” የቀረበው ሪፖርት ከእውነት የራቀ ነው ” – የትግራይ ኢንዱስትሪ ቢሮ
በትግራይ ክልል ” ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች ስራ ጀምረዋል ” በሚል ፓርላማ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ሪፖርት ” ከእውነት የራቀ ነው ” ሲል የክልሉ ኢንዱስትሪ ቢሮ ወቀሰ፡፡
ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጥር 28 ቀን 2016 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከ200 በላይ ኢንዱስትሪዎች ስራ ጀምረው ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው ብለው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ፤ በክልሉ ከጦርነቱ በኋላ ስራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎችን በተመለከተ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበላቸው ሪፖርት በተጨባጭ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የተራራቀ ነው ሲል ሪፖርቱን ውድቅ አድርጓል፡፡
የቢሮው ም/ኃላፊ አቶ መሐሪ ገብረሚካኤል፤ ” በአሁኑ ወቅት በክልሉ ስራ የጀመሩት ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ 2 መቶ አነስተኛ ፣ 5 መካከለኛ እንዲሁም 12 ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ናቸው ” ብለዋል።
” ነገር ግን ‘ 2 መቶ 17 ኢንዱስትሪዎች ሁለገብ ድጋፍ ተደርጎላቸው ስራ ጀምረዋል ‘ ተብሎ የተገለጸው ከእውነታው ጋር የተራራቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከፍተኛ የብድር እና የወለድ መጠንን ጨምሮ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር አሁንም ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ስራ እንዳይጀምሩ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ በቀጠለበት አግባብ ሁለገብ ድጋፍ ተደርጓል ለማለት አያስደፍርም ሲሉ ተችተዋል።
በክልሉ በነበረው ግጭት የተነሳ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከነበረበት ከፍተኛ ጉዳት በዘላቂነት እንዲያገግም መሬት የወረዱና ተጨባጭ ድጋፎች እንዲደረጉም ነው የትግራይ ክልል ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐሪ ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የአሀዱ ነው።