
ለአሥር ዓመታት ያከራከረው ፋብሪካ
ዜና ፋብሪካው ከተሸጠ በኋላ የተገነባበት ቦታ ለአሥር ዓመታት ያከራከረው ጉዳይ የመጨረሻ ፍርድ አገኘ
ፋብሪካው ከተሸጠ በኋላ የተገነባበት ቦታ ለአሥር ዓመታት ያከራከረው ጉዳይ የመጨረሻ ፍርድ አገኘ
ቀን: February 11, 2024
- ፍርድ ቤቶች በቀረበላቸው ክስ ብቻ የሰጡት ፍርድ ለአስፈጻሚ ተቋማት ፈተና ሆኖ ከርሟል
- ጉዳዩ አንድ ዓይነት ቢሆንም ሰበር ችሎት ሁለት ጊዜ ፍርድ ሰጥቶበታል
ከአሥር ዓመታት በፊት ኅዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም. በተደረገ የሽያጭ ውልና ውሉን ተከትሎ ታኅሳስ 16 ቀን 2005 ዓ.ም. የአክሲዮን ድርሻና ስመ ሀብቱን ወደ ገዥዎች ለማዞር፣ መመሥረቻ ጽሑፍ ማሻሻያ ተደርጎ የተሸጠን ፋብሪካ፣ በመሻሻጡ ላይ ጥያቄ ባይነሳም፣ ሻጭ የተገነባበት ቦታ ወይም ፋብሪካው ያረፈበት ቦታ ‹‹የእኔ ነው›› በሚል በተፈጠረ ውዝግብ ለአሥር ዓመታት ሲያከራክር ከቆየ በኋላ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ከፈዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጠው፡፡
ላለፉት አሥር ዓመታት ከኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች እስከ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ድረስ ሲያከራክር የሰነበተው ፋብሪካ፣ ‹‹ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የሚባል ድርጅት ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ 01 ቀበሌ ውስጥ እንደሚገኝ የተገለጸው ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ድርጅት ጠቅላላ ስፋቱ 11,305 ካሬ ሜትር ስፋት ባለ ግቢ ውስጥ ሻጭ ለብቻው የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ (ካርታ) ባሠሩበት 3,015 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ 78 በመቶ በሚሆነው ላይ የተገነባ መሆኑን ክርክር የተደረገባቸው ሰነዶችና የመጨረሻ ፍርድ የተሰጠበት ሰነድ ያብራራሉ፡፡
ድርጅቱን (ፋብሪካውን) የገነቡት ጌታቸው እሸቱ (ኢንጂነር) እና ወ/ሮ ሐረግነሽ መኮንን የተባሉ ባለሀብቶች ሲሆኑ፣ ግዥውን የፈጸሙት ደግሞ በዕውቅቱ ታደሰ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ መሠረት በረደድ የተባሉ ባለሀብቶች መሆናቸውን የፍርድ ሰነዶቹ ይገልጻሉ፡፡
በሥር ፍርድ ቤቶች ክርክር የተደረገባቸውና ፍርድ የተሰጠባቸው ሰነዶች እንደሚያብራሩት፣ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ሻጮች ሲሆኑ እነ በውቀቱ (ዶ/ር) ገዥዎች ናቸው፡፡
ገዥና ሻጭ ኅዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ባደረጉት የሽያጭ የውል ስምምነት በ22,500,000 ብር ተገበያይተዋል፡፡ የሽያጭና የግዥ ውሉ የተፈጸመው የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔር ሕጎች ሒደትን በጠበቀ ሁኔታ መሆኑ በሰነዶች ሠፍሯል፡፡
ፋብሪካው የተገነባው እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በወሰዱት ብድር በመሆኑ፣ እነ በውቀቱ (ዶ/ር) ግዥውን የፈጸሙት፣ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ከልማት ባንክ ጋር የገቡትን የብድር ውል ግዴታ ለመፈጸም ተስማምተው ነው፡፡ ገዥና ሻጭ ውሉን ሲፈጽሙ በወቅቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያልተከፈለ ሰባት ሚሊዮን ብር መኖሩ ተረጋግጦና እነ በውቀቱ (ዶ/ር) ለመክፈል ተስማምተው መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
ገዥዎቹ ከጠቅላላ የሽያጭ ዋጋ 22,500,000 ብር ላይ ሰባት ሚሊዮን ብር ቀንሰው ቀሪውን 15,500,000 ለሻጮቹ እንዴትና እስከ መቼ መክፈል እንዳለባቸው በፈጽሙት የስምምነት ውል ላይ አሥፍረዋል፡፡
