችን [ወደ ትግራይ] በመመልመል ወንጀለኛ ነህ” የሚል ክስ ቢቀርብባቸውም በቂ ምስክር ባለመቅረቡ ሌላ ክስ መቅረቡን ይናገራሉ።
ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም “በቅማንት እና በአማራ መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርገሃል. . .” የሚል አሳማኝ አይደለም የሚሉት ሌላ ክስ እንደተመሰረተባቸው ለቢቢሲ ትግርኛ ያስረዳሉ።
ባለቤታቸው እስካሁን ድረስ ለዓመታት አዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ እና እስካሁን ፍርድ እንዳልተሰጣቸው ጨምረው ተናግረዋል።
የኮሎኔሉ ደመወዝ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ከሦስት ዓመታት በላይ በመቋረጡ ከነ ልጆቻቸው ችግር ውስጥ መሆናቸውን፣ በተለይ ልጆቻቸው ለከፍተኛ የሥነ ልቦና ችግር እንደተጋለጡም ያስረዳል።
በእንዲህ ያለ ሁኔታ በእስር ላይ የሚገኙት የወ/ሮ ብርሃን ባለቤት ብቻ አይደሉም። ቢቢሲ ያነጋገራቸው በርካታ የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩ፣ ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው የትግራይ ተወላጆች በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ እና በሌሎችም አካባቢዎች ታስረው እንደሚገኙ ይናገራሉ።
እነዚህ የትግራይ ተወላጆች ከአምስት ዓመት እስከ እድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው እና በከባድ ወንጀል ከተፈረደባቸው ሲቪሎች ጋር ተደባልቀው በተለያዩ እስር ቤቶች እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።
እነዚህ የሠራዊት አባላት “በአጠቃላይ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ነን። ሕግ እና መብት ለእኛ ሲሆን አልሠራም” እንደሚሉም ቤተሰቦቻቸው ጨምረው ተናግረዋል።
በሁሉም ላይ የቀረበው ክስ “ሕገ መንግሥቱን ለማፍረስ መሞከር”፣ “አገርን መክዳት”፣ “የትግራይ ሠራዊትን መደገፍ’ እና ሌሎችም እንደሆኑ አክለው ተናግረዋል።
በአገሪቱ የተለያዩ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ እነዚህ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በበኩላቸው “አገር እያገለገልን ተከዳን” በማለት እንደሚያዝኑ ጨምረው ያስረዳሉ።
የፌደራል መንግሥት ጉዳያቸውን በሚገባ አለማየቱን፣ የህወሓት መሪዎች እና የትግራይ አስተዳደርም ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ተነጋግረው መፍትሔ ሊሰጧቸው እንዳልቻሉ በመናገር ቅሬታ ያቀርባሉ።
- የአመራር ቀውስ እንደገጠመው የሚገልጸው ህወሓት ለምን መሪዎቹን መቀየር አልቻለም?1 የካቲት 2024
- በትግራይ ህፃናት እና እናቶች በከፋ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው ተባለ8 የካቲት 2024
- የትግራይ አስተዳደር በአከራካሪ ቦታዎች ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ስምምነት ተደርሷል መባሉን አስተባበለ5 የካቲት 2024
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሌላ ግለሰብ፣ የኮሎኔል ማዕረግ ያለቸው ወንድማቸው በተመሳሳይ መንገድ እንደታሰሩባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በወንድማቸው ላይ የተመሠረተው መሰል ክስ ላይ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሊገኝ ባለመቻሉ፣ የሲቪል ፍርድ ቤት ከሰባት ወራት የእስር ጊዜ በኋላ ክሳቸው እንዲዘጋ መወሰኑን ተናግረዋል።
ነገር ግን ‘ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍርድ ቤት የሚታይ ይሆናል’ በሚል ሰበብ ሳይፈቱ ቀርተዋል፤ አንዳንዶቹ ወደ ጦላይ ሌሎች ደግሞ ወደ ታጠቅ ተወስደዋል ሲሉ የተፈጠረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
