
10 የካቲት 2024, 11:12 EAT
በጋዛ እስረኞች እርቃናቸውን ሆነው፣ የፊጥኝ ታስረው እና ዐይናቸው ተሸፍኖ የሚያሳዩ በእስራኤል ወታደሮች የተቀረጹ እና በበይነ መረብ ላይ የተጫኑ ቪዲዮዎች ዓለም አቀፍ ሕግን ሊጥሱ እንደሚችሉ የሕግ ባለሙያዎች ተናገሩ።
ዓለም አቀፍ ሕግ እስረኞች ለውርደት እና ለሕዝብ ዕይታ መጋለጥ የለባቸውም ይላል።
ቢቢሲ ከአውሮፓውያኑ ሕዳር 2023 ጀምሮ በጋዛ በእስራኤል ወታደሮች ተቀርፀው በይፋ የተጋሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቪዲዮዎችን ተመልክቷል።
ከእነዚህ ቪዲዮዎች መካከል ስምንቱ እስረኞችን እንደሚያሳይ ማረጋገጥ ችሏል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል በሚል ከለያቸው ተጠባባቂ ወታደሮች መካከል አንዱን ከአገልግሎት ማገዱን የገለጸ ሲሆን እንደዚህ ያሉ ቪዲዮዎች እሴቶቼን አይወክሉም ብሏል።
ሆኖም ቢቢሲ በዚህ ላይ ተጨማሪ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
በተባበሩት መንግሥታት የዓለም አቀፍ ወንጀሎች ፍርድ ቤት ዋና አማካሪ የሆኑት ዶክተር ማርክ ኤሊስ እንዳሉት ቪዲዮዎቹ የጦር እስረኞች አያያዝን በተመለከተ የተደነገጉትን ሕጎች ሊጥሱ ይችላሉ።
- ፍልስጤምን የሚደግፉ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ያነሱት የረሃብ አድማ ሳምንት አለፈው10 የካቲት 2024
- የእስራኤል ደህንነት ማስፈራሪያዎች እየሰነዘሩባቸው እንደሆነ የደቡብ አፍሪካዋ ሚኒስትር ተናገሩ9 የካቲት 2024
- በጋዛ ያለው ጦርነት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሊስፋፋ ይችላል?4 የካቲት 2024
ወታደሮችን ማገልገል
ቢቢሲ የተመለከታቸው አብዛኛዎቹ ቪዲዮዎች ግጭቶችን እና ወታደሮች የጋዛ ነዋሪዎች ጥለዋቸው የወጡ መኖሪያ ቤቶችን ሲመለከቱ የሚያሳዩ ናቸው።
አንድ ቪዲዮ ወታደሮች የዳይኖሰር አምሳያ ልብስ ለብሰው መሳሪያ ሲተኩሱ የሚያሳይ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በአንድ ባዶ የፍልስጤማውያን ቤት ውስጥ ፒዛ ሲያዘጋጁ ያሳያሉ።
ሆኖም ቢቢሲ የሕግ ባለሙያዎች የፍልስጤማውያን እስረኞችን ያልተገባ አያያዝ ያሳያሉ ያሏቸውንና ተቀርፀው ለሕዝብ የተለቀቁ ስምንት ቪዲዮዎች አግኝቷል።
ስምንቱም ቪዲዮዎች የተጋሩት ማንነታቸውን ባልደበቁና ወታደሮች ሆነው በሚያገለግሉ ወይም ሲያገለግሉ በነበሩ ሰዎች ነው።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በስፋት የተጋራውንና አንድ ፍልስጤማዊ እስረኛን የሚያሳየውን ምስል በመተንተን ቢቢሲ ምስሉ የተጋራበትን ዋና ገጽ መለየት ችሏል።
‘ሪቨርስ ኢሜጅ ሰርች’ የተባለው የምስል ማረጋገጫ ዘዴን በመጠቀም የተደረገው ትንተና ምስሉ ዮሲ ጋምዙ ሊቶቫ ከተባለ እስራኤላዊ ወታደር የዩቲዩብ ገጽ የተገኘ መሆኑን አመልክቷል።
ወታደሩ ከታኅሳስ ወር መጀመሪያ ላይ አንስቶ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ናሃል ብርጌድ አካል የሆነው የግራናይት ሻለቃ 932 በሚል የለየውን ሠራዊቱን ምስል ጨምሮ በርካታ ቪዲዮዎችን በገጹ ላይ ጭኗል።
