
February 11, 2024

አሥረኛው አገር አቀፍና ሦስተኛው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲፖዚየም በተካሄደበት ወቅት
ከአራት መቶ በላይ ዩኒየኖች፣ ከመቶ ሺሕ በላይ መሠረታዊ ማኅበራትና አምስት የኅብረት ሥራ ክልላዊ ፌዴሬሽኖች ቢኖሩም፣ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ በመሆኑ በሚፈለገው ልክ ውጤት ማስመዝገብ እንዳልቻሉ፣ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሚና ከገበያ በላይ ነው›› በሚል መሪ ቃል ጥር 29 ቀን 2016 ዓ.ም. አሥረኛው አገር አቀፍና ሦስተኛው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲፖዚየም በተካሄደበት ወቅት፣ ምክትል ኮሚሽነር አብዲ ሙመድ ለሪፖርተር እንደተናገሩት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከፍተኛ የአባላት ቁጥርና ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ቢኖራቸውም፣ ገበያን ከማረጋጋት አኳያ በሚፈለገው ልክ ውጤት እያስመዘገቡ አይደለም ብለዋል፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ሰጪነት በስፋት አንደሚሳተፉ የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ በሚፈለገው መጠን ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሠራቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ተወዳዳሪ መሆን አልተቻለም በማለት ችግሩን አስረድተዋል፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ዋነኛ ችግር በተማረ የሰው ኃይል አለመመራታቸው እንደሆነ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር አብዲ፣ የአደረጃጀት፣ የአሠራርና የገንዘብ እጥረት፣ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ችግሮች ማነቆ እንደሆኑባቸው ተናግረዋል፡፤
‹‹በቁጥር ትንሽ በተፅዕኖ ትልቅ›› የሆኑ የኅብረት ሥራ ማኅበራት መኖር አለባቸው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ከነበረው አደረጃጀት መውጣት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ ሥራ ላይ የተሰማሩ ማኅበራትን በማዋሀድ የአባላትና የካፒታል መጠናቸውን ከፍ በማድረግ፣ በተማሩ ሰዎች መመራት አለባቸው ሲሉ አክለዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ፊቱን ወደ ሸማቾች ማኀበራት ቢያዞርም በተለይ የጤፍ ምርት ባለመኖሩ መቸገሩን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሸማቾች ማኅበር ተወካይ ገልጸዋል፡፡
‹‹ቀደም ሲል የግብርና ሚኒስቴር የገበያ ትስስር ለመፍጠር በሚል በርካታ ገንዘብ መመደቡን በሚዲያ ጭምር ያስታወቀ ቢሆንም፣ ገንዘቡ ባለመቅረቡ ኅብረተሰቡ ገንዘቡ የት ገባ በማለት እየጠየቀን ነው፤›› ሲሉ ተወካይዋ ተናግረዋል፡፡
‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበራት የፓርቲ ሳይሆኑ የግሉ ዘርፍ አባል መሆን አለባቸው፤›› ያሉት የኢኮኖሚ አማካሪው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ናቸው፡፡
መንግሥት ሌላውን ዘርፍ እንደሚደግፍና እንደሚያደራጅ ሁሉ፣ ለኅብረት ሥራ ማኅበራትም የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ ደምስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
መንግሥት የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በትክከል ከተጠቀመባቸው እየታየ ያለውን የዋጋ ግሽበትና የሥራ አጥነት ችግር በቀላሉ ለመፍታት ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የተጠናከሩ ማኅበራት ካሉ ከምርት እስከ ፍጆታ ባለው ሥርዓት መግባታ ይችላሉ ያሉት የኢኮኖሚ አማካሪው፣ ግብይትና ቁጠባ ላይ ብቻ ሳይሆን ከምርት ጀምሮ ከተሳተፉ ንግድ ተኮር የሆኑ ምርቶችን ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በአደራጅ አካላትም ሆነ በፖሊሲ አውጭዎች ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆንና ኋላቀር የአደረጃጀት አካሄድን መከተል፣ ለዘርፉ ማደግ እንቅፋቶች መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ፣ የኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው መለሰ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ዓለም አቀፋዊ ግብይቶችን ጨምሮ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን የሚመሩ አርሶ አደሮች በመሆናቸው፣ ካላቸው ዕውቀት አኳያ የአመራር አባላት በተማረ ኃይል ሊተኩ ይገባል ሲሉ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