የፍትሕ ሚዛን የያዘች ሴት

14 የካቲት 2024

በተለያዩ ምክንያቶች ዜጎች በወንጀል ተጠርጥረው ይያዛሉ።

በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅባቸው ጊዜያት በርካታ ሰዎች በጅምላ ተይዘው ይታሰራሉ።

እነዚህ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦች በመጋዘኖች፣ በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ በሚገኙ ጊዜያዊ ማቆያዎች እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ጭምር እንደሚታሰሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተለያዩ ጊዜያት ባወጧቸው ሪፖርቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።

የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ማንነትን መሠረት ያደረጉ የጅምላ እስሮች መፈፀማቸውን ታሳሪዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲገልጹ ነበር።

በቅርቡም በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ግጭት ከተፈጠረ በኋላ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች እና ሌሎች በርካታ ግለሰቦች በተለያዩ ማቆያዎች ውስጥ ታስረው ይገኛሉ።

እስረኞች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈፀመባቸው እና ለከፋ የጤና እክል የተዳረጉ እንዳሉ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

ለዚህም በርካታ እስረኞች ለተላላፊ በሽታዎች በሚያጋልጥ ሁኔታ በአንድ ክፍል ተፋፍገው መቀመጣቸው፣ ለጤና ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች መታሰራቸው፣ በቂ ምግብ እና ውሃ እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት አለመኖሩ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መስከረም ወር ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ተገደው እንዲቆዩ በሚደረጉበት ‘ሲዳ አዋሽ’ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ በሚገኝ ማዕከል በተስቦ በሽታ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና 190 ሰዎች ሆስፒታል ገብተው እንደነበር መግለጹ ይታወሳል።

ለመሆኑ ተጠርጣሪዎች መታሰር ያለባቸው የት ነው? ሕጉስ ምን ይላል ?

የሕግ ባለሙያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ያሬድ ኃይለማሪያም እንደሚሉት በመደበኛ የሕግ ሥርዓት ውስጥ በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰቦች በሕግ አግባብ የተጠረጠሩበት ወንጀል ተነግሯቸው የፍርድ ቤት ማዘዣ ሊሰጣቸው ይገባል።

ትዕዛዙን ተከትሎም ለምርመራ መወሰድ ያለባቸው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲሆን፣ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ይኖርባቸዋል።

ከዚያም ክስ ከተመሠረተባቸው ጉዳያቸው እስከሚቋጭ፣ ፍርድ ከተላለፈባቸውም ፍርዳቸውን እስከሚጨርሱ መደበኛ በሚባሉ ማረሚያ ቤቶች ብቻ እንዲቆዩ ሕጉ ያዛል።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሰብዓዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ዶ/ር ሚዛኔ አባተም ይህንኑ ነው የሚያስረግጡት።

በመደበኛው የሕግ ሥርዓት አንድ ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ መታሰር ያለበት በሕግ እውቅና በተሰጣቸው የማቆያ ቦታዎች ወይም ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ ነው።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚታየው ከዚህ ለምን ይለያል?

የሕግ ባለሙያው ያሬድ እንደሚሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች የተጠርጣሪዎችን አያያዝ ጨምሮ መደበኛውን የሕግ አካሄድ ስለሚገድቡ የጅምላ እስሮች እንዲፈጸሙ በር ይከፍታሉ።

በአገሪቷ ያሉ መደበኛ እስር ቤቶች እና ማረሚያ ቤቶች ማስተናገድ ከሚችሉት አቅም በላይ የሚታሰሩ ሰዎች ይበራከታሉ።

ከዚህም ባሻገር መደበኛው የሕግ ሥርዓት ስለሚገደብ፣ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ስለማይቀርቡ እና የተፋጠነ የሕግ ሥርዓት ስለማይኖር የእስረኞች ቁጥር የሚቀንስበትም ዕድል የለም።

በመሆኑም በሚፈጠረው መጣበብ ምክንያት ተጠርጣሪዎች በተገኘው ክፍት ቦታ ሁሉ እንዲታሰሩ የማድረግ አጋጣሚ ይፈጠራል ይላሉ የሕግ ባለሙያው።

ኢሰመኮ በቅርቡ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ የታሰሩ የምክር ቤት አባላትን እና ሌሎች ግለሰቦችን በጎበኘበት ወቅት ባጋጠመ ‘ጥበት’ ምክንያት ግለሰቦቹን ወደ አዋሽ መውሰድ እንዳስፈለገ በፖሊስ ተገልጾልኛል ብሎ ነበር።