ገዥዎች ለሻጮች በቅድሚያ ሁለት ሚሊዮን ብር ሰጥተው ቀሪውን 13,500,000 ብር በአራት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ 3,375,000 ብር ለመክፈል ተስማምተው ውል መፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቶች የቀረቡት ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የግዥና የሽያጭ ስምምነት ውሎች በአግባቡ የተፈጸሙ ቢሆንም፣ ገዥዎች እነ በውቀቱ (ዶ/ር) በስምምነቱና በውሉ መሠረት የመጀመሪያውን ዓመት ክፍያ 3,375,000 ብር ለመክፈል ሻጮች እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) የፋብሪካውን ስመ ሀብት (የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ) በገዥዎች ስም እንዲያዘዋውሩላቸውና እንዲያስረክቧቸው ሲጠይቁ የክርክሩ መንስዔ የሆነው ችግር መፈጠሩን ሰነዶች ያብራራሉ፡፡
በፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም የመጨረሻው ፍርድ የተሰጠበት ሰነድ እንዳረጋገጠው፣ የስም ዝውውር እንዲፈጽሙ የተጠየቁት እነ ጌታቸው (ኢንጂነር)፣ ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ ግንባታ 78 በመቶ የሚሆነውን ግንባታ ያረፈበት 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ የይዞታው ማረጋገጫው ካርታ፣ በእነሱ ስም (በኢንጂነር ጌታቸው) ስለሆነ ገዥ (እነ ዶ/ር በውቀቱ) አይመለከታቸውም የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ሰነዶቹ ይገልጻሉ፡፡
እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ሽያጭ የፈጸሙት በጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የግል ማኅበር ስም የተዘጋጀውንና ስፋቱ 8,290 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታ ብቻ መሆኑን በመግለጽ፣ ከሽያጭ ውሉ ጋር ተመሳሳይነት የሌለው ምላሽ መስጠታቸውንም ሰነዶቹ ያብራራሉ፡፡
የሽያጭ ውሉ ሲፈጸም ገዥዎች እነ በውቀቱ (ዶ/ር) የሚያውቁት፣ ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማከፋፈያ ፋብሪካን መግዛታቸውንና በውል ሰነዱም ላይ ሠፍሮ የሚገኘው 11,305 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታና አንድ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሆኑን እንጂ፣ 3,015 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ በእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ስም ካርታ ያለውና ቀሪው 8,290 ካሬ ሜትር በጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም ስለመሆኑ እንደማያውቁ ክርክር ያደረጉባቸው ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን የግዥ ስምምነት ያደረጉበት ወይም የገዙት ፋብሪካ 78 በመቶ የሆነው ግንበታው በ3,015 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈና በሽያጭ ውል ሰነዱ ላይም ሠፍሮ የሚገኘው ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማከፋፈያ ፋብሪካ መሆኑን የክርክር ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡
በገዥና በሻጭ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ወደ ኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች አምርቶ፣ የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የሽያጭ ውሉንና ሌሎች ማስረጃዎችን መርምሮ፣ የሻጮችን (እነ ጌታቸው ኢንጂነር) ክርክር ውድቅ በማድረግ፣ ለገዥዎች (ለእነ በውቀቱ (ዶ/ር)) ፍርድ የሰጠ ቢሆንም፣ ሻጭ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን በመግለጽ ጉዳዩን ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በማቅረብ፣ የክልሉ ፍርድ ቤት የሰጠውን ፍርድ ማሻራቸውን ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የክልል ፍርድ ቤትንና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ፍርድ የሻረው፣ ሻጮች