አንድ ፓራሜዲክ ሕፃን ልጅ ተሸክሞ

13 የካቲት 2024

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ አሰቃቂ ክስተቶች የሚገለጹበት ይዘት አለው።

ዜናው የተሰማው ከሰዓት 8 ሰዓት ገደማ ነው።

የሕክምና ሠራተኛው ማህሙድ አል-ማስሪ እና ሌሎች የሥራ አጋሮቹ ሰሜናዊ ጋዛ ከሚገኘው አል-አውዳ ሆስፒታል ሆነው በተጠንቀቅ ይጠብቃሉ።

ዜናው በድምፅ ማጉያ ተነበበ። እንዲህ ይላል “አምቡላንስ ቁጥር 5-15 ተመትቷል።” ይህ አምቡላንስ የማህሙድ አባት አምቡላንስ ነው። እሳቸውም እርዳታ ሰጪ ናቸው።

ማህሙድ እና የሥራ ባልደረቦቹ የተፈጠረውን ለመቃኘት ወደ ሥፍራው ገሰገሱ።

ከሥፍራው ሲደርሱ አምቡላንሱ እንደ ጨርቅ ተበጣጥሶ እዚህም እዚያም ተበታትኗል። ማህሙድ ጭርምትምት ወዳለችው አምቡላንስ መሮጥ ጀመረ። ነገር ግን ውስጥ የነበሩት ሁሉ “ተቃጥለው እና ተበጣጥሰው” ተመለከተ።

የቢቢሲ አረቢኛ ዘጋቢ ፊልም አዘጋጆች ጦርነቱ በጀመረበት ወር ማህሙድ እና የሥራ ባልደረቦቹን ተከትለው ሲዘዋወሩ ነበር።

ማህሙድ አባቱን ዮስሪ እና ሌሎቹ ሁለት የሕክምና ባለሙያዎችን ሲያጣ የተሰማውን ስሜት በካሜራቸው ማስቀረት ችለዋል።

“ፊቱ እንዳልነበረ ሆኖ ነው ያገኘሁት” ይላል ማህሙድ እንባ እየተናነቀው።

ማህሙድ [በስተቀኝ] የአባቱን መገደል ካወቀ በኋላ የሥራ ባልደረባው ሲያጽናናው
የምስሉ መግለጫ,ማህሙድ [በስተቀኝ] የአባቱን መገደል ካወቀ በኋላ የሥራ ባልደረባው ሲያጽናናው

ይህ የሆነው ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ፣ እስራኤል በጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ ጦርነት በከፈተች በአምስተኛው ቀን።

የዮስሪ አል-ማስሪ አስከሬን በነጭ ጨርቅ ተጠቅልሏል። ደም የለበሰው የጭንቅላት መከላከያ ቆብ (ሄልሜት) ከጎናቸው ይታያል።

ቀብራቸው ሲፈጸም ማህሙድ ተንበርክኮ እያለቀሰ እንባውን ለመጥረግ ይሞክራል። ጭንቅላቱን ይወዘውዛል። የሥራ ባልደቦቹ ከበውታል።

የጋዛው ጋዜጠኛ ይህ ሲሆን ካሜራውን አቀባብሎ ይቀርፃል። ፌራስ አል አጃምሪ “ጋዛ 101፡ ኢመርጀንሲ ሬስኪው” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም እየሠራ ነው።

የ29 ዓመቱ ማህሙድ የሦስት ልጆች አባት ነው። ከአባቱ ሞት በኋላ ለተወሰኑ ሳምንታት እረፍት ወጣ።

ነገር ግን ብዙ መቆየት አልቻለም። ልቡ በአባቱ ሞት ቢደማም፤ ወደ ሥራ መመለስ ፈልጓል።

“ፍላጎቴ ፍልስጤማውያንን በአቅሜ መርዳት ነው” ይላል።

ስልኩ ስክሪን ላይ የአባቱን ፎቶ አድረጓል። “ሁሌም ላየው እፈልጋለሁ። ቀንም ሆነ ማታ።”