“ከዚያም ዳኛ፣ ጠበቃ እና ዐቃቤ ሕግ ከሠራዊቱ ተመድቦላቸው፣ በወታደራዊ ችሎት የዓመታት እስራት ተፈረደባቸው። ከዚያም ወደ ሲቪል እስር ቤቶች በትኗቸዋል። አንዳንዶቹን ወደ ቃሊቲ፣ አዲስ አበባ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ሸዋሮቢት፣ ሐዋሳ እና ሌሎች ቦታዎች ተወስደዋል። አሁንም እየተሰቃዩ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ እስረኞች ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“አዲስ አበባ አካባቢ ያሉት የተሻለ ዕድል አላቸው፤ ራቅ ባሉ ቦታዎች ያታሰሩትን ግን ማንም ቤተሰብ አይጠይቃቸውም። የት እንዳሉም በትክክል ስለማይታወቅ በሕይወት ስለመኖራቸውም በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም” ብለዋል።
ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሹ ጦርነትን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ያለመው የሰላም ስምምነት፣ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተፈረመ ከአንድ አመት ከሦስት ወር በላይ ሆኖታል።
ስምምነቱ ጦርነቱን ከመግታት ባለፈ፣ በእስር ላይ ለሚገኙት የትግራይ ተወላጆች የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት እና የፀጥታ ኃይል አባላትን ተስፋ የሰጠ ነበር።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከፍተኛ ባለማዕረግ ቤተሰቦች፣ ሰላም መውረዱ ታሳሪዎቹን “ነፃ እንደሚያወጣ” ጠብቀው እንደነበር ይናገራሉ።
ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ በህወሓት መሪዎች እና በትግራይ ሠራዊት ላይ የነበረው ክስ ተቋርጧል። ክሳቸው ያልተቋረጠ እስረኞች እንዲፈቱም አድርጓል። ነገር ግን ሌሎች በርካቶች እስር ቤት ሆነው ከአሁን አሁን እንፈታለን በማለት ቢጠብቁም ጉዳያቸውን የሚመለከት አለማግኘታቸውን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።
ኮሎኔል ወንድማቸው የታሳረባቸው ግለሰብ በበኩላቸው፣ የፌደራል መንግሥት ወንድማቸውን ጨምሮ ከ 5,000 የማያንሱ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት እና የፀጥታ አባላት የትግራይ ተወላጆች በመላ አገሪቱ ታስረው እንደሚገኙ መረጃ አንዳላቸው ይገልጻሉ።
ቢቢሲ በፌደራል እና በክልል ማረሚያ ቤቶች ምን ያህል የሠራዊቱ አባል የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ታስረው እንደሚገኙ ይፋዊ ቁጥር ማግኘት አልቻለም።
ጠበቃቸው ምን ይላሉ?
የሕግ ባለሙያው አቶ ሐብቶም ከሰተ ‘በማንነታችን ምክንያት ታስረን ተፈርዶብናል’ የሚሉትን የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ፣ ለመከታተል በፈቃደኝነት የሚሰሩ የሕግ ባለሙያዎችን ቡድን ያስተባብራሉ።
ጠበቃው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሁሉም ከሞላ ጎደል የተከሰሱት “በአገር ክህደት” ወንጀል እንደሆነ እና የወታደራዊ ችሎቱ ሂደት ፍትሃዊ እንዳልሆነ እንዲሁም ተከሳሾች የራሳቸው ጠበቃ እንዳያገኙ መከልከላቸውንም ይገልጻሉ።
መንግሥት በራሱ ተከላካይ ጠበቃ የመደበላቸውም ቢሆኑ፣ ጠበቆቻቸውን ለማግኘት ተከልክለው ጉዳያቸው መታየቱን አክለው ተናግረዋል።
ከፍርድ ሂደቱ በኋላም ‘ይግባኝ ለማለት’ ዕድሉን ያገኙት የተወሰኑትን ብቻ መሆኑን ተናግረው፣ የሞት ፍርዳቸው ወደ ዕድሜ ልክ እስራት የተቀየረላቸውም አሉ ብለዋል።
አቶ ሐብቶም እና ሌሎች ጠበቆች፣ ክሱን እና ችሎቱን “ፍትሃዊ ሆኖ” ስላላገኙት ነበር ይግባኙን ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት የወሰዱት።
ሂደቱን በተመለከተም ጉዳዩ ወደ ሰበር ሰሚ በሄደበት ጊዜ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዳልተፈረመ በማስታወስ፣ አንዳንዶቹ ውሳኔዎች በሰበር ችሎት ሲሻሩ፣ ሌሎች ደግሞ ለሰበር የሚቅርብ አይደለም በሚል ተመልሰዋል ብለዋል።
“ሌሎች ደግሞ ጉዳያቸው እንዲታይ መጠየቅ ሲጀምሩ፣ የመከላከያ ፍትህ ዳይሬክቶሬት የክሱን እና የፍርድ ውሳኔ ቅጂዎችን ሊሰጣቸው ፍቃደኛ አልነበረም” በማለት የገጠማቸውን ችግር ጠበቃው ተናግረዋል።
ከፍርድ ሂደቱ በኋላ የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ ቢደረግም፣ የዓመታት እና የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው የትግራይ ተወላጆች የመከላከያ ሠራዊት አባላት በየእስር ቤቱ ይገኛሉ።