ውል እንዲፈርስ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡትን ክስ ውድቅ አድርጎ፣ የሽያጭ ውሉንና አክሲዮኑን ለማስተላለፍ የተሻሻለበትን ቃለ ጉባዔ ካፀደቀ በኋላ፣ የቦታ ስፋቱ 3,015 ካሬ ሜትር የሆነው ይዞታ የእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) መሆኑን ብቻ በመግለጽ መሆኑን የክርክር ሰነዶቹ ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ፋብሪካ ግንባታ 78 በመቶ ያረፈው በ3,015 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ስለመሆኑ ያለው ነገር አለመኖሩንም ሰነዶቹ ያብራራሉ፡፡
በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር የተሰኙት እነ በውቀቱ (ዶ/ር)፣ ‹‹መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ተፈጽሟል፤›› በማለት ለፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት የአቤቱታ ማመልከቻ ቢያቀርቡም፣ ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በማፅደቅ አቤቱታቸውን ውድቅ ማድረጉንም ፍርድ ሰነዶቹ ያብራራሉ፡፡፡ በችሎቱ ውሳኔ የተበሳጨት በውቀቱ (ዶ/ር) በችሎት በተሰየሙ ዳኞች ላይ ተቃውመው በማሰማታቸውና ችሎት በመድፈር ወንጀል ከእነ ቤተሰቦቻቸው፣ እስከ ስድስት ወራት የሚደርስ የእስራት ቅጣት እንደተጣለባቸውም የፍርድ ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡
ምንም እንኳን በፋብሪካው ሽያጭ የተፈጠረው ውዝግብ ከኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች እስከ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሰበር ሰሚ ችሎት ደርሶ የመጨረሻ ፍርድ ያገኘ ቢሆንም፣ ፍርዱን ማስፈጸም ባለመቻሉ ጉዳዩ እንደገና ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ችሎት ሊመለስ መቻሉን የክርክር ሰነዶች ያብራራሉ፡፡
በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማለትም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 155684 መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በከፊል የተሰጠው ውሳኔን በሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 166294 ሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. የፀናውን ውሳኔ፣ የኦሮሚያ ክልል የቢሾፍቱ ከተማ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽሕፈት ቤት፣ በፍርድ ቤቶቹ ፍርድ መሠረት ሊያስፈፅምላቸው አለመቻሉን በማብራራት፣ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት፣ ከላይ በተጠቀሱት ውሳኔዎች መሠረት ፋብሪካው 78 በመቶ ያረፈበትን ቦታ ጭምር በጠቅላላ 30.15 ካሬ ሜትር ቦታና በእነ ዕውቀቱ (ዶ/ር) እንዲያስረክቧቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው እነ ጌታቸው (ኢንጂነር)፣ አምስት ዳኞች ለሚያሰሙበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ማቅረባቸውን የፍርድ ሰነዶቹ ያብራራል፡፡
ለችሎቱ ተጠሪ የሆኑት እነ በውቀቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ፣ የቢሾፍቱ ከተማ መሬት አስተደደርና አጠቃቀም ጽሕፈት ቤት በፍርዱ መሠረት ለማስረከብ ባደረገው ጥናት፣ እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ሁለት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ስም የቦታው ስፋት 3,015 ካሬ ሜትር የሆነና ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበር ስም ሌላ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱን እንዳረጋገጠ ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም ፋብሪካው በስሙ በተሰጠው 8,290 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ መገንባት ሲገባው፣ የግንባታው 78 በመቶ ያረፈው በጌታቸው (ኢንጂነር) ስም ባለው 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በመሆኑና የሽያጭ ውሉ ደግሞ እንዳይፈርስ በሁሉም ፍርድ ቤቶች የፀና ፍርድ ተሰጥቶ ባለበት ሁኔታ ፍርዱን ማስፈጸም እንደማይቻል ገልጿል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለፍርድ ቤት በሰጠው አስተያየት መሠረት፣ ፍርዱን ማስፈም የሚችለው ፋብሪካው ከተገነባበት ቦታ ውጪ ያለውን ክፍት ቦታ በማሸጋሸግና በፍርዱ የተቀመጠው የቦታ ስፋት ለእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) በመስጠት በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠበትን ውሳኔ ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲያፀናው በመጠየቅ ምላሽ መስጠታቸውን ሰነዶቹ ይገልጻሉ፡፡
የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ከተሰየሙት አምስት ዳኞች አንዱ በፍርድ ሲለዩ አራት ዳኞች በአብላጫ ድምፅ የሰጡት ባለ ዘጠኝ ገጽ ፍርድ ትንታኔ የሚጀመረው ስለፍርድ አፈጻጸም ስለሚደነግገው የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ጽንሰ ሐሳብ በማስረዳት ነው፡፡ በሥነ ሥርዓት ሕጉ ሰባተኛ መጽሐፍ ተደንግጎ እንደሚገኘው፣ የተፈረደለት ሰው የፍርድ አፈጻጸም ሲጠይቅ፣ ፍርዱን የሚያስፈጽመው ፍርድ ቤት እንዲፈጽም የተጠየቀውን ፍርድ መሠረት በማድረግና በድንጋጌዎቹ የተረጋገጠውን ሥርዓት ተከትሎ መሆን እንዳለበት በአብላጫ ድምፅ ፍርድ የሰጡት ዳኞች በፍርዱ ላይ አሥፍረዋል፡፡ የፍርድ አፈጻጸም ግብ ሥነ ሥርዓቱን በመከተል ፍርዱን ተግባራዊ ማድረግ ወይም በተግባር መተርጎም መሆኑንም አክለዋል፡፡ ለፍርድ አስፈጻሚ የሚሰጠው ትዕዛዝም ፍርዱን ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑንና የተወሰነላቸው ሰዎች፣ የተወሰነላቸውን ነገር እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ትዕዛዝ መሆኑን፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 378 እና 392 (1) ድንጋጌ መሠረት መሆን እንዳለበት የተሰጠው የመጨረሻ ፍርድ ያብራራል፡፡ በሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 368 እና 392 (2) ድንጋጌ መሠረት፣ የፍርድ ውሳኔ የሚያስፈጽመው ፍርድ ቤት፣ የፍርድ ውሳኔውን ይዘት አድማስ ባገናዘበ መልኩ፣ ስለፍርዱ አፈጻጸም ተስማሚ በሆነ መልኩ በመለየት ፍርዱን የማስፈጸም ሥልጣን ያለው መሆኑንም በፍርዱ ተተንትኗል፡፡ አስፈጻሚው ፍርድ ቤት የፍርድ ባለዕዳው በሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 392(2) ድንጋጌ መሠረት፣ በማንኛውም ምክንያት ቢሆን ፍርዱን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም የማይችል መሆኑን ከተረዳ፣ ፍርዱ ሳይፈጸም እንዲቆይ ትዕዛዝ መስጠት እንደሚችልም ችሎቱ በፍርዱ አመልክቷል፡፡
ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ የሥር ፍርድ ቤት (ከፍተኛው ፍርድ ቤት) የሰጠውን ውሳኔ በማሻሻል፣ በእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ስም በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘውና 78 በመቶ የፋብሪካው ግንባታ ያረፈበት 3,015 ካሬ ሜትር ቦታና በላዩ ላይ የሚገኘው ንብረት የእነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ነው ብሎ ፍርድ መስጠቱ ተገቢ አለመሆኑን ፍርዱ ያብራራል፡፡
