EthiopianReporter.com 


ዜና
የትግራይ ክልል 52 በመቶ የእርሻ መሬቱ በአማራና በኤርትራ ኃይሎች መያዙን አስታወቀ

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: February 11, 2024

የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ የክልሉ 52 በመቶ የእርሻ መሬት በአማራና በኤርትራ ሠራዊት ኃይሎች በመያዙ ምክንያት የታቀደውን ያህል ምርት ማምረት አለመቻሉን አስታወቀ፡፡

የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓለም ብርሃን ሀሪፈዮ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት የፕሪቶሪያ ስምምነቱን ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ ባለማድረጉ፣ በክልሉ ከፍተኛ ምርት የሚያስገኙ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በኤርትራ ኃይሎች ተይዘዋል፡፡

በ2016 ግማሽ በጀት ዓመት ውስጥ 15 ሚሊዮል ኩንታል እህል ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ አምስት ሚሊዮን ብቻ ወይም 37 በመቶ ያህል ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ በአጠቃላይ 1.3 ሚሊዮን ሔክታር የሚታረስ መሬት እንዳለ፣ ከዚህ ውስጥም 640 ሺሕ ሔክታር መሬት በማረስ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ወይም 37 በመቶ እህል መገኘቱን አክለው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የክልሉ 52 በመቶ የእርሻ መሬት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እጅ ሥር እንደሌለ ያስታወሱት ኃላፊው፣ ክልሉም ከጦርነቱ ጉዳት በፍጥነት መልሶ ማገገም ባለመቻሉ፣ የግብርና ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ አሁን ያለው የእርሻ መሬት 48 በመቶው ብቻ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በክልሉም ድርቅ፣ ረሃብና ጦርነት በመከሰቱ በርካታ ሰዎች ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አብራርተዋል፡፡

በተለይ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ አብዛኛዎቹ የክልሉ ነዋሪዎች ለእርሻ የሚገለገሉባቸው ከብቶቻቸውም ስለሞቱባቸውና ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች ስለወደሙባቸው፣ በአሁኑ ጊዜ እያረሱ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ክልሉ እንደ ጥሩ ጎን የሚያነሳው አሁን ያለውን የሰላም  ጭላንጭል በመጠቀም በመስኖ ልማት፣ እንዲሁም ለግብርና የሚሆኑ ግብዓቶችን ለአርሶ አደሮች በማቅረብ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ነው ገልጸዋል፡፡

ከሁሉ በላይ ውኃ ያለባቸው አካባቢዎችን በመለየት ማኅረበሰቡን የመስኖ ልማት ተጠቃሚ በማድረግ፣ የግብርና ዘርፉ እንዳይጎዳ ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

በተለይ በምዕራብ፣ በደቡብና በሰሜን ትግራይ አካባቢዎች ከፍተኛ ችግር እንዳለ በመጥቀስ፣ በኤርትራ ድንበር የሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በኤርትራ ኃይሎች ሥር በመውደቃቸው የግብርና ዘርፉ መጎዳቱን ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመከሰቱ በማዕከላዊና በሰሜን ምዕራብ ዞኖች ለምርት ደርሶ የነበረ ጤፍ ሙሉ ለሙሉ መበላሸቱን ያስታወሱት ኃላፊው፣ በክልሉ እንዲህ ዓይነት ችግር በተደጋጋሚ መከሰቱን አስረድተዋል፡፡

ክልሉ ያለበትን ችግር በመረዳት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግለት ለፌዴራል መንግሥት በተደጋጋሚ ጥያቄ መቅረቡን ገልጸው፣ ክልሉ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ የፌዴራል ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎች በአካል በመምጣት አይተዋል ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል በዋናነት የሚመረቱ የእርሻ ምርቶች ጤፍ፣ ስንዴ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ በቀጣይ የፌዴራል መንግሥት ለክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል በሚገኙ 27 ወረዳዎችና 107 ቀበሌዎች ውስጥ በርካታ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን፣ ብዙዎቹም ለከፍተኛ ድርቅ እየተጋለጡ መሆናቸው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