
ከ 4 ሰአት በፊት
በአሜሪካ ሚዞሪ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ካንሳስ ከተማ በብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን የድል ዝግጅት በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች 21 ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ።
ባለሥልጣናት እንዳሉት ረቡዕ ዕለት በተፈጠረው ተኩሱ ለሕይወታቸው አስጊ የሆነ ጉዳት የደረሰባቸውን ስምንት ሰዎችን ጨምሮ ሌሎች ተጎጂዎች ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።
ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ስምንቱ ሕጻናት ሲሆኑ ጉዳቱ ለክፉ የሚሰጣቸው እንዳልሆነ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
ተኩሱ የተከፈተው የአሜሪካ ብሔራዊ የእግር ኳስ ሊግን ቻምፒዮን ለመለየት በሚደረገው ‘ሱፐር ቦውል’ የ‘ካንሳስ ሲቲ ቺፍስ’ ድልን በማስመልከት በተዘጋጀ የስፖርት እና የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ነው።
በወቅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ዝግጅቱን ለመታደም ተሰባስበው ነበር።
ፖሊስ ከተኩሱ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ሦስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏል።
የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የመጀመሪያው ተኩስ ሲሰማ ‘የካንሳስ ሲቲ ቺፍስ’ ቡድን ተጨዋቾች መድረክ ላይ ነበሩ።
በተኩስ እሩምታው የከተማዋን ከንቲባ እና የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ጨምሮ በትርኢቱ ላይ የተሰባሰቡ ሰዎች ራሳቸውን ለማዳን ሲሮጡ ታይተዋል።
- የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ ሕግን አጸደቀ24 ሰኔ 2022
- የወንጀል ተጠርጣሪዎች መታሰር ያለባቸው የት ነው? በምን ሁኔታስ ሊያዙ ይገባል?14 የካቲት 2024
- ስለ ሬጌው ንጉሥ ቦብ ማርሌይ አራት አስገራሚ እውነታዎች14 የካቲት 2024
የካንሳስ ከተማ የፖሊስ ኃላፊ ስቴሲ ግሬቭስ እንዳሉት ተኩሱ ከተከፈተ በኋላ ፖሊሶች ወዲያውኑ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በቦታው የነበሩ መርማሪዎችም በፍጥነት ምርመራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ክፍሉም ወዲያውኑ ወደ ተግባር በመግባት የተጎዱትን ሲረዱ ነበር ብለዋል።
በዝግጅቱ ያለውን ጸጥታ ለመቆጣጠር ከ800 በላይ ፖሊሶች ተሰማርተው የነበረ ሲሆን የድንገተኛ አደጋ ክፍሉም አስፈላጊ የሆነ ሕክምና ለመስጠት በሥፍራው እንደነበር ተገልጿል።
የከተማዋ ፖሊስ ኃላፊ ግሬቭስ ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ ሕይወቱ ያለፈውን ጨምሮ 22 ሰዎች በተኩስ ሩምታው መያዛቸውን ጠቅሰው፣ ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል።
የአካባቢው የራዲዮ ጣቢያም ሊዛ ሎፕዝ የተባለው ዲጄው በተኩሱ እንደተገደለበት ገልጿል።
ባለሥልጣናት እንዳሉት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአፋጣኝ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ለሕይወታቸው አስጊ የሆነ ጉዳት የደረሰባቸውም በ10 ደቂቃ ውስጥ ወደ ሕክምና ተቋም ማድረስ ተችሏል።
ዕድሜያቸው ከስድስት እስከ 15 የሚሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ስምንት ሕጻናትም በሜርሲ የሕጻናት ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ተገልጿል።
በተኩሱ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች በተጨማሪ ለማምለጥ በመገፋፋት ጉዳት ያጋጠማቸው እየታከሙ መሆኑን በአካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎች አሳውቀዋል።
የከተማዋ ባለሥልጣናት የተጎጂዎችን ስም እንዲሁም በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ምንም ዓይነት መረጃ አላጋሩም።
ሆኖም አንድ የፖሊስ ምንጭ የተፈጠረ አለመግባባት ወደ ወደ ግጭት በማምራቱ የተከሰተ መሆኑን ለቢቢሲ የአሜሪካው አጋር ሲቢኤስ ተናግረዋል። እኝህ ምንጩ እንዳሉት ተኩሱ ከሽብርተኝነት ጋር የተገናኘ አይደለም።
ፖሊስ በበኩሉ የተኩስ ሩምታው የተከፈተበትን ምክንያት እየመረመረ እንደሆነ በመግለጽ የዓይን እማኞች እንዲሁም ክስተቱን በተመለከተ መረጃ ያላቸው ግለሰቦች ለፖሊስ መረጃ እንዲሰጡ ጠይቋል።
የካንሳስ ከተማ ከንቲባ ኪዩንተን ሉካስ በበኩላቸው የተኩስ ድምጹን ሲሰሙ እርሳቸውና ሌሎች በሥፍራው እንደነበሩ ገልጸው፣ ከዚያም እርሳቸው እና ቤተሰባቸው ነፍሳቸውን ለማዳን መሮጥ እንደጀመሩ ተናግረዋል።
“ ከባለቤቴ እና ከእናቴ ጋር በቦታው ነበርኩ። የቡድኑ ተጨዋቾችና አድናቂዎቻቸው ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ነበሩ። ይህ ይከሰታል ብዬ በፍጹም አላሰብኩም ነበር።” ብለዋል ከንቲባው።
የካንሰስ ቺፍስ ድርጅት ባወጣው መግለጫም በክስተቱ ማዘኑን ገልጾ፣ ተጨዋቾቹ ፣ አሰልጣኞቹ እና ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ደኅና መሆናቸውን ገልጿል።
ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ባወጡት መግለጫም በአገሪቷ ያለውን የጦር መሣሪያ ጥቃትን አሳሳቢነት ገልጸዋል።
“ የዛሬው ክስተት ሊያስደነግጠን፣ ሊያሳፍረን ፣ ሊያሸማቅቀን ይገባል” በማለት የጦር መሣሪያ ሕግ መሻሻል እና በአሜሪካ የጦር መሣሪያ መታገድ እንዳለበት ተናግረዋል።