ከላይ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች አንፃር ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻና ማሸጊያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲሸጥ ሻጭና ገዥ ያደረጉት የሽያጭ ውል ሊፈርስ አይገባም በሚል በሥር ፍርድ ቤቶች ተወስኖ ውሳኔው ፀንቷል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ ያረፈበት አብዛኛው ክፍል በ3,015 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መሆኑም በተረጋግጧል፡፡ እንዲሁም እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) እንደሚሉት በፋብሪካው ስም በተሰጠው ይዞታ ላይ የተገነባው ራሱን የቻለ ሌላ ፋብሪካ ሳይሆን፣ በሽያጭ ያስተላልፉት 78 በመቶ የሆነው ግንባታ ያረፈበት 3,015 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻ፣ መሸጫና ማከፋፈያ ፋብሪካ አካል የሆነ ግንባታ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ፋብሪካ በቦታው ላይ አለመኖሩን የሥር ፍርድ ቤቶች ባደረጉት ማጠራት ተረጋግጧል፡፡ እንዲሁም የፋብሪካውን የሽያጭ ውል አፈጻጸም ውጤት አልባ በሚያደርግ መልኩ፣ ‹‹የፋብሪካውን አካል ጭምር እንድንረከብ የአፈጻጸም ትዕዛዝ ሊሰጥ ይገባ ነበር›› በሚል እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ያቀረቡት መከራከሪያ፣ የዋናውን ውሳኔ ይዘትና መንፈስ ያልተከተለ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም ሲሉ አራት ዳኞች ፍርድ መስጠታቸውን የፍርድ ሰነዱ ያስረዳሉ፡፡
በአጠቃላይ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ለእነ በውቀቱ (ዶ/ር) በሽያጭ ያስተላለፉትን ጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻ፣ መሸጫና ማከፋፈያ ፋብሪካ፣ ምንም እንኳን የፋብሪካው ካርታ ላይ ያለው የይዞታ ስፋት 8,290 ካሬ ሜትር መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፣ በተጨባጭ የፋብሪካው ሙሉ ግንባታ ያረፈው በሽያጭ ውሉ ላይ በተጠቀሰውና 78 በመቶ ግንባታው ባረፈበት በ3015 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መሆኑን በማረጋገጥ፣ የቢሾፍቱ መሬት አስተዳደር ሁለት ሙያዊ አማራጮችን በማስቀመጥ ፍርዱን ማስፈጸም እንደሚቻል ማብራሪያ መላኩን ችሎቱ ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም የላከለትን ማብራሪያ መሠረት በማድረግና የፍርዱን መንፈስ በመከተል፣ ከአንደኛው ይዞታ ወደ ሌላኛው ይዞታ ገብቶ የተገነባው የፋብሪካው አካል እንዲፈርስ በማድረግ ማስፈጸሙ፣ ከዋናው ፍርድ መንፈስ መራቅ ነው›› በማለት ሁለተኛውን አማራጭ ወስዶ፣ ስፋቱ 3,015 ካሬ ሜትር በሆነው የጌት እሸት ዲተርጀንት ማምረቻ፣ መሸጫና ማከፋፈያ ፋብሪካ ያረፈበትን ለማካካስ፣ ግንባታ ካልተፈጸመበት ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ስፋቱ 8,290 ካሬ ሜትር ከሆነው ክፍት ቦታ ላይ በማሸጋሸግ ፍርዱን እንዲያስፈጽምና በአፈጻጸም ሒደት ካርታ ማስተካከል የሚያስገድድ ከሆነ ካርታውን እንዲያስተካክል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝም ቅር በመሰኘት እነ ጌታቸው (ኢንጂነር) ያቀረቡትን ይግባኝ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሠረዝ የሰጠው ትዕዛዝ፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 392 (1) ሥር በተዘረጋው ሥነ ሥርዓት መሠረት መሆኑ ተገልጿል፡፡ በተቻለ መጠን የፍርድ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግም የሚያስችል ተስማሚ መንገድ በመከተል፣ ፍርዱን ማስፈጸማቸውን የሚያሳይ እንጂ፣ ከዋናው ፍርድ ውሳኔ ውጪ የሆነ የፍርድ አፈጻጸም ትዕዛዝ ሰጥተዋል የሚያሰኝ ባለመሆኑ፣ የተፈጸመ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለመኖሩን በፍርዱ አረጋግጦ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 212760 መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. የሰጠው የአፈጻጸም ትዕዛዝና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 245822 ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. የተሰጠውን ትዕዛዝ፣ በሰበር ሥነ ሥርዓት መመርያ ቁጥር 17/2015 አንቀጽ 9(1/ሀ) መሠረት በአብላጫ ድምፅ በማፅናት የመጨረሻ ፍርድ ሰጥቷል፡፡