
13 የካቲት 2024
አንድ “ግዙፍ ሚዲያ” ለመፍጠር በሚል ዋልታ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት እንዲሁም ዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን፤ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ስር ሊጠቃለሉ ነው። በፋና እና በዋልታ ውስጥ የ25 በመቶ ድርሻ ያለው የትግራይ መልሶ ማቋቋም ኢንዶውመንት ፈንድ (ኤፈርት) በጉዳዩ ላይ አለመሳተፉን ለቢቢሲ ገልጿል።
ከገዢው ፓርቲ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው እነዚህ ተቋማት ከሌሎች በተለየ መንግሥታዊ ዜና እና መረጃዎችን በቀዳሚነት በማግኘት እና በማቅረብ የሚታወቁ ናቸው።
ቀደሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አሁን ደግሞ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ፋና እና ዋልታ፤ እንዲዋሃዱ ለማድረግ ሥራው ካለፈው ታኅሣሥ ወር ጀምሮ በሂደት ላይ እንደሆነ የሁለቱ መገናኛ ብዙኃን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለተቋማቱ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደሚያስረዱት ሁለቱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እና የኹነት አዘጋጁ ድርጅት ዋፋ እንዲዋዱ እየተደረገ ያለው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ሀሳብ አመንጪነት” ነው።
በኢህአዴግ የትጥቅ ትግል ጊዜ የተቋቋመው ፋና፤ በአዲስ መልክ የመጀመሪያው “የግል” ሬዲዮ ጣቢያ ሆኖ የተቋቋመው ከ29 ዓመታት በፊት በ1987 ዓ.ም ነበር። ፋና ራዲዮን የመሠረቱት ከአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር “ግንኙነት አላቸው” የሚባሉት የትግራዩ ኤፈርት፣ የአማራው ንጋት ኮርፖሬት (የቀድሞው ጥረት)፣ የኦሮሚያው ቱምሳ ዲቨሎፕመንት ግሩፕ (የቀድሞው ዲንሾ) እንዲሁም የ“ደቡብ” ክልሉ ወንዶ ናቸው።
ፋና ሬዲዮ በ2003 ዓ.ም. ወደ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያደገ ሲሆን፣ ከስድስት ዓመት በፊት በ2010 ዓ.ም. ደግሞ የቴሌቪዥን ጣቢያ መክፈቱ ይታወሳል። ፋና ሬዲዮ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በተለያዩ ክልሎች በሰባት ቋንቋዎች ፕሮግራሞችን የሚያስተላልፉ 12 የማሰራጫ ጣቢያዎች አሉት።
ከፋና ተመሳሳይነት ባለው መልኩ በአራቱ የልማት ድርጅቶች ባለቤትነት የተቋቋመው ዋልታም ምሥረታው ከኢህአዴግ ጋር ግንኙነት ያለው ነው። “የኢህአዴግ ኢንፎርሜሽን ማዕከል” በሚል ስያሜ የዜና ተቋም ሆኖ የተመሠረተው ዋልታ፤ የተቋቋመው በ1986 ዓ.ም ነው።
ዋልታ ካለፈው ዓመት መጨረሻ አንስቶ “አዲስ ዋልታ” ተብሎ የሚጠራውን የቴሌቪዥን ጣቢያ በ2010 ዓ.ም. ያቋቋመ ሲሆን፣ በቅርቡም በውጭ ቋንቋዎች ፕሮግራሞችን የሚያስተላልፍ “አፍሮ ኒውስ” የተባለ የቴሌቪዝን ጣቢያ ከፍቶ በሙከራ ሥርጭት ላይ ነው። ከዚህም ባሻገር የቀድሞውን “አፍሮ ኤፍኤም” በመግዛት እና “አዲስ ዋልታ ኤፍኤም” ወደሚል መጠሪያ በመቀየር የሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት ሆኗል።
ሁለቱ ግዙም የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ፋና እና ዋልታ፤ በ2000 ዓ.ም በኹነት ዝግጅት (event organizing) ሥራ ላይ የተሰማራውን ዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን አቋቁመዋል። ከሁለቱ ተቋማት ስም የመጀመሪያዎቹን ፊደላት በመውሰድ የተመሠረተው ዋፋ መንግሥታዊ ኹነቶችን በማዘጋጀት በይበልጥ ይታወቃል።
- ‘ተዉኝ ልኑርበት!’. . . ዜጎች መረጃ ለመስጠት ያለባቸው ስጋት እና የመገናኛ ብዙኃን ፈተና26 ጥር 2024
- የፕሬስ ነጻነት ሁኔታ በኢትዮጵያ እና ጋዜጠኞች የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች3 ግንቦት 2023
- ዩቲዩብ የቲቢ ጆሽዋ ንብረት የሆነውን የኢማኑኤል ቲቪ ቻናልን ዘጋ1 የካቲት 2024
ስለ ውህደቱ የተዘጋጀው ሰነድ ምን ይላል?
ቢቢሲ የተመለከተው ተቋማቱን ለማዋሃድ የተዘጋጀው ባለ 28 ገጽ የመነሻ ዕቅድ ሰነድ እንደሚያስረዳው፤ ዋልታ፣ ፋና እና ዋፋ እንዲቀላቀሉ የተፈለገበት “ዋናው” ምክንያት “በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት” የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ለመፍጠር ነው።
ሰነዱ “አገራችን ለማሳካት እየሠራችበት ያለውን ብሔራዊ ገዥ ትርክት ዋና አጀንዳው በማድረግ የአገራችንን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን የሚያስችል ዋነኛ የሚዲያ እና የኮሙዩኒኬሽን አቅም ይሆናል” ሲል በተቋማቱ ውህደት የሚፈጠረው “ግዙፍ ሚዲያ” ምን ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ አስፍሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ከዕዳ ወደ ምንዳ” በሚል ርዕስ ከአራት ወራት በፊት ጥቅምት ላይ ለከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ሥልጠና በሰጡበት ወቅት ስለ ገዢ ትርክት የመፍጠር አስፈላጊነት ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
የመነሻ ዕቅድ ሰነዱ እንደሚያስረዳው ከውህደቱ በኋላ የሚፈጠረው መገናኛ ብዙኃን “ለብሔራዊ ጥቅም ዘብ” ሆኖ የሚቆም ሲሆን፣ የመንግሥትን ፖሊሲ እና የተቋማትን አፈጻጸምም “እየተቸ የሚደግፍ ሚዲያ” ይሆናል።
የመገናኛ ብዙኃኑ “ብሔራዊ ገዥ ትርክትን የኢትዮጵያውያን አቋም እና እምነት እንዲሆን” እንደሚሠራ የሚገልጸው ሰነዱ፤ ይህንን ማስረጽ በሚያግዙ “የሚዲያ ሥራዎች” ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ይገልጻል።
“የብሔራዊነትን ትርክት በልዩ ልዩ መንገድ ማስረጽ ዓላማቸው የሆኑ የፊቸር ፊልም፣ የዶክመንትሪ ፊልም፣ የሙዚቃ ዝግጅት እና የኅትመት፣ የቴአትር፣ የልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ መድረኮች ሥራዎች” በሚዲያው አማካኝነት እንደሚከወኑም ተጠቅሷል።
የተቋማቱ መዋሃድ ጥቅም ሆኖ በሰነዱ ላይ የተጠቀሰው ሌላኛው ጉዳይ “ውድድርን ማሸነፍ የሚችል” መገናኛ ብዙኃን የመፍጠር ጉዳይ ነው።
ሰነዱ ይህንን ሀሳብ ሲያብራራ፤ “የሁለቱን ሚዲያዎች አቅም በማቀናጀት የሚፈጠረው ሚዲያ ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር በሰው ሃብት፣ በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ፣ በቁሳቁስ እና በሌሎችም አቅሞች ተወዳዳሪ ብሎም በልዩ የትኩረት አጀንዳዎቹ መሪ ሚዲያ ለመሆን ይችላል” ይላል።
ተቋማቱ ተዋህደው ይህንን ሥራ የሚያከናውነው የመገናኛ ብዙኃን ሲመሠረት “ፋና” የሚለውን “የነባሩን ሚዲያ ስያሜ” እንደያዘ መቀጠሉ “ተመራጭ” እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል።
ሰነዱ “በሚዲያ ዘርፍ በተለይም በሬዲዮ ሚዲያ ዘርፍ ሰፊ ተቀባይነት ያለው፤ በቴሌቪዥን ዘርፍ ደግሞ ከኢቢሲ የሚወዳደር፣ አንዳንድ ጊዜም ከኢቢሲ የሚበልጥ ሚዲያ በመሆኑ፤ ከዋልታ ስም አንጻር የፋና ስም ገናና ነው” ሲል ፋና የተመረጠበትን ምክንያት ያስረዳል።
ፋና የተመረጠው “በአድማጭ ተመልካቹ ዘንድ የተገነባውን መልካም ስም ለይዘት ለተዓማኒነት ያለውን ፋይዳ ግምት” በማስገባት የተቀመጠ መሆኑን የሚጠቅሰው ሰነዱ፤ ተቋሙ “በገበያ ውስጥ ያለውን የቆየ ስም ማስቀጠልም” ሌላኛው ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል።
ተቋማቱ ሲዋሃዱም አሁን ያለው “ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት” የሚል ስያሜ “ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን” ተብሎ እንደሚቀየር ይጠቁማል።

“ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን” በስሩ ምን ምን ይይዛል?
