
February 14, 2024
የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት በግንቦት 2015 ዓ.ም. ለፀደቀው፣ ‹‹የግብርና ምርት ውል (Contract Farming)›› አዋጅ ማስፈጸሚያ የሚሆን ረቂቅ መመርያ አዘጋጀ፡፡
በግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ዕውቅና ተሰጥቶት የተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ስድስት ክፍሎች ሲኖሩት፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፀድቆ በፍትሕ ሚኒስቴር ከተመዘገበበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ሪፖርተር ያገኘው ረቂቅ ያሳያል፡፡
በረቂቁ በተለያዩ ክፍሎች ከተጠቀሱት መካከል በግብርና ምርት ውል ዓይነትና በሦስተኛ ወገን የሚሰጥ የድጋፍ ዓይነትና የአፈጻጸም መሥፈርቶች፣ በምርት ርክክብ ጊዜ በውሉ ከተገለጸው በላይ ዋጋ ሲጨምርና ሲቀንስ ስለሚደረጉ ማሻሻያዎች፣ ከአቅም በላይ የሆነ ኃይል ሲፈጠር የማሳወቂያ ሒደት አፈጻጸምና የተለያዩ ድንጋጌዎች ይዟል፡፡በምርት ርክክብ ጊዜ በውሉ ከተገለጸው በላይ ዋጋ ሲጨምርና ሲቀንስ የሚደረጉ ማሻሻያዎች በተመለከተ በአምራችና በአስመራች ውል ላይ የተቀመጠ ማሻሻያ ካለ፣ በውሉ መሠረት ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ረቂቅ መመርያው ይገልጻል።በተጨማሪም የዋጋ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ዝርዝር ውል ወቅት ካልሰፈረ በወቅታዊ ዋጋ ላይ ልዩነት ሲኖር ሁለቱ ወገኖች በመነጋገር፣ ወይም ሁለቱንም በሚወክል አደራዳሪ አማካይነት ስምምነት ማድረግ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡ በሁለቱም መንገዶች ስምምነት ካልተደረገ ተደራዳሪዎቹ የየራሳቸውን አንዳንድ ሰው መርጠው የሚመለከተው አካል እንዲያደራድራቸው ለማድረግ ጥረት ማድረግ፣ እንዲሁም በሁሉም መንገዶች ካልተስማሙ በአዋጁ መሠረት በፍርድ ቤት ዳኝነት ምላሽ እንደሚያገኙ ረቂቁ ያብራራል።አምራች በአስመራች የተሰጠውን የግብርና ቴክኖሎጂ መጠቀም በመተው ከውሉ ውጪ ሌላ የተጠቀመ ከሆነ፣ በተሰጠው የቴክኒክ ድጋፍ መሠረት ሳይጠቀም ሲቀር፣ ምርቱን ከሰበሰበ በኋላ ሆን ብሎ ለራሱ ሲያስቀር ወይም ለሌላ ወገን ሲሸጥ፣ በአስመራችና በአምራች ውል የተጠቀሱና በአምራቹ ሊተገበሩ የሚገባቸው ሌሎች ጉዳዮች ሳይተገበሩ ሲቀሩ አምራቹ ውል ጥሷል ተብሎ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ይገልጻል፡፡በግብርና ምርት ውሉ መሠረት ጥራትን መጠበቅ የሚያስችሉ ግብዓቶች ለአምራቹ ማቅረብ ካልቻለ፣ በግብርና ምርት ውሉ መሠረት ጥራትን መጠበቅ የሚያስችል የቴክኒክ ድጋፍ ለአምራቹ ሳይሰጥ ሲቀር፣ ያልተፈቀደ ወይም ጊዜ ያለፈበት ወይም በግብርና ምርት ውሉ ያልተጠቀሰና የግብርና ምርቱን ጥራት የሚለውጥ ኬሚካል ከተጠቀመ፣ በውሉ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ተገኝቶ ምርቱን ከአምራቹ ባለመረከቡ በሚደርስ የምርት ጥራት መጓደል፣ ሌሎች ጥራትን ለመጠበቅ የሚያስችሉና በግብርና ምርት ውሉ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ሳይፈጽም ቢቀር አስመራቹ ውል እንደ ጣሰ ተቆጥሮ ኃላፊነት ይወስዳል ሲል ረቂቁ ያብራራል፡፡በረቂቅ መመርያው የተገለጹ ድንጋጌዎችን የሚጥስ ግለሰብ ላይ ከሚወሰዱ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች መካከል አስመራች በአምራቹ ላይ ላደረሰው ጉዳት በውላቸው ላይ በተገለጸው መሠረት ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍል ማስደረግ፣ አምራቹ አነስተኛ ይዞታ ያለው አርሶ/አርብቶ አደር ከሆነ በግብርና ውል መሠረት በሚደረገው የአምራችና የአስመራች ግንኙነት፣ በጽሑፍ በሚገለጽ የተወሰነ ጊዜ ከግብርና ምርት ውል አሠራር እንዳይሳተፍ ማድረግ፣ አምራቹ ሰፊ እርሻ ያለው ከሆነ በአስመራቹ ላይ ላደረሰው ጉዳት በውላቸው ላይ በተገለጸው መሠረት ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍል ማስደረግ፣ አስመራቹ ወይም አምራቹ አግባብ ካለው አካል ሊያገኝ ይችል የነበረውን ድጋፍ ወይም ማበረታቻ አንዲያጣ ማድረግ፣ እንዲሁም በሦስተኛ ወገን ላደረሰው ጉዳት በውላቸው ላይ በተገለጸው መሠረት ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍል ማስደረግ የሚሉ ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል፡፡ በተጨማሪም ዕርምጃ የሚወስደው አካል ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት የተፈጸመው ድርጊት የግብርና ምርት ውልን፣ አዋጁንና መመርያውን ያልተከተለ መሆኑና ሌላኛውን ወገን የጎዳ መሆኑ በገለልተኛ አካል በጥናት አስቀድሞ ማረጋገጥ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የተዋዋይ ወገኖችን ወይም የተዋዋይ ሦስተኛ ወገንን የመደራደር መብት አለመጣሱን ማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለሚመለከተው ተዋዋይ ወይም ሦስተኛ ወገን አስቀድሞ ቅሬታውን በጽሑፍ መግለጽ ያለበት መሆኑን ረቂቅ መመርያው ይገልጻል፡፡አርሶና አርብቶ አደሩን ከአስተማማኝ ገዥዎች ጋር በማገናኘትና ጠንካራ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር በመቅረፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ትልቅ ሚና ይጫወታል የተባለ የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የወጣው የግብርና ምርት ውል (Contract Farming) አዋጅ፣ ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ ይታወሳል፡፡በአዋጁ መሠረት ሁለት የግብርና ምርት ውል ዓይነቶች ሲመራ፣ የመጀመሪያው አስመራች ከአምራቹ ጋር የሚዋዋለው የልማትና ምርት ግብይት ውል ሲሆን፣ ሁለተኛው የምርት ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎችና ጅምላ ነጋዴዎች ከግብርና ምርት አምራቾች ጋር የሚያደርጉት የምርት ግብይት ውል ነው፡፡