ነፍስ አድን ባለሙያዎች ከተመታው አምቡላንስ ውስጥ አስከሬን ሲያነሱ
የምስሉ መግለጫ,ነፍስ አድን ባለሙያዎች ከተመታው አምቡላንስ ውስጥ አስከሬን ሲያነሱ

ማህሙድ አባቱ ለመጨረሻ ጊዜ አብረው ያሳለፉት ከመሞታቸው ከጥቂት ሰዓታት በፊት ነበር።

አባቱ ቡና እንዲያፈላላቸው ጠየቁት። ሁሌም እኩለ ቀን ስግደት ከማድረጋቸው በፊት ቡና ይጠጣሉ። ልምዳቸው ነው። ከዚያ በኋላ አምቡላንሷ ተንቀሳቀሰች። ዮስሪ እና ባልደረቦቻቸው ተያይዘው ወጡ።

ነገር ግን አልተመለሱም።

ይህ ከመሆኑ ከሁለት ቀናት በፊት ሞሐመድ ጉዳት ደርሶበት ነበር። ወደ ሆስፒታል የሄደው በሰዎች እና በቃሬዛ ታግዞ ነው። የፍንዳታ ፍንጥርጣሪዎች አንገት እና ወገቡ ላይ ተሰክተው እንዳሉ ነበር ሆስፒታል የደረሰው።

አባቱ ይህን ሲመለከቱ እንባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም። ከልጃቸው አልጋ ጎን ሆነው አለቀሱ።

“በጣም ጨንቆት ነበር” ይላል ሞሐመድ።

ነገር ግን አሁን ስለአባቱ ሲያስብ ሰላም የሚነሳው ነገር ተበጣጥሳ የወደቀችው አምቡላንስ ናት።

“ሁሌም ብቻዬን ተቀምጬ ያንን ምሥል በአእምሮዬ መልሼ እከስተዋለሁ። ወደ አምቡላንሱ እየሮጥኩ ነበር። ወደ አባቴ እየሮጥኩ ነበር። ሰውነቱ ተገነጣጥሎ ስመለከት የምይዘው የምጨብጠው አጣሁ። ራሴን አለመሳቴ ይገርመኛል” ይላል።

ሞሐመድ የመጀመሪያ ህክምና ባለሙያ (ፓራሜዲክ) ሆኖ ለሰባት ዓመታት አገልግሏል። ብዙውን ጊዜ ያሳለፈው ጃባሊያ በተሰኘችው የጋዛ ሰፈር ነው። የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር አባል ነው።

ዘጋቢው ፊልም እነዚህን የአምቡላንስ ሠራተኞች ተከትሎ ከመስከረም ወር መጨረሻ ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል አብራቸው ሲዘዋወር የሚያስመለክት ነው።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም ሐማስ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎችን በመግደል 250 የሚሆኑትን ደግሞ አግቶ ወስዷል። ይህን ተከትሎ እስራኤል በምላሹ ከባድ ወታደራዊ እርምጃ በጋዛ ላይ መውሰድ ጀምራለች።

የማህሙድ አባት ዮስሪ የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር አባል ነበሩ
የምስሉ መግለጫ,የማህሙድ አባት ዮስሪ የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር አባል ነበሩ

በመጀመሪያው ወር ጥቃት 10 ሺህ ጋዛዊያን ተገድለዋል የሚለው በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ነው። ከጦርነቱ መጀመር በኋላ አስካሁን ባለው ጊዜ በጠቅላላው 27 ሺህ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተዘግቧል።

ፊልሙ የአምቡላንሱ ሠራተኞች የቆሰሉ ሰዎችን ተሸክመው ሆስፒታል ሲያደርሱ ያሳያል። አንዳንዴ ደግሞ የአምቡላንሱ ሠራተኞች ራሳቸው የጥቃቱ ሰለባ ሲሆኑ፣ አሊያም ዘመድ አዝማዶቻቸው ሲጎዱ ይታያል።