ታኅሳስ 24፣ 2023 በተጋራ ቪዲዮ ላይም አንድ ፍልስጤማዊ እስረኛ እርቃኑን ሆኖ፣ እጆቹ የፊጥኝ ታስረውና እየደማ በወንበር ላይ ተቀምጦ ሲመረመር ታይቷል።

ቢቢሲ ይህ ድርጊት የተፈፀመበትን ቦታ ለማወቅ ከወታደሩ የፌስቡክ ገጽ ጋር በማመሳከርና በተቋሙ መለያ አርማ በመታገዝ ምርመራ ያደረገ ሲሆን፣ በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ አካባቢ የሚገኝ ጋዛ ኮሌጅ እንደሆነ ለይቷል።
በዚሁ ቪዲዮ ላይ እስረኛው በባዶ እግሩ በጋዛ ጎዳናዎች ላይ ሲንቀሳቀስ ታይቷል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሰጠው መግለጫ ላይ ፎቶው የተወሰደው በመስክ ላይ በተካሄደ መጠይቅ ወቅት መሆኑን እና በተጠርጣሪው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ገልጿል። የወታደሩ ድርጊትም የእስራኤል ሕጎችን እና እሴቶችን የሚቃረኑ ናቸው ብሏል። በቅርቡም ወታደሩን ከአገልግሎት ለማገድ መወሰኑን ገልጿል።
ቪዲዮዎቹ ተነስተዋል
በተመሳሳይ ቀን እስራኤላዊው ወታደር ሌቶቫ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን እስረኞች በስፖርት ሜዳ ላይ ተሰብስበው የሚያሳይ ሌላ የዩቲዩብ ቪዲዮ ለቅቋል። ቦታው በጋዛ የሚገኘው ያርሙክ ስታዲየም እንደሆነም ቢቢሲ አረጋግጧል።
አብዛኞቹ እስረኞች የውስጥ ሱሪ ብቻ የለበሱ ናቸው። የተወሰኑት ደግሞ የእስራኤል ወታደሮች ዕይታ ሥር ሆነው ዐይናቸው ታስሮ በረድፍ በረድፍ ተደርድረው በጉልበታቸው ተንበርክከው ይታያሉ።
በቪዲዮው አንድ ቦታ ላይ ደግሞ ሦስት ሴት እስረኞች ያሉበት ቡድን ተንበርክከው እና ዐይናቸው ታስሮ የእስራኤል ሰንደቅ ዓላማ ከተሰቀለበት የእግር ኳስ ግብ ጀርባ ይታያሉ።

በዚህ ቪዲዮ ላይ የእስራኤል ወታደር ተደጋግሞ ይታያል እየተቀረፀ እንደሆነ የሚያውቅም ይመስላል።
ወታደሩ የለበሰውን የደንብ ልብስ እና አርማውን በይፋ ከሚታወቁ የእስራኤል መከላከያ ኃይል የደንብ ልብስ ጋር ቢቢሲ ያመሳከረ ሲሆን ግለሰቡ ሌተናንት ኮሎኔል ወይም የሻለቃ አዛዥነት ማዕረግ እንዳለው ማወቅ ችሏል።
ቢቢሲ ጉዳዩን አስመልክቶ ከእስራኤል መከላከያ ኃይል አስተያየት ከጠየቀ በኋላ ቪዲዮዎቹ ከሌቶቫ የዩቲዩብ ገጽ ላይ ወርደዋል።
የሥነ ምግባር ደንብ
ሌሎች ሁለት ቪዲዮዎች ደግሞ በሌላ የእስራኤል ወታደር ቲክቶክ ገጽ ላይ ተጭነዋል። እነዚህ ቪዲዮዎች ዐይናቸውን የታሰሩ እስረኞች እና መሳሪያ ታጥቆ የቆመ ወታደርን ምስል ያሳያሉ።
አንደኛው ታኅሳስ 14 የተለጠፈ ሲሆን በራፕ ሙዚቃ የታጀበው ቪዲዮው ዐይናቸውን የታሰሩ እስረኞች በፒክአፕ መኪና ውስጥ ታጭቀው፣ አንድ ወታደር አጠገባቸው ሆኖ አውራ ጣቱን ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ምስል ይዟል።
ከሌሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ጋር በማመሳከርም ይህ ወታደር ኢሊያ ብላንክ እንደሚባል ቢቢሲ ለይቷል።