ሆኖም እንዲህ ዓይነት እስሮች ከቦታ መጣበብ በላይ ሌላ ዓላማ ያዘሉ ናቸው ይላሉ አቶ ያሬድ።

“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደነገገ ማለት መደበኛ የሆነው የሕግ ሥርዓት የማይሠራበት አውድ መፈጠሩን የሚገልጽ ነው” የሚሉት ባለሙያው፣ ሕጎች እና ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ማየት የተለመደ እንደሆነ ይናገራሉ።

ተጠርጣሪዎችን ምቹ ባልሆነ ቦታ ወስዶ በማሰር ሕክምና በማያገኙበት፣ በቂ ምግብ እና ውሃ በሌለበት፣ በቤተሰብ በማይጎበኙበት፣ የሕግ አገልግሎት በማያገኙበት ለመቅጣት መንግሥታት አጋጣሚውን ይጠቀሙበታልም ይላሉ።

በ1997 ዓ.ም. የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ከታሰሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች አንዱ እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ ያሬድ፣ ዝዋይ ውስጥ በጣም ጠባብ በሆነ ከቆርቆሮ የተሰራ መጋዘን ውስጥ ወደ 300 ሰዎች ተፋፍገው የቆዩበትን አጋጣሚን ለአብነት ይመዛሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ክፍል ውስጥ እስረኞች እግራቸውን መዘርጋት ስለማይችሉ ቁጭ ብለው ነበር ሌሊቱንም ቀኑንም የሚያሳልፉት።

“ከመተፋፈጉ የተነሳ ከእስረኞቹ በሚወጣው ትንፋሽ የሚወረዛው የቆርቆሮ ጣሪያ መልሶ ውሃ ያዘንብ ነበር” ብለዋል።

በዚህም የተለያዩ ወረርሽኞች ተከስተው ብዙ እስረኞች መታመማቸውን እና ሕይወታቸው ያለፈም እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

ዶ/ር ሚዛኔም በተለያዩ ጊዜያት አስገድዶ መሰወር የሚመስሉ ሁኔታዎች ሲከሰቱ እንደነበር ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ሲገልጽ መቆየቱን አውስተዋል።

ሆኖም በመደበኛው የሕግ ሥርዓትም ሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የታሳሪዎችን ሕይወት አደጋ ላይ መጣል እና ማሰቃየት አይፈቀድም።

እስረኞች በወታደሮች ቁጥጥር ሥር ሆነው የሚያሳይ ምስል

የእስር ቤቶች መጣበብ ምን ያመለክታል?

የሕግ ባለሙያው አቶ ያሬድ ‘ጥበት’ የቀውስ ምልክት እንደሆነ ይናገራሉ።

“የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ እንዳለ እና መንግሥት ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችንም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታዎችን በአግባቡ እየተወጣ አለመሆኑን ነው የሚያሳየው” ይላሉ።

በየትኛም አገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአጭር ጊዜ ነው መታወጅ ያለበት የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ ወታደራዊ የሚመስል የአፈና መዋቅር መዘርጋት ማለት እንደሆነ ያስረዳሉ።

በዚህም መንግሥት “ያበጠ የፖለቲካ ትኩሳትን ለማስተንፈስ” የሆነ ቦታ የተፈጠረን ችግር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ እንደ መልካም አጋጣሚ ይጠቀምበታል ሲሉም ይወቅሳሉ።

ባለሙያው እንደሚሉት በኢትዮጵያ ሕግ የእስረኞች ማቆያ ቦታ ስፋት ከእስረኞች ቁጥር ጋር ተመጥኖ የተቀመጠ ነገር የለም።

ልክ እንደ ሌሎች አገራት ስንት ካሬ እስር ቤት ውስጥ ምን ያህል እስረኞች መቆየት እንዳለባቸው በዝርዝር አይገልጽም።

ሆኖም የአስቸኳይ ጊዜ ወቅቶችን ጨምሮ በማንኛውም ሁኔታ እስረኞች ለጤናቸው አደገኛ የሆነ እና ለሰው ልጅ ክብር ከሚገባው ውጭ በሆነ መጥፎ አያያዝ ውስጥ መያዝ እንደሌለባቸው ያስቀምጣሉ።

ለበሽታዎች በሚያጋልጡ፣ በቂ የምግብ አቅርቦት እና ሕክምና በሌለበት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲታሰሩ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችም ሆኑ ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድም።

በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ሰዎችን ማሰርም ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የለውም።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የወታደራዊ እስረኛ፣ የጦር ምርኮኛ ወይም ጉዳያቸው በወታደራዊ ፍርድ ቤት የሚታዩ ሰዎች ሲሆኑ ብቻ ነው በወታደራዊ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው የሚታየው።

“ሰላማዊ ሰዎችን ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ማሰር የማሰቃየት ተግባር አለው” የሚሉት አቶ ያሬድ፣ በእነዚህ ካምፖች ውስጥ እስረኞች ተላልፈው የሚሰጡት እስረኞችን እንዲይዙ አሊያም እንዲቆጣጠሩ ከተፈቀደላቸው አካላት ውጪ ስለሚሆን ለብዙ ስቃዮች እንደሚዳረጉ ይናገራሉ።

በተጨማሪም በካምፖቹ ውስጥ ወታደራዊ ስፖርቶች እንደ ማሰቃያ ተግባራዊ ይሆናሉ።

ከዚህ ቀደም በአገሪቷ የተከሰቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ የታሰሩ ግለሰቦችን ጠጠር በተነጠፈባቸው ቦታዎች ላይ በጉልበታቸው እየዳሁ እንዲሄዱ እና ልብሳቸውን አውልቀው እንዲንከባለሉ በማድረግ ወታደራዊ ሥልጠናዎች በቅጣት መልክ ተቀይረው የማሰቃየት ተግባር ሲፈጸምባቸው እንደነበር አቶ ያሬድ ያወሳሉ።

አንድ ተጠርጣሪ መያዝ ያለበት በማን ነው ?

በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀባቸው ጊዜያት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች የመያዣ ትዕዛዝ ባልያዙ እና ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ለማሳየት ፈቃደኛ ባልሆኑ ሲቪል በለበሱ ሰዎች እንደተያዙ ሲናገሩ ይሰማል።

ዶ/ር ሚዛኔ እንደሚሉት ሕግ እና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ያለው የፖሊስ አካል ሲሆን፣ ግለሰቦች በወንጀሎች ተጠርጥረው በተለያዩ ሰዎች ቢያዙ እንኳን ወዲያው ለፖሊስ ተላልፈው መሰጠት አለባቸው።

እነዚህ የሰለጠኑ የፖሊስ አካላት ናቸው ጉዳዩን መያዝ ያለባቸው እና የምርመራ እንዲሁም ፍርድ ሒደቱን መከታተል የሚኖርባቸው።

በየትኛውም ሁኔታ አንድ ተጠርጣሪ በፀጥታ አካላት ሲያዝ ምክንያታዊ ጥርጣሬ መኖር እንዳለበትም ዶ/ር ሚዛኔ ያስረዳሉ።

ሆኖም በአስቸኳይ ጊዜ ወይም በተለያዩ አውዶች ውስጥ የተለያዩ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ተጠርጣሪዎችን የሚይዙባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ይጠቁማሉ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መጣበብ እና መሸራረፍ አጋጣሚን የሚፈጥር መሆኑን ብዙ ጊዜ መገንዘባቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ሚዛኔ፣ በመንግሥት አካላት የሚወሰዱ እርምጃዎች ተመጣጣኝነታቸው፣ ተገቢነታቸው፣ ሕጋዊነታቸው እና አስፈላጊነታቸው መጤን እንዳለበት ያሰምሩበታል።

ለተጨማሪ አራት ወራት በቅርቡ በተራዘመው እና በአማራ ክልል በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመዲናዋ አዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች በሚገኙ ማቆያዎች በርካታ እስረኞች ታስረው ይገኛሉ።

ምን ያህል ተጠርጣሪዎች ታስረው እንደሚገኙ በመንግሥት በኩል የተገለጸ አሃዝ የለም።

የኢሰመኮ ባልደረባ ዶ/ር ሚዛኔም የታሰሩ ሰዎች ትክክለኛ አሃዝ ማወቅ እንዳልቻሉ ገልጸው፣ በርካታ ሰዎች እንደታሰሩ፤ ነገር ግን የተፈቱ እንዳሉ እንደሚታወቅ ገልጸዋል።

በእስረኞች ላይ ደረሰ የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ በተደጋጋሚ ለሚቀርበብት ክስ መንግሥት የሰጠው ምላሽ የለም።

ቢቢሲም በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት አስተያየትን ለማካተት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።