
ከ 6 ሰአት በፊት
ቻይና በሙስና ቀልድ አታውቅም። ሙስና ውስጥ ተዘፍቆ የተገኘን የትኛውንም ባለሥልጣን አይቀጡ ቅጣት ታከናንባለች።
ቀደም ባሉ የቻይና መሪዎች የተጀመረው የፀረ ሙስና ‘ውጊያ’ በአሁኑ የፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ዘመነ መንግሥትም ቀጥሏል።
ሰሞነኛው የፕሬዝዳንቱ የፀረ ሙስና ዘመቻ ከፍተኛ ክብር ካላቸው ታላላቅ ባንኮች እስከ ኑክሌር ኃይል ቢሮ የዘለቀ ነው።
ብዙዎች ይህ ዘመቻ መቼ ያበቃ ይሆን የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። አጭሩ መልስ ደግሞ መቼም የሚቆም አይመስልም የሚል ነው።
ሙስና የቻይና መንግሥታዊ አስተዳደር ማዕከላዊ ትኩረት ነው።
ይህ ትኩረት አንዳንዴ ሥራውን በአግባቡ ያለመሥራት ፍንጭ ያሳየን ሰው እንኳን አይምርም። ሌላ ጊዜ ደግሞ ‘እዚህ ግባ’ የሚባል ጥፋት ያልተገኘባቸውን የማሳወገጃ መንገድ ይሆናል። ዢ ያለ በቂ ምክንያት ሰዎች ላይ ያላቸውን ሥልጣን እንዲጠቁሙ የሚያደርግም ነው።
ሆኖም ነገሩን ከዚህ በተቃራኒ የሚመለከቱት አሉ።
በጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ የቻይና ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊው ፕሮፌሰር አንድሪው ዌንድማን “ምናልባት ዢ ከከፍተኛ ሙስና ጋር በተያያ የተጋነነ ፍርሃት ሊኖራቸው ይችላል። ሆኖም ፍራቻቸው መሠረት የሌለው አይደለም” ይላሉ።
ቀጥለውም “በእርግጥ የሚፈሩት ሙስና እውነት ነው። በሌላ በኩል ለፖቲካዊ ጥቅም እያዋሉት የመሆን ዕድሉም ከፍ ያለ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ያኔ ማኦ የፓርቲው ሊቀ መንበር በነበሩበት ጊዜ ሙስናን መቆጣጠር የሚቻለው ሰዎች ለፓርቲው ያላቸውን ፍቅር በማጎልበት ነው የሚል ፍልስፍና ነበረ።
ቀጥሎም በዴንግ ዣዎፒንግ እና ጂያንግ ዜሚን ዘመነ መንግሥት ደግሞ እሳቤው ተቀየረ። ሰዎች የተሻለ ሕይወት ከኖሩ ወደ ሙስና ስቦ የሚከታቸው ምክንያት ይቀንሳል የሚል ሆነ።
ቀጥለው በመጡት ሁ ጂንታዎ ዘመነ መንግሥት ደግሞ የሰዎች የኑሮ ሁኔታ ቢሻሻልም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚተጉ ሰዎችም ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ተመነደገ።
አሁን ያሉት ፕሬዝዳንት ዢ ወደ ማኦ ዘመነ መንግሥት ፍልስፍና የተመለሱ ይመስላሉ። እሳቸው ሙስና የጋረጠውን ፈተና መቀልበስ የሚቻለው ሰዎች ለፓርቲያቸው ያላቸው ፍቅር ሲጋጋም ነው የሚል እምነት ላይ ደርሰዋል።
ፓርቲው አዲስ የፀረ ሙስና ዘመቻ ጀምሯል። በዚህም የፓርቲውን ሕግጋት የጣሱ ሰዎች ላይ እያንዣበበ ነው።
- ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት ብሪክስ ተግባራዊ ማድረግ የሚፈልገው ምንድን ነው?8 የካቲት 2024
- ቻይና ውበታቸውን ተጠቅመው ከሚያማልሉ ሰላዮች እንዲጠበቁ ዜጎቿን አሳሰበች26 ጥር 2024
- ኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ አገራት መወዳጀት የሚያዋጣቸው ከቻይና ወይስ ከአሜሪካ?16 ጥር 2023
‘ሰዎች በቀላሉ ይሰወራሉ’
