
ከ 4 ሰአት በፊት
በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል አሁንም ድረስ አለመተማመን መኖሩን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ።
አቶ ጌታቸው ይህንን ያሉት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ከተመሠረተው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባለፈው ሳምንት የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ነው።
አቶ ጌታቸው ሰኞ የካቲት 4/2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ በአሁኑ ወቅት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል አለመተማመን መኖሩን አንስተዋል።
ለዚህም እንደ ዋቢ ያነሱት ክልሉ ያለበትን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቅረፍ ያቀረበው የብድር ጥያቄ ከፌደራሉ መንግሥት ተቀባይነት አለማግኘቱን በመጥቀስ ነው።
“ብድር ጠይቀን ነበር ነገር ግን ተቀባይነት አላገኘንም። ብድር ወስዳችሁ ምን ላይ ነው የምታውሉት? የሚል ስጋት እንዳለም ግልጽ ነው። በአጠቃላይ ያለማመን ነገር አለ። ‘የመጣ ገንዘብ ቢመጣ ትጥቃችሁን ለመፍታት ፍላጎት የላችሁም። ሠራዊታችሁን ማጠናከር ነው የምትፈልጉት’ በአጠቃላይ ብዙ የሚነሱ ነገሮች አሉ” ብለዋል።
የትግራይ አመራሮች በበኩላቸው በምላሹ “ሕዝባችን በሰላም መኖሩን ከማረጋገጥ ውጪ፣ የሆነ አካባቢን የማወክ ወይም የማዕካላዊ መንግሥት ሥልጣንን የመመኘት ፍላጎት እንደሌለን በሚገባ ለማስረዳት ሞክረናል” ሲሉም ነው አአቶ ጌታቸው የገለጹት።
ከዚህ በተጨማሪ በፌደራል መንግሥት በኩል የቀረበባቸው ወቀሳ ‘እኛን ለማዳከም ከሌሎች ኃይሎች ጋር ትሠራላችሁ፣ እንዲሁም በትግራይ የሚፈራ ሃብት በጥቁር ገበያ ትሸጣላችሁ? መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ትደግፋላችሁ የሚል ነው ብለዋል።
የትግራይ አመራሮች በበኩላቸው ‘የፌደራል መንግሥት ትግራይን ለማዳከም እየተንቀሳቀሰ ነው፤ አንድነታችንን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ነው፣ ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኗል’ የሚሉ ክሶች ለፌደራሉ መንግሥት አመራሮች ማቅረባቸውንም ነው አቶ ጌታቸው የገለጹት።
ከፌደራል መንግሥቱ በኩል ከሌሎች ኃይሎች ጋር ትሰራላችሁ በሚል የቀረበባቸውን ክስ እንደማይቀበሉት ፕሬዝዳንቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በተጨማሪም ወርቅን በተመለከተ በሕጋዊ መንገድ እንደሚሸጥ፣ ሆኖም ይህ በግለሰቦች እንጂ በክልሉ መንግሥት የሚሠራ እንዳልሆነ አብራርተዋል።
አቶ ጌታቸው በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የፌደራሉ መንግሥት መፈጸም ከነበረበት አንዱ እና አልተፈጸመም ብለው የጠቀሱት ተዋጊዎችን ትጥቅ የመፍታት እና መልሶ የማቋቋም (ዲሞቢላይዜሽን እና ሪኢንተግሬሽን) ነው።
የትግራይ ኃይሎች ከ270 ሺህ በላይ ሠራዊት እንዳለው የጠቀሱት አቶ ጌታቸው ይህ ሠራዊት ወደ ቤቱ የሚመለስ ከሆነ ለዚህ የሚመጥን በጀት መኖር እንዳለበት ጠቅሰዋል።
መልሶ ማቋቋሙ ተግባራዊ እንዲሆን “የፌደራሉ መንግሥት ከውጭም ጭምር ገንዘብ ሰብስቦ ማምጣት አለበት” ሲሉም ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።
ይህ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ በካምፕ ውስጥ ሆኖ የፌደራል መንግሥት ስንቅ የማቅረብ ኃላፊነት እንደነበረበት ጠቅሰው፣ ለአንድ ወር አካባቢ ስንቅ የማቅረብ እንቅስቃሴ የነበረ ቢሆንም አለመቀጠሉን አቶ ጌታቸው አመለክተዋል።
“ይህ ሠራዊት መስዋዕትነት የከፈለ፣ ለትግራይ ህልውና የቆመ ሠራዊት የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሳይሆን ተበተን የምንልበት ምክንያት ስለሌለ፤ ብዙ ችግር እያለም ቢሆን ከመንግሥት ሠራተኛ ገንዘብ እየቀነስን ለሠራዊቱ ወጪ የምናወጣበት ሁኔታ አለ። ይህንንም መተሳሰብ አለብን” ሲሉም ተደምጠዋል።
ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በተመለከተ የህወሓት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የአሜሪካ መንግሥት፣ የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች በሚገኙበት በቅርቡ ግምገማ እንደሚደረግ አመለክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትብብር ትላልቅ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉበት ነው ማለታቸው ይታወሳል።
- የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት ስረዛ ይነሳልኝ ጥያቄ ተቀባይነት እንዳላገኘ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ13 ግንቦት 2023
- ህወሓት ክልላዊ ምርጫ ቢያከናውን “ሕገ-መንግሥታዊ አይሆንም” ወ/ት ብርቱኳን5 ግንቦት 2020
- “ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የመዋጋት ፍላጎት የላትም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ6 የካቲት 2024
የህወሐትን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ ከመግባባት ተደርሷል