የመነሻ ዕቅድ ሰነዱ፤ የሦስቱ ተቋማት ውህድ የሆነው “ግዙፍ” የመገናኛ ብዙኃን ሲደራጅ “የቲቪ ዘርፍ፣ የሬዲዮ ዘርፍ፣ የኪነ ጥበብ ዘርፍ፣ እና የኤቨንት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎች” እንዲኖሩት በምክረ ሀሳብነት አስቀምጧል። ተቋሙ ከውህደቱ በኋላ ሦስት የቴሌቪዥን እና ሁለት የራዲዮ ጣቢያዎች እንደሚኖሩትም አስፍሯል።
የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ጣቢያ “በዜና፣ በወቅታዊ እና በመዝናኛ” ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ ነባሩ ፋና ቲቪ ለዚህ ተመርጧል። ፋና ቴሌቪዥን ካሉት ጣቢያዎች ውስጥ “ለዜና እና ለወቅታዊ ጉዳዮች አማራጭ” መሆኑ እንዲሁም፤ የጣቢያው የመዝናኛ ፕሮግራሞች “ተመልካች ያላቸው” መሆን ለዚህ ምርጫ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
የመዝናኛ ፕሮግራሞች በዚህ ጣቢያ ላይ የሚተላለፍ ቢሆንም ለመዝናኛ እና ለሲኒማ “ራሱን የቻለ ተጨማሪ” የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደሚያስፈልግ ሰነዱ አመልክቷል።
ሁለተኛው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘጋቢ ፊልሞች ላይ የሚያተኩር እንደሚሆነ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል። ዘጋቢ ፊልሞችን ለማስተላለፍ የታቀደው በ“አዲስ ዋልታ” ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲሆን፣ ጣቢያው እንደ አዲስ ስያሜ ሲያገኝ “የዋልታን ስያሜ ፈጠራ በተሞላበት አግባብ መጠቀም” በአማራጭነት ተቀምጧል።
በዋልታ ስር የሚገኘው “አፍሮ ኒውስ” የቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ በአገር ውስጥ እና በውጭ ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ይዘቶችን የሚያስተናግድ እንዲሆን ታጭቷል። ይህ ጣቢያ ይዘቶቹን ሲያቀርብ “ሁለቱም ሚዲያዎች እስካሁን ሲሠሩባቸው የቆዩትን እና አዳዲስ የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን” እንደሚጠቀም ሰፍሯል።
ዋልታ ያስጀመረው “አዲስ ዋልታ ኤፍ ኤም” የራዲዮ ጣቢያ “በውጭ ቋንቋ የኢትዮጵያን መልክ እና ጉዞ ለ24 ሰዓት የሚያሰራጭ” እንደሚሆን ሰነዱ ይጠቅሳል። ፋና ሬዲዮ ደግሞ አሠራሩ ላይ “ሪፎርም” አድርጎ ቀድሞም የነበረውን የአገር አቀፍ እና የክልል ሥርጭቶች ይቀጥላል።
በሁለቱ ተቋማት የተመሠረተው የኹነት አዘጋጁ ተቋም ዋፋ በአንጻሩ፤ “ለግዙፉ ተቋም የኹነት ዝግጅት አቅም በመሆን የይዘት ልህቀትን እና የገቢ አቅምን የሚያሳድግ አንድ ዘርፍ” ሆኖ እንደሚቀጥል በሰነዱ ላይ ተቀምጧል። ዋፋ “ሚዲያው ለሚያከናውናቸው የመዝናኛ፣ የፓናል እና ሌሎች የኹነት ሥራዎች አንድ ጠንካራ ክንፍ እንዲሆን ማድረግ” እንደሚቻል ሰነዱ ላይ ተመላክቷል።
ዋፋ “በአገሪቱ ቁጥር አንድ የኤቨንት አዘጋጅ” እንዲሆንም የታቀደ ሲሆን፣ “ደረጃውን የጠበቀ የድምጽ ማቀነባበሪያ እና መቅረጫ ስቱዲዮ እንዲኖረው” እንደሚደረግም ሰነዱ ያመለክታል። “በኪነ ጥበቡ ዘርፍ በአገሪቱ የመጀመሪያ የሚሆነውን የፊልም መንደር በመገንባት” የሚመሠረተው መገናኛ ብዙኃን ለራሱ ፊልሞች እንዲጠቀም እና ለሌሎች ፊልም ሠሪዎች እንዲያከራይ ማድረግም ከዕቅዶቹ መካከል ነው።
የውህደቱ ሂደት እና ኤፈርት
ባለ 28 ገጹ የውህደት ሰነድ እንደሚያስረዳው የመገናኛ ብዙሃኑ የውህደት ሂደት በበላይነት የሚመራው ከሁለቱም ተቋማት የሚወጣጡ አባላት ባሉት ዐቢይ ኮሚቴ ነው። የዐቢይ ኮሚቴው አባላት የሚመረጡት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሆነ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። ከዐቢይ ኮሚቴው ስር ስድስት የቴክኒክ ኮሚቴዎች እንደሚኖሩም ተጠቅሷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚያስረዱ ኮሚቴዎቹ ተቋቁመው ሥራ ከጀመሩ ሁለት ወር ገደማ ሆኗቸዋል። ኮሚቴዎቹ የሚመሩት የውህደት ሥራ እስከ ቀጣዩ መጋቢት ወር ድረስ እንደሚጠናቀቅ እና ለተቋሙ አዲስ ሥራ አስፈጻሚ ይመረጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከፋና እና ዋልታ አመራሮች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።
የዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ፋንታዬ ጌታነህ በበኩላቸው ውህደትን በተመለከተ “በግላቸው” የደረሳቸው ነገር እንደሌለ እና ከአገር ውጭ እንደነበሩ በመግለጽ ስለ ውህደቱ ማረጋገጫ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ይሁንና ሥራ አስፈጻሚዋ “ገና ነው” ሲሉ ሂደቱ መረጃ መስጠት በሚያስችል ደረጃ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። ወ/ሮ ፋንታዬ አክለውም፤ “[ውህደት] ለጥሩ ነገር የሚደረግ ነገር እንደሆነ ነው ማሰብ የሚቻለው። ለብቻ ከመሮጥ፤ መተባበር መተዘጋገዝ ክንድ ነው። ተጋግዞ መሥራት፣ ተጋግዞ መሄድ የበለጠ አቅም ይፈጥራል” ብለዋል።
የዋልታ እና ፋና ውህደትን አስመልከቶ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ በሂደቱ ላይ “ሊያጋጥሙ የሚችሉ” ተብለው ከተጠቀሱ ተግዳሮቶች መካከል በተቋማቱ ውስጥ ድርሻ ያለው የትግራዩ ኤፈርት ጉዳይ ይገኝበታል።
ከኤፈርት በኩል “ከባለቤትነት ጋር የተያያዘ ፈተና” ሊያጋጥም እንደሚችል የጠቀሰው ሰነዱ፤ “ህወሓት እንደ ድርጅት በሁለቱም ተቋማት ውስጥ በኢንዶውመንቱ በኩል የነበረው የባለቤትነት ጉዳይ እልባት ማግኘቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ሲል የመፍትሔ ሀሳብ አስቀምጧል።
በስሩ 34 ድርጅቶችን የያዘው ኤፈርት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተይይዞ እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ ተቋማቱን እንዳያስተዳድር በፍርድ ቤት እግድ ተጥሎበት ነበር።
በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ድርጅቶቹን ሲያስተዳድር የነበረው የኮሜርሻል ኖሚኒስ እንደነበር የኤፈርት የኢንቨስትመንት እና ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጎይቶም ይብራህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይሁንና ኤፈርት ድርጅቶቹን ከኮሜርሻል ኖሚኒስ ከተቀበለ በኋላ ከነሐሴ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተደጋጋሚ ደብዳቤዎችን ቢጽፍም በዋልታ እና በፋና የአመራር ቦርዶች ውስጥ ሊኖረውን የሚገባውን ውክልና እስካሁን ድረስ አለማግኘቱን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት የተቋማቱን ውህደት በተመለከተ በኤፈርት በኩል የተደረገ ተሳትፎ አለመኖሩን የሚናገሩት አቶ ጎይቶም፤ ይሁንና “በመረጃ ደረጃ” ስለ ጉዳዩ መስማታቸውን ገልጸዋል።
“እንደ ባለድርሻ በብዙኃን ድምጽ (majority) የማይወሰን ነገር አይኖርም ብዬ አላስብም። ግን የባለድርሻ ሀሳቡ መደመጥ አለበት። ሀሳቡ ከተደመጠም በኋላ የራሱን ውሳኔ ሊወስን ይችላል” ሲሉ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማቱ ውስጥ 25 በመቶ ድርሻ ያለው የኤፈርት ሀሳብ ሊካተት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በሁለቱ ተቋማት ውስጥ ሌላኛው ባለድርሻ የሆነው ንጋት ኮርፖሬት በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ስለማሳለፉ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የኮርፖሬቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ስዩም መኮንን፤ “በቅርብ ስላልነበርኩ አላወቅሁም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከቱምሳ ዲቨሎፕመንት ግሩፕ ተመሳሳይ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ያቀረበው ጥያቄ ይህ ዘገባ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኘም።