EthiopianReporter.com 

ዜና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስንብትና የሚያገኟቸው ጥቅማ ጥቅሞች

ዮሐንስ አንበርብር

ቀን: February 11, 2024

በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ኢትዮጵያን ላለፉት 32 ዓመታት፣ ከዚህ ውስጥም ከአሥር ዓመታት በላይ የሚሆነውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት አቶ ደመቀ መኮንን፣ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ሐሙስ ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ተሰናብተው በምሥጋና ተሸኝተዋል። 

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስንብትና የሚያገኟቸው ጥቅማ ጥቅሞች | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ
አህመድ (ዶ/ር) ፓርላማ ሲገቡ

ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተኩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ሲሆኑ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃላፊነታቸው የተተኩት ደግሞ በውጭ ግንኙነት ዘርፍ ለረዥም ዓመታት አገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩት ታዬ አጽቀ ሥላሴ (አምባሳደር) ናቸው። 

ተተኪ ተሿሚዎቹን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹አቶ ደመቀ በብልፅግና ውስጥ ባለው የመተካካት አሠራር መሠረት ላሳደጉትና ለመሩት ሰው የፓርቲ ሥልጣናቸውን አስረክበዋል፡፡ ዛሬ ደግሞ በክብርና በፍቅር የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነታቸውን አስረክበው የተሸኙ ሲሆን፣ የተከበረው ምክር ቤት በኢፌዴሪ መንግሥት ስም ምሥጋና እንዲያቀርብልኝ እየጠይቃለሁ፤›› ብለዋል።

በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን መረካከብና አቶ ደመቀ ላገለገሉበት ምሥጋና ተችሯቸው መሰናበታቸው ተጨማሪ ክብር መሆኑን እያንዳንዱ ሰው ማወቅ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

‹‹ብዙ አሉባልታና ወሬ በውጭ ቢሰማም፣ ሁሉም ነገር በውይይትና በምምክር የመጣ መሆኑ ከግምት እንዲገባና ወደፊት እኛም መሰል ዕድል እንድናገኝ የምክር ቤት አባላት በየቤታቸው እንዲፀልዩልን እጠይቃለሁ፤›› ብለዋል። 

አቶ ደመቀ ላለፉት 12 ዓመታት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ ላለፉት 32 ዓመታት ደግሞ ኢትዮጵያን በተለያዩ ኃላፊነቶች ማገልገላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። 

አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎም ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለሰጡት አገልግሎት በራሳቸውና በምክር ቤቱ ስም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል። 

የተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጥቅማ ጥቅሞች

ከኃላፊነት የተነሱ የአገር መሪዎችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከኃላፊነት ከተሰናበቱ በኋላ ቀሪ ዘመናቸውን ከመንግሥት የሚያገኟቸው ጥቅማ ጥቅምች በ2002 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ ቁጥር 653 ተደንግጓል።

የአገር መሪ ማለት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው በአዋጁ የትርጓሜ ክፍል ተደንግጓል።

በመሆኑም አቶ ደመቀ ከኃላፊነት የተነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ መሆናቸው መጠን፣ በተጠቀሰው አዋጅ ላይ የተደነገጉትን ጥቅማ ጥቅሞች በሕይወት እሳካሉ ድረስ የሚያገኙ ይሆናል። በአዋጁ መሠረትም ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በቀጣዩ የሕይወት ዘመናቸው የሚከተሉትን ጥቅማ ጥቅሞች ከመንግሥት ያገኛሉ።

የግል ወጪና አበል

ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በኃላፊነት ላይ በነበሩበት ጊዜ ይከፈላቸው የነበረው የወር ደመወዝና አበል ከኃላፊነት ከተሰናበቱ በኋላም ሳይቋረጥ የሚቀጥል ሲሆን፣ መንግሥት በኃላፊነት ላይ ለሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የደመወዝና አበል ማስተካከያ ያደረገ እንደሆነም ለተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም (ለአቶ ደመቀ መኮንን) የግል ወጪና አበል ማስተካከያ እንደሚደረግ በአዋጅ ቁጥር 653 የተደነገገ በመሆኑ ይኼው መብት ይጠበቅላቸዋል።

የመኖሪያ ቤት አገልግሎት

በዚሁ አዋጅ መሠረት ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው መኖሪያነት የሚያገለግል ከአራት እስከ አምስት መኝታ ክፍሎች ያሉት መኖሪያ ቤት የሚያገኙ ሲሆን፣ የተሟላ የቤት ውስጥ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ደመወዝም በመንግሥት ወጪ ይሸፈንላቸዋል።

