የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን

ከ 9 ሰአት በፊት

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን በወራት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ሆስፒታል በመግባታቸው ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስብሰባ የሚያደርጉትን ጉዞ ሰረዙ።

የ70 ዓመቱ ኦስቲን ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ ሆስፒታል ጥብቅ የሕክምና ክትትል በሚያስፈልጋቸው ህሙማን ክፍል ውስጥ ናቸው።

ፔንታገን እንዳለው ሚኒስትሩ ሆስፒታል የገቡት ድንገተኛ የሽንት ፊኛ ችግር ገጥሟቸው ነው።

ኦስቲን ማክሰኞ ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ እንዳለው ፔንታገን የገለጸ ሲሆን ለጊዜው ግን ያለባቸው ኃላፊነት ለምክትላቸው ተላልፏል ብሏል።

ሰኞ ዕለት በፔንታገን የወጣው የዋልተር ሪድ የጦር ሆስፒታል ባለሥልጣናት መግለጫ እንዳለው ሚኒስትሩ ለተራዘመ ጊዜ ሆስፒታል ውስጥ ይቆያሉ ተብሎ አይጠበቅም።

“ሚኒስትሩ ነገ [ማክሰኞ] ወደ መደበኛ ሥራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ አለን” ብሏል መግለጫው።

ሆኖም የመጀመሪያ ጥቁር የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሆስፒታል ውስጥ የሚቆዩት ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ አልተጠቀሰም ።

አሁን ላይ ኦስቲን ያጋጠማቸው የሽንት ፊኛ ችግር ከካንሰር እንደሚያገግሙ የተጣለውን ተስፋ እንደማይለውጥም ተነግሯል።

የፔንታገን ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል ፓት ራይደር እንዳሉት “ ኦስቲን እያደረጉ ያለው የካንሰር ሕክምና አመርቂ ውጤት እያስገኘ ነው”

ሚኒስትሩ ረቡዕ በቤልጂየም ብራስልስ በዩክሬን ዲፌንስ ኮንታክት ግሩፕ (ዩዲሲጂ) የሚካሄደውን ስብሰባ ይመራሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ይህ ጉዟቸው ቢሳካ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ የሚያደርጉት የመጀመሪያው የባህር ማዶ ጉዞ ይሆን ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ሐሙስ ዕለት በሚካሄደውና በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ኃላፊ ጀንስ ስቶልትንበርግ በሚመራው የድርጅቱ መከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ለመገኘትም ይዘውት የነበረው እቅድ ሳይሳካ ቀርቷል።

ኦስቲን ዩክሬንን ለመከላከል የተቋቋመው ቡድን የመጨረሻ ስብሰባ ላይ የተካፈሉት ጥር ወር መጨረሻ ላይ ከቤታቸው ሆነው ነበር።

ረቡዕ የሚካሄደውን የቡድኑን ስብሰባም በበይነ መረብ አማካኝነት ለመካፈል ማቀዳቸውንም ቢሯቸው ለቢቢሲ ገልጿል።

ኦስቲን ቀደም ብሎ በምስጢር ሆስፒታል መግባታቸውን ተከትሎ ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው።

ሚኒስትሩ ምርመራ እየተካሄደባቸው ያለው ታኅሳስ ወር ላይ የፕሮስቴት ካንሰር ሕክምና ሲያደርጉም ሆነ ጥር ወር ላይ በድጋሜ ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ ለሕዝቡም ሆነ ለአሜሪካ የመንግሥት መዋቅር ላይ ላሉ ቁልፍ ሰዎች አለማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው።

ፔንታገን እሁድ እለት ከሰዓት ባወጣው መግለጫ ኦስቲን ለሕክምና ሜሪላንድ ወደሚገኘው ዋልተር ሪድ ብሔራዊ የጦር ሆስፒታል መወሰዳቸውን የዋይት ሃውስ እና ከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣናት እንዲያውቁ መደረጉን አስታውቋል።

የዚያኑ ዕለት በድጋሜ ባወጣው መግለጫ ኦስቲን ኃፊነታቸውንና ሥራቸውን ለምክትል መከላከያ ሚኒስትሩ ካትሊን ሂክስ ማስተላለፋቸውን ገልጿል።

በኋላ ላይም ሆስፒታሉ ለኦስቲን የቅርብ ክትትል ለማድረግ የፅኑ ህሙማን ክፍል መግባታቸውን ገልጾ ነበር።

ሐኪሞች ኦስቲን ያጋጠማቸው የሽንት ፊኛ ችግር ከካንሰር ሙሉ በሙሉ እንደሚያገግሙ የተጣለውን ተስፋ ይለውጣል ተብሎ እንደማይጠበቅ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ኦስቲን ከካንሰር ሕክምና ጋር በተያያዘ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው ነበር።

ሕክምናውን ተከትሎም እግራቸው፣ ዳሌያቸው እና ሆዳቸው ላይ ባጋጠማቸው የከፋ ሕመም ምክንያት በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ላይ እንደገና ሆስፒታል ገብተው ነበር።

በዚህ ወቅትም የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን እንደተገኘባቸው የተገለጸ ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በላይ ሆስፒታል ውስጥ ቆይተዋል።

ከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣናት እና የባይደን አስተዳደር ኦስቲን በድጋሜ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ እስከ ሦስት ቀን ድረስ በጠና መታመማቸውን አያውቁም ነበር።

የመከላከያ ሚኒስትሩ በአሜሪካ የመንግሥት መዋቅር ከፕሬዚደንቱ ቀጥሎ ማንኛውም ወታደራዊ ትዕዛዝ ለመስጠት በተጠንቀቅ ያለ ሰው ሲሆን በጣም ወሳኝ ከሆኑ የካቢኔ አባላት አንዱ ናቸው።

ኦስቲን ሕክምናቸውን በድብቅ ሲያደርጉ መቆየታቸው በግልጸኝነት እና በደኅንነት ላይ ስጋት የፈጠረ ነው በሚልም ሦስት የተለያዩ ምርመራዎች እንዲካሄዱባቸው ምክንያት ሆኗል።

አንዳንድ ታዋቂ ሪፐብሊካኖች ከሥልጣን እንዲነሱም ጠይቀዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ኦስቲን በተገቢው መንገድ ባለማሳወቃቸው ማዘናቸውን የገለጹ ሲሆን ፕሬዚደንት ባይደንንን በግል ይቅርታ እንደጠየቁ ተናግረዋል።

መከላከያ ሚኒስትሩ ለመንግሥት መሪዎች ያላሳወቁበትን ምክንያት በተመለከተ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ቃላቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።