ወታደሩ፣ ዐይኑ የታሰረ ግለሰብ ወለል ላይ ተቀምጦና እና በሦስት የእስራኤል ወታደሮች ተከቦ የሚያሳይ ምስል ያለበት ሁለተኛ ቪዲዮም አጋርቷል።
በቪዲዮው ላይ የተጠቀማቸው ፎቶዎች የተነሱት በሰሜን ጋዛ እንደሆነም መለየት ተችሏል።
ቢቢሲ የእስራኤል መከላከያ ኃይልን እና ቲክቶክን ስለይዘቶቹ ከጠየቀ በኋላ ቪዲዮዎቹ ተነስተዋል።
የጄኔቫ ስምምነት አንቀጽ 13 እስረኞች ሁል ጊዜም ሊጠበቁ ይገባል ይላል። በተለይ ከጥቃት፣ ከማስፈራሪያ እንዲሁም ከስድብ እና ለሕዝብ ከመጋለጥ ሊጠበቁ እንደሚገባ ያዛል።
ዶክተር ኤሊስ እንደሚሉት የጦር እስረኞችን ለሕዝብ አለማጋለጥ እና አለማንቋሸሽ ወይም አለማዋረድ የስምምነቱ ቁልፍ ጉዳይ ነው።
እስረኞችን በውስጥ ሱሪ ብቻ እርቃናቸውን እንዲሄዱ ማድረግ እና መቅረጽ ብሎም ማጋራት ዓለም አቀፍ የጦር እስረኞች ሕግን የሚጥስ ነው ብለዋል።
የተቀመጡት ድንጋጌዎች ይህን ዓይነት ድርጊት እንደማይፈቅዱም ዶ/ር ኤሊስ አስረግጠዋል።
የእስራኤልን የመከላከያ ኃይል የመጀመሪያውን የሥነ ምግባር ደንብ እንዲጻፍ የረዱት ፕሮፌሰር አሳ ካሽር በበኩላቸው እርቃናቸውን የሆኑ ሰዎችን ምስል ማጋራት የመከላከያ ኃይሉን የሥነ ምግባር ደንብ የሚጥስ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮፌሰሩ ጨምረውም እስረኞች መሣሪያ ታጥቀው ከሆነ ለመፈተሽ ልብሳቸውን የማስወለቅ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ገልጸው፤ ነገር ግን ፎቶ አንስቶ ለሕዝብ የሚጋራበት ምክንያት የለም ብለዋል።
“ በከፊል ራቁታቸውን እንዲሆኑ ያደረጉበት ምክንያትም ለማዋረድ ነው” ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
የሰብዓዊ መብቶች የሕግ ባለሙያ ማይክል ማንስፊልድም እነዚህ ምስሎች በተባበሩት መንግሥታት ፍርድ ቤት መታየት አለባቸው ብለዋል።
በግጭት እና በጦርነት ወቅት የጦር እስረኞች ከሆኑ ሰዎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ገደብ አለው ሲሉም እስረኞችን በአክብሮት መያዝ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ቢቢሲ ለቲክቶክ ስድስት ቪዲዮዎችን የላከ ሲሆን ቲክቶክ ስድስቱም የማኅበረሰባቸውን ደንብ እና መመሪያ የጣሱ መሆናቸውን ገልጿል።
መመሪያዎቹ ተጎጂዎችን ለማዋረድ የሚፈለግ ይዘት ተቀባይነት እንደሌለው ያስቀምጣሉ ብሏል።
በመሆኑም እነዚህን ቪዲዮዎች ከመተግበሪያው ላይ አጥፍቷል።
የዩቲዩብ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ዩቲዩብ በእስራኤልና በጋዛ መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ አንስቶ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ጎጂ ቪዲዮዎችን ማጥፋቱንና በሺዎች የሚቆጠሩ ገጾችን ማገዱን ገልጸዋል። ጎጂ የሆነ ይዘቶችን ለመቆጣጠር የይዘት ተቆጣጣሪ ባለሙያ ቡድኖቹ ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሆነም አክለዋል።