በቻይና በየትኛውም ዘርፍ ከፍተኛ ሥልጣን የያዙ ሰዎች አብዛኞቹ የኮሚኒስት ፓርቲው አባላት ናቸው። የፋይናንስ ተቋም፣ የስፖርት ድርጅትም ይሁን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ኃላፊ የሆነ የፓርቲው አባል የመሆኑ ዕድሉ ሰፊ ነው።
አንዴ የፓርቲው አባል የሆነ ሰው ደግሞ በፓርቲው የሥነ ምግባር ደንቦች የመጠየቅ ግዴታ አለበት። ከሙስና ጋር በተያያዘ የሚያሳስበው ጉዳዩ መጠየቁ ሳይሆን፣ ለሰፊ ትርጉም የተጋለጡ እና አንዳንዴም ከግል ስብዕና ጋር ለሚያያዙ ክሶች መጋለጡ አለ።
በዚህ ሰበብ በሚፈራው የፀረ ሙስና ኮሚሽን አማካኝነት ሰዎች በቀላሉ ሊሰወሩ ይችላል።
በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ለጥያቄ ወደ ምሥጢራዊ ቦታ የሚወሰዱ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው ቀድመው እንዲያውቁ መደረግ ይኖርበታል። ይህ ስለመሆኑ ግን ማስተማማኛ የለም።
የሆነ ቀን ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ዕይታ ሊሰወሩ ይችላሉ። ቀጥሎ ገደቡ ለማይታወቅ ጊዜ ያለ ሕግ ከለላ “ለምርመራ” መዳረግ ይኖራል።
ይህ ዓይነቱ እርምጃ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው የጸዳ መንገድ ለመክፈት ያለመ ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሊሆን ይችላል።
በቶሮንቶ ዩኒቨርሲተ የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ላይንቲ ኦንግ እርምጃው “ከአውሮፓውያኑ 1979 ጀምሮ ለቻይና ኢኮኖሚያዊ እድገት ዋነኛው ኃይል የሆነውን በድፍረት አዲስ ነገር እና ሥራን ለመፍጠር የሚከያበረታታውን ሁኔታ እንዲቀንስ” ሰበብ ሆኗል ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አሁን አሁን በቻይና “በጀርባ መንጋለል” የሚል አባባል እጅግ የተለመደ ሆኗል። ይህ ቤት ውስጥ ረጅም ሰዓታት ጌም እየተጫወቱ የሚያሳልፉ ልጆችን ለመግለጽ የሚውል አባባል ነው። አባባሉ ለዚያ ብቻ ግን የሚውል አይደለም።
በመንግሥታዊ ወይም በግል ድርጅቶች ውስጥ ያሉ በሙስና የመጠርጠር ስጋትን ለመቀንስ እና ለመኖር ያህል ብቻ የተሰጣቸው ሥራ ላይ ምንም ሰይጨምሩ እና ሳይቀነሱ የሚሰሩ ኃላፊዎችን ለመግለጽ ይውላል።
እነዚህ ኃላፊዎች ሥራ ፈጣሪዎች አዲስ ነገር ይዘው እንዲመጡ መገፋፋት ወይም በሥራቸው እጅግ ተስፈኛ መሆን በሙስና የመጠርጠር አደጋን ሊያስከትል ስለሚችል ድምጻቸውን አጥፍተው የተሰጣቸችን ብቻ ይሠራሉ።
በዚህ ጉዳይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው በቻይና ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነው የኮሚኒስት ፓርቲ ጋዜጣ የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ዴንግ ዩዌን “ዢ ባለሥልጣናት ንጹህ እና ታታሪ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ” ይላሉ።
“ነገር ግን ዢ ሙስና ላይ ስለሚያተኩሩ ባለሥልጣናቱ በጀርባቸው ይንጋለሉ። በእርግጥ ዢ ይህ እንዲሆን አይፈልጉም። እኔን ጥንክሬ እንደሠራ ካተጋኸኝ እጥራለሁ። ጅራፍ ከበዛብኝ ግን ሥራውን ቀላል አደርጌ ‘በጀርባዬ እንጋለላሁ’” ሲሉ ተናግረዋል።

ትልቅ ገንዘብ፣ ጠቀም ያለ ጉቦ