የሚያጋጥማቸውን ሁሉ ይዳስሳል፤ በተለይ ደግሞ የሕፃናትን አስከሬን ሲያነሱ በውስጣቸው ያለውን መሰበር ከፊታቸውን ያስመለክተናል።

በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሌላኛው ፓራሜዲክ ራሚ ኻሚስ ከአምቡላንስ ጎማ ሥር ተሸሽጎ ሲያለቅስ ይታያል።

ወደ ሥፍራው የመጣው አንደ ቤት ነዋሪዎች ውስጡ ሳሉ መደርመሱን ሰምቶ ነው። አብዛኛዎቹ ሕፃናት ናቸው። ወደ ውስጥ ሲዘልቅ የሦስት ሴት ሕፃናት አስከሬን መሬት ላይ ተዘርግቶ ተመለከተ። ይሄኔ ነው ሦስት ሴት ልጆቹ ድቅን ያሉበት።

“ራሴን መቆጣጠር አልቻልኩም። ሳላስበው ነው እንባዬ የወረደው” ይላል በድንጋጤ ሲያለቅስ የሚታይበት ምስል በወቅቱ የማኅበራዊ ሚድያ መነጋገሪያ የነበረው ኻሚስ።

በጥቅምት ወር መገባደጃ ላይ ደግሞ ሌላኛው የአምቡላንስ ሠራተኛ አላ አል-ሃላቢ ከዘመዶቹ ስልክ ተደወለለት።

ከሁለት ቀናት በፊት አጎቱ የሚኖርበት ቤት በእስራኤል የጦር አውሮፕላን መደበደቡን ሰማ። ነገር ግን አሁንም ከሕንፃው ፍርስራሽ ሥር ሰዎች እንዳሉ ተረዳ።

ከፍርስራሹ ሥር ከተገኙት አስከሬኖች መካከል አንዱ የአጎቱ ልጅ ነው። ወደ ሥፍራው ሲሄድ አንድ ሰው “እዚህ አንድ ልጅ አለች። ሰውነቷ ለሁለት ሳይከፈል አልቀረም” እያለ ይጮሀል።

በተመሳሳይ ቀን አላ ለአደጋ ጊዜ ሕክምና ተጠርቶ የሄደበት ሥፍራ አምስት ሕፃናት ክፉኛ ተቃጥለው የተደረደሩበት ቤት ነው።

“የሞቱ ሕፃናትን ሰውነት አቅፈህ ከፍ ስታደርግ መጀመሪያ ብልጭ የሚልልህ የእኔ ልጅ ቢሆንስ የሚለው ነው” ሲል ለፊልሙ አዘጋጆች ይናገራል።

ራሚ አምቡላንስ ውስጥ ሆኖ ሲያለቅስ
የምስሉ መግለጫ,ራሚ አምቡላንስ ውስጥ ሆኖ ሲያለቅስ

ጦርነቱ በተጀመረ በሳምንቱ እስራኤል ጋዛ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎቸ ወደ ደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል እንዲሸሹ አሳሰበች። ይሄኔ ነው አብዛኞቹ የአምቡላንስ ሠራተኞች ወደ ደቡብ ያቀኑት። የአምቡላንሱ ሠራተኞች ግን ይህን ማድረግ አልቻሉም።

ከቻሉ በስልክ አሊያም በቀይ ጨረቃ መገናኛ ሬዲዮ የቤተሰቦቻቸውን ደኅንነት ይጠይቃሉ።

ራሚ ፓራሜዲክ ሆኖ ለሁለት አስርት ዓመታት አገልግሏል። ሁሌም በጋዛ ግጭት ሲነሳ ሴት ልጆቹ የሱሪውን ጨርቅ ጨምድደው በመያዝ እንዳይሄድ ይወተውቱታል።

