February 13, 2024 

ስለ ግብረሰዶማዊነት እና ተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ቋሚ ሲኖዶስ ምን አለ ?

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻና ግብረ ሰዶማዊነትን አስመልከቶ እየተደረጉ ነው ስላላቸው ሁለገብ ተጽእኖዎችንና መመሪያ የማስለወጥ ማግባባቶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

ቋሚ ሲኖዶስ ምን አለ?

– ግብረ ሰዶማዊነት በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለጸው ለአንድ ሀገርና ሕዝብ ከነጎረቤቶቹ መጥፋት ምክንያት የሆነ ተግባር ነው። የሰዶምና ገሞራ በመቅሰፍተ እሳት መቃጠል ከእነርሱ መቀጣትም  አልፎ ላለውና ለመጪው ትውልድ አስተማሪ የሆነ ምልክት እንዲሆን ነው።

– ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ግብረ ሰዶማዊነትን የምትቃወመው ተፈጥሮዋዊ ስላልሆነ ብቻ ሳይሆን በብሉይ  ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ትምህርት በእግዚአብሔር ዘንድ የረከሰ፣ ተቀባይነት የሌለው፣ ኃጢአት በመሆኑ ነው፡፡

– ቅድስት ቤተክርስቲያን ጾታዊ ግንኙነት ወይም የተቀደሰ ጋብቻ በተቃራኒ ጾታዎች ብቻ የሚፈጾም እንዲሆን ታስተምራለች።

– ግብረ ሰዶማዊነት የሰውን ልጅ ተፈጥሯዊ ማንነት የሚንድ፣ መሠረተ እምነትንና ቀኖናን የሚሽር፣ ማኅበራዊ ዕሴት የሚያጠፋ፣ ከሥነ ምግባር መገለጫዎች በአሉታዊ ገጽ የቆመ፣ ሕሊናን የሚያውክ ለትውልድ ጥፋት፣ ለሀገር መውደም ምክንያት የሆነ አጸያፊ ተግባር ነው፡፡

– ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህን ተግባር የሚፈጽሙ ሰዎች ወደ ንሥሓና ድኅነት እንዲመጡ፣ ከሥጋና ከመንፈስ ስብራት እንዲፈወሱ ዘወትር ጥሪ ታደርጋለች እንጅ ማንም ሰው የኃጢአቱ ወይም የርኩሰቱ ተባባሪ እንዲሆን አትፈቅድም።

– በሀገራችን የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በሕግ የተከለከለ ነው።

– ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ተግባር (የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ) በግልጥ በሕገ መንግሥታቸውና በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ድንጋጌዎቻቸው እንደ ጥሩ ነገር እንደ ፍትሐዊነትና አካታችነት በመቁጠር በይፋ የደነገጉ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት መኖራቸው ግልጽ ነው። እነዚሁ ሀገራት ያላቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቅም መከታ በማድረግ በእምነታቸው፣ በባሕላቸው በማኀበራዊ መገለጫቸው ይህን አጸያፊ ድርጊት ፈጽመው በማይቀበሉ የአፍሪካና የምሥራቁ ዓለም ሀገራት ላይ ቢቻል በማግባባት፣ ካልሆነም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጫና በማሳደር እንዲቀበሉ የጥፋት ልማዳቸውን እንዲጋሩ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉትን ድብቅና ግልጽ እንቅስቃሴዎችን እንቃወማለን።

– ይህ ግብረ ርኩሰት በዘመናችን ተቀባይነት እንዲኖረው፣ የሚደረጉ ሁለገብ ማግባባቶች ፣ተጽዕኖዎችና ተያያዥነት ያላቸው ስምምነቶች በሀገራችን መንግሥት ተቀባይነት አግኝተው እንዳይፈጸሙ በጥብቅ እናሳስባለን።

– ከመገናኛ ብዙኃንና ከሌሎችም የመረጃ ምንጮች ለማወቅ እንደተቻለው ግብረ ሰዶማዊነትንና ተያያዥነት ያላቸውን ተግባራት የንግድ፣ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ ፣የፍትሕና የሰብዓዊነት ግንኙነቶች አካል በማድረግ በቃላትና በዓረፍተ ነገሮች ውስጥ አስርጎ በማስገባት አሣሪ ስምምነቶች እንዲፈጸሙ ለማድረግ ያለው ሃደት በአፋጣኝ እንዲፈተሽ። የሀገራችን መንግሥት ብሎም የአፍሪካ መንግሥታት የአህጉራችንን ሃይማኖታዊ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ዕሴቶች አስጠብቀው እንዲቀጥሉ ጥብቅ ጥሪ እናቀርባለን።