በቻይና ሰሞነኛ የሙስና ዘመቻ፣ እጅግ የተከበረ ስም ያላቸው የፋይናንሱ ዘርፍ ኃላፊዎች እየታደኑ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ውስጥ በርካታ የቀድሞ የባንክ ሊቃነ መናብርት እና ተቆጣጣሪዎች ጠቀም ያለ ገንዘብ በጉቦ መልክ ተቀብለዋል በሚል ተወንጅለዋል።
ባለፈው ዓመት ብቻ ከ100 በላይ የፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊዎች ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
“በጣም በርካታ አመራሮች ለአስርት ዓመታት በፋይናንስ ዘርፍ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል። ይህንን በአንድ እና በሁለት ዓመት ማጽዳት አይቻልም” የሚሉት ዴንግ “የባንኩ ዘርፍ ያለፈው ዓመት ዋነኛ የሙስና ትኩረት ነበር። በዚህ ዓመት እና በሚቀጥሉት ዓመታትም ትኩረት ሆኖ ይቀጥላል” ሲሉ አክለዋል።
ፕሮፌሰር ዌንድሜን ደግሞ “በባንኩ ዘርፍ ከፍተኛ ሙስና ይጠበቃል። ምክንያቱም ባንኮች ትልቅ ገንዘብ የሚገኝባቸው ተቋማት ናቸው” ይላሉ።
በቻይና ትልቁ ገንዘብ ያለው በባንኮች ዘንድ ይሁን እንጂ ትልቁ ሥልጣን ያለው ጦር ሠራዊት እጅ ውስጥ ነው።
ሕዝባዊው የነጻነት ሠራዊት የቻይና አገረ መንግሥት ጦር አይደለም። ይልቅ የቻይና ፍጹማዊ የኃይል እና ሥልጣን ምንጭ የሆነው ፓርቲን የሚጠበቅ ጦር ነው።
ስለዚህ ከጦር መሳሪያዎች ግዢ ሂደት ጋር በተያያዘ የኑክሌር ሮኬት ኃይልን የሚመሩትን ጄኔራሎች እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሊ ሻንጉፉን በማስወገድ የተወሰደው እርምጃ የቻይና የሙስና ትግል ምን ያህል መራራ እንደሆነ የሚያመለክት ነው።
መሠረቱን ሞንትሪያል ያደረገው የጂኦ ፖለቲክስ አማካሪ ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ስለሁኔታው ለቢቢሲ ሲናገሩ “እኛ የምናወራው ስለተመዘበረ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ ለፓርቲው ጦር ስለተሸጡ ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎችም ነው” ብለዋል።
በሊ ኩን የዉ የሕዝብ ፖሊሲ ጥናት ትምህርት ክፍል ውስጥ የሚሰሩት ፕሮፌሰር አልፍሬድ ዉ በኒውክሌር ኃይል ወስጥ የሚኖረው ሙስና ለዢ ትልቅ ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ።
“በሮኬት ኃይሉ ትልቅ ተስፋ ነበረው” የሚሉት ፕሮፌሰሩ ጠንካራ ሮኬት መኖር ወደፊት ከታይዋን ጋር ለሚኖር ጦርነት አስፈላጊ እንደሆነ ዢ ያምናሉ ሲሉ ጠቅሰዋል።
ቢቢሲ ዢ በፓርቲያቸው ጦር ላይ የሚያደርጉት ለውጥ ታይዋንን በኃል ለመጠቅለል የሚያድረጉትን ዕቅድ ሊያጓትተው ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ የሰነዘረላቸው ፕሮፌሰር ሲመልሱ “እርግጥ ነው!” የሚል አጭር መልስ አስከትለዋል።
ሆኖም የዢን የፀረ ሙስና ዘመቻ የሚከታተሉ ተንታኞች በቻይና የሚደረገው ‘የሙስና ትግል’ ስልታዊ ለውጥ የማያመጣ ስለሆነ ችግሩን ዘላቂ በሆነ መንገድ መፍታቱ ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

ፕሮፌሰር ፓያቴ “ፓርቲው የመቆጣጠሪያ ሥርዓት እና ደንብ ለመዘርጋት ከሚያደርገው ጥረት በተቃራኒ ሙስናን ማስቀረት አልቻለም። እስካሁን ፓርቲው የአገሪቱን መዋቅር የሚቆጣጠር ብቸኛ ኃይል ሆኖ የመሠረተ ልማት ሙስናን መቆጠጠር ተስኖታል” ይላሉ።
በርካታ አገራት ትክክለኛ እና ገለልተኛ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲያቋቁሙ፣ ግልጽነትን ሲያሳድጉ፣ የሕግ የበላይነትን ሲያሻሽሉ እንዲሁም ሙስናን እንዲዘግቡ ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃንን ሲያበረታቱ ቻይና አንዱንም አላደረገችም የሚል ትችት ይቀርብባታል።
በምትኩ የሁሉም ነገር ምንጭ ኮሚኒስት ፓርቲው ነው። ቢሆንም ግን በሙስና የተነከሩ ሰዎችን ከማሰስ ቻይና ፈጽሞ ቦዝና አታውቅም።
ሌላው ለሙስና ያለው ሕብረተሰባዊ አመለካከት ቀስ በቀስ መቀየር ይገባዋል የሚለው ነው። ፕሮፌሰር ዌድማን “ሙስናን መቀነስ እና መቆጣጠር ሕጎችን በማሻሻል ብቻ አይመጣም። ይልቅስ በሕብረተሰቡ እና በመጪው ትውልደ ሙስና ሊቀጥል የማይገባው ተግባር የሚል ጥልቅ መረዳት ሊኖር ይገባል” ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ዢ የፀረ ሙስና ጅራፍ አንዳንድ ባለሥልጣናት አፋቸው እንዲሸበብ የፍርሃት ምንጭ ሆኗል። በተለይ ያለፍርሃት ሀቀኛ መረጃ እንዲሰጡ የሚጠበቁ የቅርብ ባለሥልጣናት ከዚህ በተቃራኒው እየሄዱ ይገኛሉ።
ይህ ሁኔታ ሦስት ዓመት ከቆየው የኮቪድ ቀውስ በኋላ ለብዙዎች ግልጽ ሆኗል። የቀረው የዓለም ክፍል ከቫይረሱ አገግሞ ዳግም በሩን ሲከፍት ቻይና በጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ ተከርችማ ነበር።
“በዢ ዙሪያ ጎበዝ ሰዎች እንዳሉ ምንም ጥርጥር የለውም” የሚሉት ፕሮፌሰር ኦንግ “ትልቅ ተቃውሞ እስኪገጥም ድረስ የኮቪድን ደረጃ ወደ ዜሮ ማውረድ ብሎ ማዘዙ ለእኔ፣ ኢኮኖሚውን የሚረዱ ሰዎች የእሱን ጆሮ እንዳላገኙ ነው የሚያሳየኝ” ሲሉ ገልጸዋል።
ሌሎች ደግሞ ፕሬዝዳንት ዢ ጭንቅላታቸውን በይሁንታ ብቻ በሚነቀንቁ ሰዎች የተከበቡ ናቸው የሚል ስጋት አላቸው።
“እዚህ ጋር ዢ ግልጽ እና እውነተኛ ምክር አይፈልግም። የሚፈልገው ታማኝነትን ነው” የሚሉት ደግሞ ፕሮፌሰር ፓያቴ ናቸው።
“ዢ ሥልጣን ብቻ በሚፈልጉ ካድሬዎች እጆች ላይ የወደቀ ይመስላል። በፓርቲው የቀድሞ ታሪክ ካድሬዎች ላለመገለል እና የፓርቲውን የላይኛውን አካል ውስጠ-ነገር ለማወቅ ሽንገላን እንደሚመርጡ ዢ ያውቀል” ሲሉ አክለዋል።
በሆነ መጠን በከፍተኛው አመራር ውስጥ ያሉ “ነብሮችም” ይሁን ታች ያሉ ባለሥልጣናት ሙስና ውስጥ ገብተዋል ተብሎ ይታመናል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በየትኛውም ምክንያት ተነጥለው የወጡት የፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ስጋት ናቸው የሚል ጥርጣሬን ያስከትላል።
በዚህ የፀረ ሙስና ዘመቻ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች እንደተቀጡ ይገመታል። በዚህ ቅጣት አንዳንዶች በማስጠንቀቂያ ሲታለፉ ሌሎች ደግሞ ከባድ የእስር ቅጣት ተላልፎባቸዋል። የተቀሩት ደግሞ የመጨረሻውን ቅጣት በሞት ተቀብለዋል።
ይህ እርምጃ ለአገሪቱ የተሻለ አስተዳደር ምክንያት ሆኗል ብለው የሚያምኑ እንዳሉ ሆነው፣ የፓርቲው የጎደፈ ስም ወደ ሕዝቡ ዘልቆ እንዲገባ እያደረገ እንደሆነ የሚታያቸውም አሉ።
የፀረ ሙስና ዘመቻው ማለቂያ ያለው አይመስልም የሚሉት ፕሮፌሰር ዌንድሜን፣ ሁኔታው በሕዝቡ ውስጥ አለመተማመንን እንደፈጠረ ያነሳሉ።