February 13, 2024 – EthiopianReporter.com 

ሪፖርተር፡- ሆቴል ግንባታ ‹‹ገበታ ለአገር›› እየተባለ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩ ፕሮጀክቶች ጭምር ሲደገፍ ይታያል፡፡ ብዙ ሪዞርቶችና ሎጆች ሲሠሩ ይታያል፡፡ ግን ደግሞ በተቃራኒው ከአገሪቱ ሰላም ዕጦት ጋር በተገናኘ የሆቴል ሥራ ንግድና ገቢ መዳከሙ በሰፊው ይነገራል፡፡ ይህንን እንዴት ነው ማስታረቅ የሚቻለው?  

አትሌት ኃይሌ፡- ይህ በጣም ከባድ ነው፡፡ እንደምትሰማው እንዲያውም በአሁኑ ሰዓት ሆቴሎች እየተዘጉ ነው፡፡ ይህ ማለት ቱሪስት ወይም ተጠቃሚ እየጠፋ ነው ማለት ነው፡፡ ተጠቃሚው በአንድ በኩል በቱሪስትነት ነው የሚመጣው ወይም ደግሞ በስብሰባ ነው የሚመጣው፡፡ የፈለገውን ያህል በወርቅ ለብጠን ሆቴል ወይም ሪዞርት ብንሠራ ሰላም ከሌለ ማንም መጥቶ አይጠቀምም፡፡ ሌላው ይቅርና ኢትዮጵያ ውስጥ ዳይኖሰርስ አለ ብትል እንኳ ሰላም ከሌለ ማንም መጥቶ መጎብኘት አይፈልግም፡፡ የዛሬ ስንት ሚሊዮን ዓመት የጠፋው እንስሳ ዳይኖሰርስ ከእነ ነፍሱ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብትል ሰላም ከሌለ ማንም አይመጣም፡፡ አንድ ቱሪስት መጀመሪያ የሚያስቀምጠው መጀመሪያ ለመቀመጫዬ እንዳለችው እንስሳ ሕይወቱን ነው፣ ይህንን መገንዘብ አለብን፡፡ እንደ ሕዝብም፣ እንደ መንግሥትም ይህንን ካላደረግንና ሰላምን ካላረጋገጥን እንኳን ቱሪስት ለማምጣት ቀርቶ አንተም እኔም ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስም አንችልም፡፡

ከሰሞኑ ዓይተናል ሁላችንም ከአዲስ አበባ ለመውጣት እንኳ እየተሳቀቅን ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው እዚህ ሶዶ በአውሮፕላን የመጣሁት፡፡ በአውሮፕላን መጥቼ አላውቅም፡፡ መኪናዬን እየነዳሁ ከሶዶ አልፌ አርባ ምንጭ ደርሼ ሥራዬን ሠርቼ እመለሳለሁ፡፡ ሰሞኑን ግን ያሠጋል፡፡ በመኪና መሄድ አትችልም አሉኝ፡፡ እንዴት የማውቀውን መንገድ ትከለክሉኛላችሁ ብልም በፍፁም አይሆንም አሉኝ፡፡ ሐዋሳ በአውሮፕላን ለመሄድ ? ኧረ ባካችሁ ግፍ ነው ነበር ያልኩት፡፡ እንዲህ ባለው አስገዳጅ ሁኔታ ግን በመኪና መሄድ የሚቻሉ ቦታዎችን በአውሮፕላን ለመሄድ ትገደዳለህ፡፡ ይህ ሁኔታ ቱሪስቱን ብቻም ሳይሆን፣ የብዙ ሺሕ ሠራተኛ ኃላፊነት ያለበት እንደ እኔ ያለውን ሰው እንቅስቃሴም ይገድባል። ይህንን ቆም ብለን ሁላችንም ልናስብበት ይገባል፡፡

መንግሥትም እንደ መንግሥት፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ቆም ብለን ብናሰብበት፡፡ ካልሆነ ግን በስተመጨረሻ ሁላችንም እንከስራለን፡፡ መንግሥት አባት ነው፡፡ አባት ደግሞ ሁል ጊዜ ልጆችን አስቀምጦ መምከርና መመካከር ነው ያለበት፡፡ ሕፃን ልጅ ወደ እሳት ሲሄድ ኡፍ ነው ይባላል፡፡ ኡፍ ነው እያልን ማስተማር ነው እንጂ አልተመለሰም ብለህ እሳት ውስጥ አትጨምረውም፡፡

እኔ የማወራው እንደ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ እንደ ኢንቨስትመንት ሳወራ ደግሞ ታክስ ከፋይ ነኝ፡፡ መንግሥት ታክስ ከእኔ እንደሚጠብቀው ሁሉ፣ እኔም ደግሞ ከመንግሥት የምጠብቀው ነገር አለ፡፡ እሱም ሰላም ነው፡፡ እኔ ሰላምን የምጠይቀው ለእንግዶቼና ለሠራተኞቼ ነው፡፡ ግን ደግሞ የእኔስ? አሁን እኮ የእኔም የሰላም ዋስትና ችግር ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡ ይህችን ነገር በደንብ ትኩረት ልናደርግባት ይገባል፡፡

እዚህ አገር ውስጥ አንዱ ትልቅ ችግር ምንድነው መሰለህ ? በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ታክስ እየከፈልክ መብትህን ስትጠይቅ በሌላ ይተረጎማል፡፡ ለምሳሌ የእኛ ድርጅቶችን እንመልከት። የኃይሌ ድርጅቶች አሉ፣ የኃይሌና የዓለም ድርጅቶች አሉ፣ የማራቶን ሞተርስ አለ፣ ያያ እና ሌሎች ድርጅቶቻቾን አሉ ፤ እንዲህ እያልን ብንደማምራቸው በእነዚህ ድርጅቶች በዓመት ውስጥ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር እንገብርባቸዋለን፡፡ ይህ የተሠራው ከምንም አይደለም፡፡ የመንግሥት ኃላፊነት ይህንን መጠበቅ ነው፡፡ ይህንን ለምን ተናገርህ ወይም ለምን እንዲህ አልክ የሚለኝ ካለ ደግሞ እኔ በጣም እቸገራለሁ፡፡ ብዙ ዓመታት ማለትም 30 ዓመት በአገሬ ውስጥ ስሠራ አሳልፌያለሁ፡፡ በውጭ ደግሞ አውሮፓንም አሜሪካንም አውቀዋለሁ፡፡ ግዴታዬን መወጣት ብቻ ሳይሆን መብቴንም እፈልጋለሁ፡፡ ግዴታዬን በአግባቡ እወጣለሁ በተመሳሳይ መልኩ መብቴም እንዲከበር እፈልጋለሁ፡፡ መብቴን ለማስከበር ደግሞ አይ አላውቅልህም የሚለኝ ካለ ይህ በጣም ከባድ ነው፡፡