የተሽከርካሪ አገልግሎት

በተጨማሪም ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ደረጃቸውን የጠበቁ ሦስት ለመጓጓዣ የሚያገለግሉ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ይመደቡላቸዋል፡፡

የተሽከርካሪው ሹፌር ደመወዝ፣ የነዳጅና የጥገና፣ እንዲሁም ሌላ ወጪ በመንግሥት ይሸፈናል፡፡ እንዲሁም ለአቶ ደመቀና ለቤተሰቦቻቸው ጥበቃ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ጥበቃውን በሚያካሂደው ሪፐብሊካን ጋርድ (የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል) የሚመደብ ይሆናል።

የግል ደኅንነት ጥበቃ አገልግሎት

ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የግል ደኅንነት ጠባቂዎች በመንግሥት እንደሚመደብላቸውም የአዋጁ ድንጋጌ ያመለክታል። ጥበቃውን የሚያካሂደው የሪፐብሊካን ጋርድ (የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል) ሲሆን፣ ለአቶ ደመቀና ቤተሰቦቻቸው የሚመደበው የጥበቃ ኃይል መጠን ጥበቃውን በሚያካሂደው አካል የሚወሰን ይሆናል፡፡

የሕክምና አገልግሎት

በአዋጅ ቁጥር 653 ድንጋጌ መሠረት ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀና ቤተሰቦቻቸው በመንግሥት ወጪ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የተሟላ የሕክምና አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ የሕክምና አገልግሎቱ እንደ ሁኔታው በመንግሥት ወይም በግል የጤና ተቋም የሚሰጥ ሲሆን፣ ባለመብቱና ቤተሰቦቻቸው በአገር ውስጥ የጤና ተቋም ለሕክምና አገልግሎት የሚተኙ ከሆኑ አገልግሎቱን የሚያገኙት በአንደኛ ደረጃ ማዕረግ ይሆናል፡፡

የቢሮ የስልክና የፕሮቶኮል አገልግሎት

ከኃላፊነት የተሰናበቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ቀሪ ዘመናቸውን በተለያዩ ሕዝባዊ አገልግሎቶች በመሰማራት የሚያሳልፉ ከሆነ፣ መኖሪያ ቤታቸው በሚገኝበት ከተማ የቢሮ አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን፣ ራሳቸው መርጠው ለሚቀጥሯቸው አንድ ጸሐፊና አንድ ባለሙያ ደመወዝ በመንግሥት የሚሸፈን ይሆናል። 

በተጨማሪም ለቢሮ የሚያስፈልጉ ኮምፒዩተር፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ፖስታና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች መንግሥት ወጪያቸውን ሸፍኖ ያሟላል። ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቀሪ ዘመናቸውን የሚገለገሉበት የዲፕሎማቲክ ፓስፖርትና የቪአይፒ አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን፣ የቀድሞ ኃላፊነታቸውን የሚመጥን ሙሉ የፕሮቶኮል አገልግሎት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያገኛሉ።

መብቶችንና ጥቅሞቹ የሚቋርጡባቸው ሁኔታዎች

ከኃላፊነት የተነሱ የአገር መሪዎችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከኃላፊነት ከተሰናበቱ በኋላ ቀሪ ዘመናቸውን የሚያገኟቸው ጥቅማ ጥቅምች ሊቋረጥ የሚችልበት ሁኔታም በዚሁ አዋጅ ቁጥር 653 ተደንግጓል።

በዚህም መሠረት ተሰናባቹ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆኑ ሌሎች መሰል መብት የሚያገኙ የአገር መሪዎች መንግሥታዊ ሥርዓትን ለማፍረስ የሞከሩ እንደሆነ፣ የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ከተሳተፉ፣ የአገር ክህደት ወንጀል ከፈጸሙ፣ በኃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት ያገኟቸውን አገራዊ ጉዳዮች የሚመለከቱ ሚስጥራዊ መረጃዎች ካልጠበቁ፣ ወይም ሕገ መንግሥቱንና በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተቋቋሙትን ተቋማት ካላከበሩ የሚያገኟቸው ጥቅማ ጥቅሞች የሚቋረጡ ይሆናል።

ይሁን እንጂ እነዚህ መብቶችና ጥቅሞች ሊቋረጡ የሚችሉት ባለመብቱ የተላለፈው ድርጊት ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ቀርቦ የጥፋተኛነት ውሳኔ ከተሰጠና ይኼውም በኋላ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከተወሰነ በኋላ ነው።