EthiopianReporter.com 

FEBRUARY 11, 2024

ናታን ዳዊት

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ከልክ በላይ እየሆነ ነው፡፡ ፍላጎቱን የሚመጥን አቅርቦት የለም፡፡፡ እያደገ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ችግርና በየዓመቱ እየተደራረበ የሚመጣውን ፍላጎት ከግንዛቤ ያስገባ በትክክል የተቀረፀ ዕቅድና ፖሊሲ አለ ለማለትም ያስቸግራል፡፡ የከተማዋ የመኖሪያ ቤት ችግርን ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክትም እንደ አጀማመሩ ሊቀጥል አለመቻሉ ቤት ፈላጊዎችን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው፣ የቤት ኪራይ ዋጋንም እያናረው ሄዷል፡፡ 

ሌላው ቀርቶ የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን ተመዝግበው ሲቆጥቡ የነበሩ ዜጎች በስማቸው ‹‹ሲገነቡ›› የነበሩ ቤቶቻቸውን ያለማግኘታቸው በራሱ እንደ መንግሥት ግንባታ ላይ የነበሩ ቤቶችን ለማስተላለፍ እንኳን መቸገሩን ያመላክታል፡፡

በ1997 ዓ.ም. እና ከዚያም በኋላ በነበረ ምዝገባ ከሚጠናቀቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የማግኘት መብታቸውን እንዳጡ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቢቆም እንኳ መንግሥትን አምነው ቤት ለማግኘት ሲቆጥቡ የነበሩ ዜጎች በሙሉ ቤት የማግኘት መብታቸው ሊከበር ይገባ ነበር፡፡

ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ ሲከሰቱ የነበሩ ችግሮች አንደኛው መገለጫው በርካታ ቢሆንም፣ ነባር ተመዝጋቢዎችን ወደ ጎን ብሎ ለሌሎች እንዲተላለፉ መደረጉ አንድ ማሳያ ነው፡፡ 

ዛሬ የፍትሕ ያለህ የሚሉ የቀድሞ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎችን በአግባቡ ቋጭቶ ወደ ሌላ ምዕራፍ መሸጋገር ሲገባ፣ ይህ ያለመደረጉ በራሱ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፖሊሲና አስተዳደር የለም ብለን የምንሞግተውና የምንጠይቀው እንዲህ ያሉ ችግሮችንም ይዘን በመጓዛችን ነው፡፡  ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ በከተማችን ውስጥ ያለውን እጅግ የበዛ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመሙላት አስተዳደሩ ከቀድሞው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት የተሻለ አሠራር እንዲዘረጋ ሲጠበቅበት ይህንን ሊያደርግ አልቻለም፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ ያስችላሉ የሚባሉ በጥናት ላይ የተመሠረቱ የመፍትሔ ሐሳቦች በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርቡ ቢሆንም፣ ይህንን በአግባቡ መጠቀም እየተቻለ ባለመሆኑ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዴት ሊፈታ እንደተፈለገ ግራ እያጋባ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ በራሱ በከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ችግሮችን ይቀርፋሉ ብሎ በአደባባይ ይፋ ያደረጋቸው የመፍትሔ ሐሳቦችና የግንባታ ስምምነቶች አየር ላይ ተንጠልጥለው ቀርተዋል፡፡ 

አሁን ባለው በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታና ከተማ ውስጥ አለ ከሚባለው የመሬት አቅርቦት ችግር አንፃር፣ ብዙዎችን ለማድረስ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በቀዳሚነት የሚቀመጥ አማራጭ ነው፡፡ ይህንን የተሻለ አማራጭ መንግሥት ለምን እንዳቆመው በራሱ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በእርግጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቀድሞ በነበረው አሠራር ላለመቀጠሉ ዋነኛ ምክንያት ከፋይናንስ እጥረት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይሰማል፡፡ አስተዳደሩ ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ብሎ የተበደረውን 50 ቢሊዮን ብር ብድር ከፍሎ ሊጨርስ አለመቻሉ እንደሆነም ሲገልጹ ሰምተናል፡፡

ነገር ግን ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ያልተቻለው ፕሮጀክቱን ከጅምሩ በአግባቡ ማስተዳደር ባለመቻሉ ጭምር ነው፡፡ ፕሮጀክቱን በቶሎ አስገንብቶ ለማስጨረስ ያለመቻሉ የግንባታ ዋጋን በማናሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አዋጭ አይደሉም እንዲባል አስገድዷል፡፡ ለተጠቃሚዎች ይተላለፉበት የነበረው በመንገድ ውስብስብ ችግሮችና የአሠራር ሒደቱም ደካማ መሆናቸው እንጂ ፕሮጀክቱ አዋጭና ቀዳሚ ምርጫ እንደነበር በግልጽ መናገር ያስፈልጋል፡፡ 

ስለዚህ በብዙ መመዘኛ እንደ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ያሉ ፕሮጀክቶች ዜጎች ዓመታትም ጠብቀውም ቢሆን ሊያገኙ የሚችሉበትን ዕድል የታጣው ፕሮጀክቱን በአግባቡ ካለማስተዳደር ነው ቢባል ከእውነት መራቅ አይሆንም፡፡ ይህም የከተማዋን የቤት ችግርና የኑሮ ውድነትን አስከትሏል፡፡ 

