

February 14, 2024
እሑድ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከታላላቅ አገራዊ ክንውኖች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ይህንን መሰል የታሪክ ማስታወሻ በታላቅ ክብር ተገንብቶ ለምረቃ ሲበቃ፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በጋራ ዕውቅና ሊቸሩት የሚገባ እሴት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ለታላቁ የዓድዋ ድል ክብር የሚመጥን መታሰቢያ ላለፉት 127 ዓመት ሳይኖር ቆይቶ በ128ኛ ዓመቱ ዕውን ሲደረግ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የሚኮሩበት መሆን ይኖርበታል፡፡ የዓድዋ ድልን የሚያህል ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የጀግኖች ኢትዮጵያውያን የመስዋዕትነት ዓርማ፣ በታላቅ ክብርና ሞገስ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ሲቆምለት ደስታው የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆን አለበት፡፡ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎችና የሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ዕምብርት ላይ ይህንን የመሰለ ታሪክ ዘካሪ ቋሚ መታሰቢያ ተገንብቶ ሲመረቅ ከደስታ በተጨማሪ ተስፋ ይሰጣል፡፡ ይህ ተስፋ ታሪክን መዘከር ብቻ ሳይሆን፣ በማያግባቡ የታሪክ ትርክቶች ምክንያት እየደረሱ ያሉ ጥፋቶችን ያርማል ተብሎ ይታሰባል፡፡
የዓድዋ ድል በተዘከረ ቁጥር መላ ኢትዮጵያውያን የእምነትና የብሔር ልዩነት ሳያጋድጋቸው በአንድነት ታሪክ የሠሩበት መሆኑ ይወሳል፡፡ ይህ ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችና በቅኝ አገዛዝ ይማቅቁ ለነበሩ ሁሉ ታላቅ መነቃቃት የፈጠረ ድል፣ ያለፈውንም ሆነ የአሁኑን ትውልድ ከመጪው ትውልድ ጋር የሚያገናኝ የጋራ ድልድይ የሆነ ማስታወሻ ሲገነባለት ከደስታና ከተስፋ በተጨማሪ የራስን ድርሻም መመርመር ያስፈልጋል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የኢትዮጵያውያንን የጋራ መስዋዕትነት ታሪክ ከመዘከርና ከማስተዋወቅ በተጨማሪ፣ ለአንድነትና ለአገረ መንግሥት ግንባታ ፀር የሆኑ ትርክቶችን ፈር በማስያዝ ዘመን ተሻጋሪ ማኅበራዊ ትስስርን ማጠናከር ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ በሁሉም ጎራ የተሠለፉ ኢትዮጵያውያን የጋራ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከልዩነቶቻቸው ይልቅ አገራቸውን አስቀድመው ያንን የመሰለ ታሪክ በታላቅ መስዋዕትነት ሲጽፉ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሥልጣኔ አውቀናል በቅተናል የሚለው ትውልድ አባላት መስከን አቅቷቸው ሲጫረሱ ታሪክም ሆነ መጪው ትውልድ ይፋረዳሉ፡፡በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተቀናብሮ በቀረበው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ምናባዊ መልዕክት፣ ‹‹ያ ሁሉ ጦር አስተዳደራችን ተመችቶት እንዳይመስልህ፣ አገሬን ብሎ ነው የዘመተው፡፡ ሁሉ ነገር በእጁ ሁሉ ነገር በደጁ ሆኖለት አይደለም የዘመተው፣ ስለማያኮርፍ ነው የዘመተው…›› ያሉት ልብ ሊባል የሚገባው ቁምነገር ነው፡፡ ምንም እንኳ ምናባዊ መልዕክት ቢሆንም ይህ ጉዳይ በብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ የሚመላለስ እውነት መሆኑን ግን መካድ አይቻልም፡፡ በአገር አስተዳደር ጉዳይ ያልተመቸው ሁሉ በጥይት በሚፋጅባትና በሳንጃ በሚሞሻለቅባት የአሁኗ ኢትዮጵያ፣ ከቅርብ ቤተሰብ አባል እስከ ዘመድ ወዳጅ ድረስ በሰላም ዕጦት እየደረሰ ያለው ዕልቂት ከብዙዎች የትውስታ መዝገብ ውስጥ አይጠፋም፡፡ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ ነውር ተደርጎ ለትልቁም ለትንሹም ችግር ጠመንጃ መነቅነቅ በተለመደባት አገር ውስጥ፣ የዓለም ግፉአኖች የነፃነት ዓርማ የሆነው ታላቁ የዓድዋ ድል ጭምር ከመወዛገቢያነት አልፎ በርካታ ችግሮች መድረሳቸው የማይረሳ አሳዛኝ ትዝታ ነው፡፡ኢትዮጵያውያን ዓለምን ያስደነቀ ታሪክ ሠርተው ካለፉ ከመቶ ዓመታት በኋላ ያለው መከራ ብዙ ያሳስባል፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ምናባዊ መልዕክት እንደተነገረው ከ100 ሺሕ በላይ ጀግኖች ኢትዮጵያውያንን፣ ያንን ለመሰለ አኩሪ ታሪክ ለሚያሠራ መስዋዕትነት ያግባባው ከቋንቋ በላይ የአገር ፍቅር ነበር፡፡ የእነሱ ዘመን ከመገናኘት ለመለያየት፣ ከመቀራረብ ለመራራቅ የተመቸ እንደነበር መገለጹ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የምናባዊ መልዕክቱ ጭብጥ የጊዜውን ሁኔታ በታሪክ ተከትቦ እንዳየነው በሚገባ የሚያብራራ ሲሆን፣ እንደ ዛሬው ቴክኖሎጂ በቀላሉ ተደራሽነት ባልነበረበት ዘመን የኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ተጠራርተው ዓድዋ መዝመት አሁንም ድረስ ያስደምማል፡፡ ምንም ዓይነት የመገናኛና የትራንስፖርት አውታር ባልነበረበት በዚያ ጊዜ፣ ሁሉንም ጀግኖች ያስተሳሰረው የአገር ፍቅር እንደነበር ሲታወስ ልብን ከማሞቅ በላይ ዛሬስ የሚለውን ሞጋች ጥያቄ ይቀሰቅሳል፡፡ ምክንያቱም ይህ ዘመን ቅንነቱ ካለ ለአገር በአንድነት ተሠልፎ በጋራ ለመሥራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ምቹ ነውና፡፡ ችግሩ ግን ለልዩነት ዕውቅና ሰጥቶ ለመቀራረብ ፈቃደኝነት ባለመኖሩ ምክንያት አገር እየደማች ነው፡፡የአገር ጉዳይ ሲነሳ በየዘመናቱ እየመጣ የሚሄድ ትውልድ የራሱን ታሪክ ሠርቶ ያልፋል፡፡ የሚሠራው ታሪክም ዘመኑ በሚጠይቀው ዕውቀት፣ ዕሳቤ፣ የአገር ተጨባጭ ሁኔታና ዓለም አቀፋዊ ጫና ጭምር ነው፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች እንደተባለውም በተገለጸላቸው መጠን ታሪክ ሠርተው አልፈዋል፡፡ የአገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች ጋር በመፋለም አስከብረው ነፃ አገር ለመጪው ትውልድ አስረክበዋል፡፡ እንደሚታወቀው አውሮፓውያን በበርሊን ኮንፈረንስ በወሰኑት መሠረት አፍሪካን ዕጣ ተጣጥለው እንደ ቅርጫ ሲቃረጡ፣ ብቻዋን ቅኝ ገዥዎችን ተፋልማ ያልተደፈረች አገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ይህንን በመሰለ የጀግንነት ተጋድሎ የሚያኮራ ታሪክ ሠርተው ሲያልፉ፣ ተከታዩ ትውልድ እንደተባለው በጎደለው እየሞላ የራሱን ታሪክ መሥራት ይገባው ነበር፡፡ የሚሠራው ታሪክ አኩሪ እንጂ አንገት የሚያስደፋ እንዳይሆንም መጠንቀቅ ነበረበት፡፡ ከዚያ ውጪ ትናንት የጎደለውን ወይም የተዛነፈውን ዛሬ እየሞሉና እያስተካከሉ በዕድገት መራመድ ሲገባ፣ የትናንቱ ትርክት ላይ ተቸንክሮ እግርን መጎተት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ለዘመኑ የዕድገት ደረጃም አይመጥንም፡፡የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተገንብቶ ለምረቃ መብቃቱን አስመልክቶ የተለያዩ ሐሳቦች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እየተንሸራሸሩ ነው፡፡ ሐሳቦቹ በተለያዩ ቅኝቶች ሲቀርቡ ግን ደረጃቸውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ሙዚየሙ ከአራቱም ማዕዘናት ወደ ዓውደ ግንባሩ የዘመቱ ጀግኖች መታሰቢያ እንደ መሆኑ መጠን፣ ወካይ የሆኑ ሐውልቶችም ሆኑ ቅርሶች በተቻለ መጠን ድሉን እንዲመጥኑ ማሳሰቡ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የዓድዋ ድል ሲዘከር ተሳትፎው የጋራ መሆኑ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ስለሚታመን ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉት የፖለቲካ ቁርሾ፣ ቂም፣ ጥላቻና አሉባልታ ለታላቁ የዓድዋ ድል አይመጥኑም፡፡ ኢትዮጵያ በታላቁ የዓድዋ ድል ምክንያት በዓለም አደባባይ አንቱታን ያገኘች ብቸኛ የአፍሪካ አገር ነበረች፡፡ ብቸኛዋ የአፍሪካ አኅጉር የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል፣ ከዚያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባልና የአፍሪካ ኅብረት ምሥረታ ጠንሳሽ ነበረች፡፡ ይህ ሁሉ ክብር የተገኘው በታላቁ የዓድዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ ይህ ታላቅ ድል ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ብለው ያስመዘገቡት ነው፡፡ ይህ ትውልድ እከሌ ከእከሌ ሳይባባል ይህንን ታላቅ ታሪክ ሲዘክር የመግባቢያ መንገዱንም አብሮ ይፈልግ!