February 13, 2024 – Konjit Sitotaw 

የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ፣ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ለመወያየት ወደ ጅግጅጋ እንደሚያቀኑ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንት ቢሂ ከዐቢይ ጋር የሚወያዩት፣ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ በተፈራረሙት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ እንደኾነ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ዐቢይ፣ ትናንት ወደ ሶማሌ ክልል አቅንተው አዲሱን የጎዴ አውሮፕላን ማረፊያ የመረቁ ሲኾን፣ ቢሂ ጅግጅጋ ስለመግባታቸው ግን የወጣ ኹነኛ መረጃ የለም። የመግባቢያ ስምምነቱ ተግባራዊ መኾን ይጀምራል የተባለበት ቀነ ገደብ አልፏል።

ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በደረስኩበት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ ሱማሊያ ያወጣችውን መግለጫ ውድቅ አድርጋለች። ሱማሊያ ስምምነቱን ሕጋዊነት የሌለው በማለት ማጣጣሏ፣ የሶማሌላንድን የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት የሚጥስ ነው ያለችው ሶማሌላንድ፣ ከማናቸውም ነጻ አገር ጋር ስምምነት የመፈራረም መብት እንዳላት ገልጣለች። ሶማሊላንድ ይህን መግለጫ ያወጣችው፣ ተመድና አፍሪካ ኅብረት በመግባቢያ ስምምነቱ ዙሪያ “በመርህ ላይ የተመሠረተ አቋም” እንዲይዙ ሱማሊያ ለጠየቀችበት መግለጫ በሰጠችው ምላሽ ነው።