ባሕር ዳር
የምስሉ መግለጫ,የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር

ከ 5 ሰአት በፊት

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት ሦስት የጎጃም ዞኖች በጥር ወር ከ65 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጪ መገደላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 5/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል እተካሄደ ባለው “የትጥቅ ግጭት” የንጹኃን ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሚፈጸም ግድያ አሳሳቢነቱ ቀጥሏል ብሏል።

ካለፈው ዓመት ማብቂያ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች የሚካሄደው ግጭት የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

በሁለቱ ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ባሻገር በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች እልባት ሳያገኙ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል በማለት ኮሚሽኑ በጥር ወር ብቻ በሦስት ዞኖች የተፈጸሙ ግድያዎችን መከታተሉን ግልጿል።

በዚህም በሰሜን ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም እና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በአንድ ወር ብቻ ቢያንስ 66 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

ጥር 20/2015 ዓ.ም. በሰሜን ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ኢሰመኮ “ማንነታቸውን ማረጋገጥ የቻላቸው” 45 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች እና የከተማይቱ ነዋሪዎች የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ እንደሚል ጠቅሰው፤ ግድያው ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ እና መንገድ ላይ በተገኙ ሰላማዊ ሰዎች ላይ እንደተፈጸመ ተናግረዋል።

ግድያው የተፈጸመው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና የፋኖ ታጣዊዎች ለሰዓታት ውጊያ አድርገው የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው ከወጡ በኋላ መሆኑንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ንጹኃኑ “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” ተብለው መገዳላቸውን የገለጸው የኢሰመኮ መግለጫ፤ ቁጥራቸውን ማረጋገጥ ያልቻላቸው “የፋኖ አባላት ናችሁ” ተብለው የተያዙ ሰዎችም መገደላቸውን አመልክቷል።

“[ከተገደሉ] የሲቪል ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ እስከአሁን ድረስ ማንነታቸውን በመለየት ለማረጋገጥ የተቻለው 45 ሲቪል ሰዎችን ብቻ ነው” ያለው ኢሰመኮ፤ ሆኖም የጉዳቱ መጠን ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ገምቷል።

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ኧርቪን ማሲንጋ፣ በመርዓዊ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በሚመለከት የወጡ ሪፖርቶች መንግሥታቸውን እንደሚያሳስበው ገልጸው፣ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ በማድረግ ግድያ የፈጸሙ ላይ ምርመራ ተደርጎ ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቃቸው ይታወሳል።

በመርዓዊ ከተማ ከተፈጸመው የሰላማዊ ሰዎች ግድያ ባሻገርም በምሥራቅ ጎጃም ሸበል በረንታ ወረዳ የዕድ ውሃ ከተማ ጥር 10/2016 ዓ.ም. የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች 15 ሰዎችን መግደላቸውንም ኢሰመኮ አስታውቋል።

በከተማዋ በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል የተደረገን ውጊያ ተከትሎ ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻና መንገድ ላይ የተገኙ ንጹኃን ላይ ግድያ መፈጸሙን ጠቅሷል።

በተጨማሪም ጥር 6/2016 ዓ.ም. በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ወይበይኝ ቀበሌ አብሥራ በተባለ አካባቢ “በወታደራዊ ቅኝት” ወቅት ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ የመንግሥት ኃይሎች 6 ሰላማዊ ሰዎችን ከቤታቸው አውጥተው ገድለዋል ብሏል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በሁሉም ወገኖች እየተደረገ ባለው ግጭት “እየደረሰ ያለው ስቃይ እጅግ እየጨመረ” ነው ካሉ በኋላ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ ለአቅርበዋል።

ቢቢሲ ጥቃቱን ተከትሎ ያናገራቸው የህክምና ባለሙያን ጨምሮ የመርዓዊ ከተማ ነዋሪዎች የተመለከቷቸውን አስከሬኖች መሠረት በማድረግ “ከስድስት ዓመት ህጻን እስከ 75 ዓመት አዛውንት” ድረስ ያሉባቸው ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አንዳንዶችም የሟቾች ቁጥር ከ100 በላይ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው ነበር።

በመርዓዊ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ግድያ ተከትሎ ስጋት የገባቸው አንዳንድ ነዋሪዎች ወደ ባሕር ዳር እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሸሻቸውን ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል።

በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለውበታል የተባለውን የመርዓዊውን ክስተት በተመለከተ የክልሉ መስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።

ካለፈው ዓመት ማብቂያ ወዲህ በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸው ይታወቃል።