February 14, 2024 

በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚቃጣ ጥቃት በአስቸኳይ ይቁም!

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግሥት እና በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ፓርቲያችን ለዚህ ችግር መነሻ ነው ሲል የጠቀሳቸውን ስህተቶች፣ ጥፋቶች እና ድክመቶች የገለጸ ሲሆን ይህንን አለመረጋጋት ተገን አድርገው የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት ላይ ታች የሚሉ የተለያዩ አካላትንም በተለያየ ወቅት አውግዟል፤ በተጨማሪም ለዚህ መፍትሔ ያላቸውን ሃሳቦችን አቅርቧል።

ሆኖም ይህ ግጭት አሁንም የቀጠለ ሲሆን ሀገራችን በተቀበለቻቸው ዓለም ዓቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጭምር ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ ሰላማዊ ዜጎችን በህይወት የመኖር መብት የሚነጥቅ ጥቃት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መፈጸሙን ከሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና ከተለያዩ አካላት ከሚወጡ መረጃዎች መረዳት ችለናል።

ለዚሁ ማሳያ የሚሆነው በቅርብ ጊዜ በሰሜን ጎጃም ዞን በመርአዊ ፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረታ እንዲሁም ምዕራብ ጎጃም ቋሪት ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎች ህይወታቸውን እንዳጡ ከተለያዩ አካላት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ ካደረጋቸው መረጃዎች መገንዘብ ችለናል።

ፓርቲያችን በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርስን ጥቃት ፍጹም የሚያወግዝ እና በአስቸኳይ ሊቆም የሚገባ መሆኑን እየገለጽን አሁንም ቢሆን በዚህ በግጭት ውስጥ እየተሳተፉችሁ ያላችሁ አካላት ለሰላማዊ ንግግር በራችሁን ክፍት በማድረግ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ማኅበረሰቡ እየደረሰበት ካለው ቀውስ እንድትታደጉት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ አሁንም ደጋግመን ጥሪ ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ በማያባራ ግጭት ማህበረሰቡን ለባሰ መከራና እንግልት ከመዳረግ ያለፈ ይህ ነው የሚባል ዘላቂ መፍትሔ ይገኛል ብለን በፍፁም አናምንም፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ትክክለኛውና አዋጩ መንገድ በውይይት፣ በንግግር እና በድርድር በማመን በቁርጠኝነት በመሥራት ብቻ እንደሆነ አሁንም ደግመን ለማስታወስ አንወዳለን፡፡

ፓርቲያችን ኢዜማ በሰላማዊ ዜጎች ህልፈት የተሰማውን ሃዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል። መንግሥት ይህንን ዓይነት ጸያፍ ተግባር የፈጸሙ የጸጥታ አካላትን ለይቶ አስፈላጊውን የፍትህ እርምጃ ወስዶ ውጤቱን ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳውቅ እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
የካቲት 06/2016 ዓ.ም.