እውነታው ይህ ከሆነ በየዓመቱ ፍላጎቱ እየጨመረ የሚመጣውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ሌላ አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ዛሬ የምናየው የቤት ችግር የዚህች ከተማ ትልቅ ቀውስ ወደ መሆን እየተሸጋገረ መምጣቱ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የተከማቸውን ፍላጎት መፍቻ መፍትሔ ካልመጣም ችግሩ ይከፋል፡፡  

በከተማችን ዛሬ በርከት ብለው የሚታዩ የሪል ስቴት ግንባታዎች ለጥቂቶች ብቻ የሚሆኑ በመሆኑ፣ እነዚህን ግንባታዎች በማየት ብዙዎችን መድረስ የሚቻል ወይም መፍትሔ ያለመኖር በእጅጉ ያሳስባል፡፡ 

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ቁጥር አንድ ማሳያ እየሆነ የመጣውም፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ያገናዘበ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፖሊሲና አስተዳደር ጉዳዩ የአስተዳደሩ ቀዳሚ ሥራ ሊሆን ሲገባው፣ ይህ አለመደረጉ ትልቅ ችግር ነው፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተቋርጧል ከተባለ በኋላ፣ በአስተዳደሩ እንደ መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ ትልልቅ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታዎችን ለማካሄድ ከተለያዩ ትልልቅ ኩባንያዎች ጋር የተደረጉ ስምምነቶች መሬት ላይ ሊወርዱ አልቻሉም፡፡ 

ለዚህ አንድ ምሳሌ ብቻ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህም ከሦስት ዓመት በፊት የከተማ አስተዳደሩ ከአንድ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በአምስት ዓመት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ቤቶች እንደሚገነቡ አስታውቆ ነበር፡፡

ይህ ብዙ የተነገረለት ፕሮጀክት ይፋ ለማድረግ አስተዳደሩና ኩባንያው ለግባታው የሚሆኑ አስፈላጊው አቅርቦቶች ሁሉ መዘጋጀታቸውን ግንባታውን ሊያደናቅፍ የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ሁሉ ተናግሮ ነበር፡፡ ይህ ትልቅ ተስፋ የሰጠ ስምምነት ግን ዛሬ የለም፡፡ በተመሳሳይ ቁጥሩ ይህንን ያህል አይሁን እንጂ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ለመገንባት ተደረሱ የተባሉ ስምምነቶች ዛሬ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ አይታወቅም፡፡ ከባለሀብቶች ጋር በሽርክና ለመሥራትና በማኅበር ተደራጅቶ ቤት ለመገንባት የሚችል ስለመሆኑ ሁሉ የተነገረ ቢሆንም፣ እንደተባለው እየሆነ አይደለም፡፡ እንቅስቃሴው ደካማ ነው፡፡   

ከግል ዘርፉ ጋር በአጋርነት ይሠራሉ ተብለው ብዙ ሲነገርላቸው የነበሩ ዕቅዶችም የውኃ ሽታ ሆነዋል፡፡ በፌዴራልም ሆነ በአስተዳደሩ በቤቶች ኮርፖሬሽኖች ተገንብተው በከተማ ውስጥ የምናያቸውም ትልልቅ ሕንፃዎችም ጉዳይ ብዙ የሚያነጋግሩ ናቸው፡፡ እነዚህን ቤቶች ለመከራየትም ሆነ ለመግዛት ያሉት አሠራሮች ሁሉ ግልጽ አይደሉም፡፡  

ስለዚህ የመኖሪያ ቤት ችግር የከፋ ነገር ይዞ ሳይመጣ ዕርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚቀርቡ መፍትሔዎችም ቢሆኑ በብሔራዊ ደረጃ ታስቦባቸው የመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚመራበት ፖሊሲ ማውጣትን ይጠይቃል፡፡ አሁን በተበጣጠሰ ሁኔታ በተለያዩ መንገዶች እየተገነቡ ናቸው የሚባሉ ቤቶች ለኅብረተሰቡ ለማስተላለፍ በአንድ ጥላ ሥር የተደራጀ አሠራር መቅረፅን ሁሉ የሚጠይቅ ነው፡፡ የቤት ፈላጊውን ቁጥር ከማወቅ ባለፈ ትክክለኛ ፍላጎቱንም በመለየት የመፍትሔ ሐሳቡንም ከዚሁ ጋር በማስተሳሰርና ፈጣን ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ካልተደረጉ በከተማችን የቤት ችግር ብዙ ጣጣ ሊያመጣበት ይችላል፡፡ ስለዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክቶች ችግር ነበረበት ቢባል እንኳን፣ ይህንን ችግር ለይቶ መፍትሔ የሚሆኑ አሠራሮችን አክሎ ቢያንስ መክፈል የሚችሉ ዜጎች የቤት ባለቤት የሚሆኑበት አሠራር በመፍጠር ይህንን ፕሮጀክት ደግሞ መጀመር ግድ ይላል፡፡ 

አሁን እንደሚባለው የፋይናንስ ችግርን መልሶ መላልሶ በመግለጽ መሸሽ አይቻልም፡፡ በወር ቆጥቦ የቤት ባለቤት መሆን የሚችል ዜጋ በቤት ኪራይ የሚሰቃየው ባለቤት ለመሆን፣ በአቅሙ አማራጮች ባለመቅረባቸውና ጉዳዩን ነገ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ ከግምት ያስገባ ከልብ እየተሠራ ባለመሆኑ ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ለቤት ችግር ብሔራዊ ፖሊሲ ሊወጣና ዜጎች በየተራ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት አሠራር ይመቻች፡፡.