EthiopianReporter.com 

ዳዊት ታዬ

February 11, 2024

ሁሉም ባንኮች በ2016 ግማሽ የሒሳብ ዓመት ከ124.2 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውን ከ2.29 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሳቸው ታወቀ፡፡

የአገሪቱ ባንኮች የ2016 ግማሽ ዓመት አፈጻጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ባንኮች አሁንም ከሌላው የኢኮኖሚ ዘርፍ በተለየ ዕድገታቸው የቀጠለ መሆኑን ነው፡፡

የባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ በ2015 ግማሽ ዓመት ላይ 1.93 ትሪሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በ2015 መጨረሻ ላይም ተቀማጭ ገንዘባቸው 2.12 ትሪሊዮን ብር ነበር፡፡ ባንኮች በ2016 ግማሽ ዓመት ካሰባሰቡት አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 53.3 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሰባሰበው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2016 ግማሽ በጀት ዓመት ማሰባሰብ የቻለው አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ 66.7 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡   

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግማሽ ዓመቱ ካሰባሰበው 66.7 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 21 በመቶ አካባቢ የሚሆነው ደግሞ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰባሰበ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት (ሲቢኢ ኑር) በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ያሰባሰበው አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ 14.4 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡    

በሒሳብ ዓመቱ ግማሽ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የአገሪቱ ባንኮች የብድር ክምችት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ትሪሊዮን ብር በመሻገር 2.08 ትሪሊዮን ብር መድረስ መቻሉን ሪፖርተር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚህ አጠቃላይ የብድር ክምችት ውስጥ ወደ 1.07 ትሪሊዮን ብር የሚሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድርሻ ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላ የብድር ክምችቱ 51.8 በመቶ ድርሻ መያዙን የሚያመለክት ነው፡፡ የአገሪቱ ባንኮች ሰኔ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የነበራቸው አጠቃላይ የብድር ክምችት 1.95 ትሪሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2015 ግማሽ ዓመት ላይ ደግሞ የብድር ክምችታቸው 1.78 ትሪሊዮን ብር እንደነበር አይዘነጋም፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች በሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ ላይ አጠቃላይ ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ 208.3 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችና አገልግሎቱን በመስኮች ደረጃ እየሰጡ ያሉት ባንኮች በጥቅል ከደረሱበት የ208.3 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ብልጫ ያለውን ድርሻ አሁንም የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡

በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 104.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን የሚያመለክት ነው፡፡

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሁሉም አገልግሎቱን የሚሰጡ ባንኮች ፋይናንስ ያደረጉት (የሰጡት የብድር ክምችት) መጠን ደግሞ በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 85.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ከተሰጠው ብድር ውስጥ 29.8 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር በኩል የተሰጠ ነው፡፡ ባንኩ በ2016 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ብቻ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሰጠው ብድር መጠን 15.7 ቢሊዮን ብር መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡   

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አስቀማጮች ቁጥር እስከ 2016 መጨረሻ ድረስ ከ20.1 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ ቆጣቢዎች 6.6 ሚሊዮን መሆናቸው ታውቋል፡፡