በትግራይ የተቀሰቀውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተሰርዞ የቆየውን የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ ከፌደራል መንግሥት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል።
ከፌደራሉ መንግሥት ጋር በነበረው ውይይታቸው የህወሓትን ሕጋዊ እውቅና ለመመለስ ስምምነት ላይ መደረሱን እንዲሁም ሌሎች የተነሱ አንኳር ነጥቦችን አብራርተዋል።
“የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት ስረዛ በሚመለከት የፌደራሉ መንግሥት ምርጫ ቦርድ የወሰነው ውሳኔ ብዙም እንደማይደግፈው፣ ህወሐት እያሉ መግለጫ እያወጡ ህወሓትን አናውቀውም የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል፤ ያሉት የሕግ እንቅፋቶች በፍጥነት ተስተካክለው ህወሓት ሕጋዊ ፓርቲነቱ የሚረጋገጥበት ሁኔታ እንዲፈጠር በሚል ተግባብተናል” ሲሉም ተደምጠዋል።
በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ህወሓትን በአሸባሪነት ፈርጆት የነበረ ሲሆን፣ በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የፓርቲው የአሸባሪነት ብያኔ መነሳቱ ይታወሳል።
ሆኖም ምርጫ ቦርድ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ለመንቀሳቀስ የሚችለው በተደነገገው አዋጅ መሠረት በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሕጉን መሠረት አድርጎ ሲፈቅድ መሆኑንም ማስታወቁ ይታወቃል።
ህወሓትም በምርጫ ቦርድ የተላለፈበትን የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ስረዛ እንዲነሳለት ጥያቄ ቢያቀርብም ምርጫ ቦርድ ውድቅ አድርጎት ነበር።
አቶ ጌታቸው ከፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጋር በተደረገው ውይይት የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት በሚመለስበት መነግድ ላይ ከመግባባት ላይ መደረሱን እና ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል።
“ይህንን በሚመለከት በፍትህ ሚኒስቴር በኩል አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ [የፌደራል መንግሥት] የቤት ሥራ ወስዷል፤ በአጭር ጊዜ እንፈጽመዋለን ማለት ነው” ብለዋል።
የፌደራል መንግሥት እና ህወሓት ባካሄዱት ግምገማ በመካከላቸው መተማመንን ለመገንባት፣ ተፈናቃዮችን በአስቸኳይ ወደ ቦታቸው ለመመለስ፣ በሁለቱም በኩል ያሉ እስረኞችን ለመፍታት እና የክልሉን ግንባታ በተመለከተ ከስምምነት ላይ መደረሱንም አመልክተዋል።
“ሕዝበ ውሳኔ አሁን ሊደረግ አይችልም”
ሌላኛው አቶ ጌታቸው የጠቀሱት በክልሉ ውስጥ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በሚመለከትም ከፌደራል መንግሥት ጋር የተደረገውን ውይይት ነው።
አቶ ጌታቸው የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ተፈናቃዮችን በአስቸኳይ ለመመለስ ቢስማሙም፣ በእነዚህ አካባቢዎች ሕዝበ ውሳኔ አሁን ሊደረግ የሚችል አለመሆኑን መግለጻቸውን ተናግረዋል።
ከፌደራል መንግሥት በኩልም የግድ ሕዝበ ውሳኔ መካሄድ አለበት የሚል አቋም እንደሌለም ነው ያስረዱት።
በእነዚህ አካባቢዎች ለሚነሳው የይገባኛል ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ለመመለስ የተጀመረው ጥረት በግጭቶች ምክንያት መደናቀፉን፣ በጉዳዩ ላይ ሁለቱ ክልሎች መረጃ ከተሰጣቸው በኋላ ወደ ተግባር ለመግባት የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ጠቅሰዋል።
የወሰን ይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ሕዝበ ውሳኔ እና ውይይት እስኪካሄድ ድረስ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ፣ እንዲሁም የራሳቸውን ተወካዮች መርጠው እንዲተዳደሩም መንግሥታቸው ይሠራል ብለዋል።
ድርቁን በተመለከተ
አቶ ጌታቸው በክልሉ የተከተሰተውን አስከፊ ድርቅ በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያም የፌደራሉ መንግሥት አሁንም በረሃብ የሞቱ ሰዎች የሉም ብሎ እንደሚያምን እና “ይህ ግን ለማንም እንደማይጠቅም” አስረድተዋል።
ነገር ግን ችግሩን ለማቃለል “የፌደራል መንግሥት የሚቻለው እንደሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ የሆነ ይሁን ፕሮጀክት አጥፈንም ቢሆን የትግራይ ሕዝብን እንደግፋለን” መባሉን ገልጸዋል።
በርካታ የረድዔት ተቋማት ኢትዮጵያ የከፋ ረሃብ ሊያጋጥማት እንደሚችል እያስጠነቀቁ ባለበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርቁን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ መጠቀም አግባብ አይደለም ሲሉ ከሰሞኑ ተደምጠዋል፡፡
“ድርቅ መንግሥት አላመጣውም፣ ችግኝ እንተከል ሲባል ምን ያደርጋል ስንል፣ ስንዴ እናምርት ስንል ምን ያደርጋል ብለን ድርቅ መጣ ብለን ብንጮህ ትርጉም የለውም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“በረሃብ ምክንያት የሚሞት ሰው የለም” ብለውም የተከሰተው ድርቅ የሰው ሕይወት እንዳይቀጥፍ መተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱ አመት ጦርነት በክልሉ ከ80 ቢልዮን ብር በላይ የሚገመት ውድመት መድረሱንም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አሳውቀዋል።