“ጉዳያቸው ከትግራይ ጦርነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ከፕሪቶሪያ ስምምነት ጋር የተያያዘ ነው። ጥፋተኛ ስለተባሉ በፍትህ ስም በእስር ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት እና የክልሉ መንግሥት ተነጋግረው መፍታት ነበረባቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ውቅት ወደ ፍትህ አሠራሩ ተመልሶ የመሄድ ዕድል ዝቅተኛ ነው የሚሉት የጠበቆች ቡድን አስተባባሪው “አሁን ያለው ብቸኛ ዕድል በልዩ የምህረት አሰጣጥ ሂደት እንዲፈቱ ማድረግ ነው” ሲሉ ቀጣይ ሊሆን የሚችለውን ሂደት ያብራራሉ።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ለዚህ ጉዳይ ተብሎ የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ እና የፌደራል ሕግ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተስፋለም ይህደጎ ጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት አድርጓል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአገሪቱ በተለያዩ እስር ቤቶች በሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት የትግራይ ተወላጆች በእስር ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ተስፋለም፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት፣ ከፌዴራል መንግሥት፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር እና ከመከላከያ ሚኒስቴር ደጋግመን ተነጋግረንበታል” ብለዋል።
ይህንንም ግንኙነት ተከትሎ የተወሰኑት መፈታታቸውን አመልክተው “የተቀሩት በፌዴራል መንግሥት ምክንያት ጉዳያቸው ተጓቷል። በተለያዩ ሰበቦች ምክንያት ጉዳያቸውን ሊጨርሱልን አልቻሉም” ብለዋል።
ጉዳዩ ከክልሉ ቁጥጥር ውጪ መሆኑን በመጥቀስም፣ “ዋና መከራከሪያችን የተደረሰው ስምምነት እንጂ በእኛ እጅ ያለ ጉዳይ አይደለም። በፌደራል መንግሥቱ ሥልጣን ውስጥ የሚገኝ ነገር ነው” ከዚህ አንጻር ደግሞ ‘የተለየ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል’፣ ‘መከላከያ ጥፋተኛ ስላላቸው ራሱ ይፍታቸው’ እና የመሳሰሉትን ሰበቦች እንደሚቀርቡ አመልከተዋል።
በተጨማሪም በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ለታሳሪዎቹ የምህረት አሰጣጥ ሂደት ቢጀመርም በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይደረግ መቅረቱን አቶ ተስፋለም ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
“ለፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ሪፖርት አቅርበናል። ምክንያቱም ከፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ። ጉዳዩ የሁለቱም ወገኖች ስምምነት ቢሆንም፣ ወሳኙ አካል የፌደራል መንግሥት ነው።”
“በስምምነቱ መሠረት የእነዚህ እስረኞች ጉዳይ በፖለቲካው ውይይት ውስጥ መካተት ነበረበት። ስምምነቱ ሁለቱንም ወገኖች ይጠቅማል ተብሎ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ግን የቅሬታ አቅራቢ እና የቅሬታ ሰሚ ግንኙነት ነው ያለን። ስለዚህ ለንግግር ሲኬድ እንደ ተደራዳሪ ሳይሆን እንደ ቅሬታ አቅራቢ ነኝ” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።
ይህንን ጉዳይ ለመቋጨትም ፖለቲካዊ መፍትሄ ብቻ የሚያስፈልገው መሆኑን እና ይህንን ሊያደርግ የሚችለው በተለይ ማዕከላዊው መንግሥት መሆኑንም በአጽኖት ይናገራሉ።
ቢቢሲ የፍትህ ሚኒስቴርን እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ምላሽ በጉዳዩ ላይ ለማግኘት፣ በስልክም ሆነ በኢሜል ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
____
* ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል የተቀየረ