
ከ 9 ሰአት በፊት
አውሮፓ ሙሉ በሙሉ ራሷን የመከላከል አቅም ለማዳበር አስር ዓመት እንደሚያስፈልጋት ግዙፉ የጀርመን የመከላከያ ኩባንያ የሆነው ርሄይንሜታል ኃላፊ ለቢቢሲ ተናገሩ።
የአህጉሪቱ የጦር መሳሪያ ክምችት “መመናመኑንም” ነው አርሚን ፓፐርገር የተናገሩት።
ኃላፊው ይህንን አስተያየት የሰጡት የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ግዙፍ የተባለውን የጦር መሳሪያ ማምረቻ ኩባንያ የመሰረት ድንጋይ ለመጣል ሎወር ሳክሶኒ በተባለችው ግዛት በተገኙበት ወቅት ነው።
በዚህ ዝግጅት ላይ የጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ እና የሆላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬደሪክሰንም ተገኝተው ነበር።
ለዚህ ሁሉ የጦር መሳሪያ ክምችት “መመናመን” ስጋት መነሻ የሆነው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት የሰጡት አስተያየት ነው።
በመጪው የአሜሪካ ምርጫ የሪፐብሊካኑ ቀዳሚ እጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ ባለመክፈላቸው አገራቸው ከየትኛውም ወረራ እንደማትከላከልላቸው ለአንድ መሪ መንገራቸውን አስረድተዋል።
በአወዛጋቢ ንግግሮቻቸው የሚታወቁት ትራምፕ በነዚህ አገራት ላይ ወራሪዎች የፈለጉትንም እንዲያደርጉ “እንደሚያበረታቱም” አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ርሄይንሜታል በአዲሱ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ላይ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈስም አስታውቋል።
- ዋልታ እና ዋፋ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ስር ሊጠቃለሉ ነው13 የካቲት 2024
- አምቡላንሱ ውስጥ የተገደለው የጋዛው ነፍስ አድን ፈጥኖ ደራሽ13 የካቲት 2024
- የኢትዮጵያ አብዮት 50 ዓመት ኢዮቤልዩ በዓልን የመዘከር ፋይዳ12 የካቲት 2024
ማምረቻው በየዓመቱ 200 ሺህ የሚሆኑ የከባድ መሳሪያ ጥይቶችን እንደሚያመርትም ተነግሯል።
ሆኖም “ኔቶን መዋጋት የሚፈልግ ወራሪ ከመጣ” ለጦር ዝግጅት ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
“በሦስት፣ አራት ዓመታት ጥሩ እንሆናል። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ለመዘጋጀት አስር ዓመት ያስፈልገናል” ብለዋል።
“በአውሮፓ በየዓመቱ 1.5 ሚሊዮን ጥይቶች ማምረት ይጠበቅብናል” ሲሉም ነው ኃላፊው ያስረዱት።
አውሮፓ የነበራት የጦር መሳሪያ ክምችት ዩክሬንን ለማገዝ የሄደ ሲሆን “ይህም የአገሪቱን ክምችት አመንምኖታል” ብለዋል።
“ጦርነት እስከቀጠለ ድረስ ዩክሬንን ልናግዝ ይገባል፤ ነገር ግን የሚያስፈልገንን የጦር መሳሪያ ክምችት ለመሙላት ቢያንስ አምስት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ለመዘጋጀት ደግሞ አስር ዓመት ያስፈልገናል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የጀርመኑ ቻንስለር ሾልዝ የትራምፕ አስተያየት ስጋት ፈጥሮባቸው እንደሆነ ቢጠየቁም ምላሽ ለመስጠት ባይፈልጉም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ለካናዳ፣ ለአሜሪካም ሆነ ለአውሮፓ አገራት “ፍጹም አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።