የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ ከእጮኛቸው ጋር

ከ 5 ሰአት በፊት

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ ለአራት ዓመት በፍቅር ከቆዩት ጓደኛቸው ጆዲ ሄይደን ጋር መታጨታቸውን አወጁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍቅረኞች ቀን በሚከበርበት ቫለንታይንስ ደይ በልዩ ሁኔታ ዲዛይን ባደረጉት ቀለበት ለጓደኛቸው የታገቢኛለሽ ጥያቄ አቅርበውላታል።

የ60 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና እጮኛቸው የ45 ዓመቷ ጆዲ የተገናኙት በሜልቦርን ከተማ ለንግድ ማኅበረሰቡ ከአራት ዓመት በፊት በተደረገ የእራት ፕሮግራም ላይ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውስትራሊያ ታሪክ በሥልጣን ላይ ሆነው የታጩ የመጀመሪያው መሪ ናቸው።

አንቶኒ አልባኔዝ የመታጨታቸውን ዜናም ከፎቷቸው ጋር አድርገው “እሺ አለች” በሚልም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አጋርተዋል።

“ይህንን ዜና ስናካፍላችሁ በደስታ ተሞልተን ነው። እናም ቀሪ ሕይወታችንን አብረን ለማሳለፍ በጉጉት እየተጠባበቅን ነው። በመገናኘታችን ዕድለኛ ነን” በማለት ጥንዶቹ ባወጡት የጋራ መግለጫ አትተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ባልደረቦችን ጨምሮ፣ የኒውዚላንዱ መሪ ክርስቶፈር ሉክሰን እና ታዋቂው ሼፍ ኒጄላ ላውሰን ለጥንዶቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ካስተላለፉት ይገኙበታል።

“ፍቅር ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። ለሁለታችሁም እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀድሞዋ የኒው ሳውዝ ዌልስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ካርሜል ቴበት ጋር ለ19 ዓመት ተጋብተው የቆዩ ሲሆን በዚህም የትዳር ቆይታቸው የ23 ዓመት ልጅ አፍርተዋል። ጥንዶቹ የተለያዩት በአውሮፓውያኑ 2019 ነበር።

የሌበር ፓርቲ መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፋይናንስ ዘርፉ ከሰሩት ጆዲ ጋር ከተዋወቁ ከዓመት በኋላ ለአገሪቱ ብሔራዊ የራግቢ ቡድን ባላቸው የጋራ ፍቅር ግንኙነታቸው መጠናከሩን ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።

ከአራት ዓመታት በፊት በአንድ ዝግጅት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የራግቢ ቡድን የሆነው የሳውዝ ሲድኒ ራቢቶህስ አድናቂ ከናንተ መካከል አለ ወይ ብለው ታዳሚውን በጠየቁበት ወቅት “ራቢቶህስ ከፍ ይበል” በሚልም የአሁኗ እጮኛቸው ጮክ ብላ ተናግራ ነበር።

ጥንዶቹ ግንኙነታቸውን በምስጢር ይዘው የቆዩ ቢሆንም በአውሮፓውያኑ 2022 ጆዲ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻም በመቀላቀል አብራቸው የነበረች ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑም በኋላ አብራቸው ዓለም አቀፍ ጉዞዎችን አድርጋለች።