February 13, 2024 – Konjit Sitotaw

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ማዚ ፒሊፕ የአሜሪካን ኮንግረስ አባል ለመሆን ሊወዳደሩ ነው
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ማዚ ፒሊፕ የሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል የአሜሪካን ኮንግረስ አባል ለመሆን በዛሬው ዕለት በሚካሄደው የማሟያ ምርጫ ላይ የሚወዳደሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ገልጿል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ማዚ የሚመረጡ ከሆነ ኒውዮርክን በመወከል ለኮንግረስ የተመረጡ ሁለተኛዋ ጥቁር ሴት እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተወልደው በአስራ ሁለት ዓመታቸው ከወላጆቻቸው ጋር ወደ እስራኤል ያቀኑት እኚህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በእስራኤል ጦር ውስጥ ብሔራዊ ግዴታቸውን ከተወጡ በኋላ ዩኒቨርሲቲ በመግባት እስከ ማስተርስ ዲግሪ ድረስ መማራቸው ተመላክቷል።
ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ወደ አሜሪካ በማምራት ነዋሪነታቸውን በኒውዮርክ ከተማ አድርገው ንቁ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
እ.አ.አ ከ2021 ጀምሮ የሚኖሩበት ናሳው ካውንቲ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆነው በመመረጥ በማገልገል ላይ የሚገኙት ማዚ ባለትዳርና የሰባት ልጆች እናት መሆናቸውም ነው የተገለፀው።