አላም እንዲሁም ወደ ሥራ ሲወጣ ልጆቹ በእንባ እንደሚሸኙት ያወሳል።

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር ሠራተኞች በዚህ ጦርነት ወቅት የገጠማቸውን፣ ያዩትን እና የሰሙትን ቤቱ ይቁጥረው።

አል-አድዋ ሆስፒታል አንድ ፍንዳታ ተከስቶ ለወትሮው ለአደጋ ጊዜ የሚፈለጉ የአምቡላንስ ሠራተኞች ራሳቸው መሸሸግ ጀመሩ።

ቢያንስ ሁለት አምባላንሶች ከጥቅም ውጪ ሆኑ። ይህ የሆነው እስራኤል ከሆስፒታል አጠገብ ያለ አንድ ቤት ዒላማ በማድረጓ ነው ይላል አንድ የአምቡላንስ ሠራተኛ።

እስራኤል ግን “እኔ ከሆስፒታሉ በመቶ ሜትሮች ርቀት ያለ ዒላማን ነው የመታሁት” ትላለች።

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በጋዛ 11 አባላቴ ተገደለዋል ይላል።

ማኅበሩ መንግሥታዊ ያልሆነ የተራድዖ ድርጅት ሲሆን፣ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን አባል ነው።

በጄኔቫ ሕግ መሠረት የቀይ መስቀል አሊያም የቀይ ጨረቃን ምልክት ያነገቡ መኪኖች የሕክምና የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች በመሆናቸው ሊጠበቁ ይገባል።

አላ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አድርጎ
የምስሉ መግለጫ,አላ

የሞሐመድ አባት የሞቱበት 5-15 አምቡላንስ የማኅበሩን ዓርማ እያውለበለበ ነበር።

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር የእስራኤል ወታደሮች ሆነ ብለው ነው አምቡላንሱን ዒላማ ያደረጉት ይላል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ደግሞ “ሆን ብለን ማንኛውም ዓይነት የሕክምና ሠራተኛ እና የቀይ ጨረቃ ማኅበር አባላትን ዒላማ አናደርግም” ይላል።

አምቡላንስ 5-15 ከነበረችበት ሥፍራ “መቶ ሜትሮች ርቆ የነበረን ዒላማ መትተናል እንጂ አምቡላንሱ ዒላማ አልተደረገም” ይላል የእስራኤል ጦር።

የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ እንደሚለው የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ ከባድ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረች ወዲህ ባለው ጊዜ በጠቅላላው ጋዛ ውስጥ 59 ተሽከርካሪዎቹ ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ይገልጻል።

ባለፈው ታኅሣሥ ማኅበሩ ጃባሊያ የሚገኘው ጣቢያው በእስራኤል ኃይል ጥቃት ስለደረሰበት በሰሜናዊ ጋዛ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ገታ ማድረጉን ይናገራል።

አላ፣ ራሚ እና ማህሙድ አሁን ወደ ደቡባዊ ጋዛ አቅንተዋል። ኻን ዩኒስ የተሰኘው አካባቢ የአደጋ ጊዜ ሕክምና እርዳታ ይሰጣሉ።

በጥር ወር መገባደጃ ላይ በኻን ዩኒስ ጦርነት ሲበረታ ማህሙድ ሚስቱን እና ሦስት ልጆቹን አል-ማዋሲ ወደተሰኘ በንጽጽር ሰላማዊ ወደ ሚባል ሥፍራ አዛውሯቸዋል።

አባቱ ከሞቱ አራት ወራት አልፏቸዋል። እሱም በጦርነት እና በምግብ እጦት የተጎዱ ወገኖቹን ማገዙን ቀጥሏል።

“የአባቴ መልዕክት ይህ ነበር። እኔም የአባቴን ምክር ተከትዬ ይህን ማድረጌን እቀጥላለሁ።”