በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የሚገኘው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ለኢንቨስትመንት በመሰጠቱ ዝሆኖቹ ከመጠለያ በመውጣት በ 15 ቀናት ውስጥ የአራት ሰዎችን ሕይወት መቅጠፋቸውን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል።
የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ለኢንቨስትመንት በመስጠቱ በርካታ ዝሆኖች ከመጠለያው ወጥተው በአካባቢው በሠፈሩ ሰዎች ላይ አደጋ እያስከተሉ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆኑ ጥቁር ዝሆኖችን ጨምሮ 31 አጥቢ እንስሳትና ከ220 በላይ የአዕዋፋት ዝርዎች እንዳሉት የሚነገርለት ይህ መጠለያ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ በተደረገው ሕገወጥ ሠፈራ ዝሆኖቹ የሚኖሩበትና የሚራቡበት ቦታ በእርሻ፣ በከሰል ምርት፣ በመንገድና በመኖሪያ ቤት ግንባታ ደኑ በመመናመኑ ዝሆኖቹ ከመጠለያ እየወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በአካባቢው ያላግባብ ቦታ የተሰጠው ግለሰብ ውሉ እንዲቋረጥና ከመጠለያው እንዲወጣ ውሳኔ እየጠበቁ እንደሆነ ገልጸው፣ በሌላ በኩል በአካባቢው የነበሩ ደኖችን መንጥረው ቦታውን ለመጠቀም በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ባለሀብቶች በሕግ እንዲጠየቁ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሐረርጌ ዞንና በሶማሌ ክልል የፋይዳና የረር ዞኖችን የሚያዋስነው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ 6,980 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለው፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ክፍል በእርሻ መሸፈኑም ነው የተገለፀው።
መረጃው የሪፖርተር ጋዜጣ ነው።