
15 የካቲት 2024, 15:19 EAT
የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ውስጥ ባለ የደኅንነት ስጋት ምክንያት ማንም ሰው የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) እንዳያደርግ ክልከላ ጣሉ።
የዋና ከተማዋ አስተዳደር ቃል አቀባይ ሳልህ ዲሬ እገዳውን በተመለከተ እንደተናገሩት፣ የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛው ጭምብልን ወንጀለኞች ማንነታቸውን በመሸፈን ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመፈጸም እያዋሉት በመሆኑ ነው ጥቅም ላይ እንዳዕውል ክልከላ የተጣለው።
ከሦስት ዓመት በፊት በመላው ዓለም ተከስቶ ዋነኛ የጤና ስጋት የነበረውን ኮቪድ 19 ተከትሎ ነበር ማስኮች በሁሉም ሰው በስፋት ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩት።
በሶማሊያ ዋና ከተማ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ያሉ የሽብር ጥቃቶች እና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶችን ለመቆጣጠር በሚል ነው የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት አሁን ላይ ማስኮችን መጠቀም ያገዱት።
ከዚህ በተጨማሪም ባለሥልጣናቱ በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት መገልገያዎች ላይ ኮፍያ ማድግ እና የጦር መሳሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስን ሕገ ወጥ አድርገውታል።
- ሞቃዲሾ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት የአረብ ኤምሬትስ እና የባህሬን የጦር መኮንኖች ተገደሉ12 የካቲት 2024
- የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች እና አልሻባብ ከባድ ውጊያ እያካሄዱ መሆኑ ተዘገበ24 ጥር 2024
- ሶማሊያዊያን ‘ፓይሬቶች’ እንደ አዲስ የሀገሪቱን የባሕር ጠረፍ ማሸበር ጀምረዋል?4 የካቲት 2024
ነገር ግን ከእስልምና እምነት ጋር ተያይዞ በሽማግሌዎች የሚደረገው ባሕላዊው ቆብን ግን ይህ ክልከላ እንዳይመለከተው ተደርጓል።
ይህ ማስክ እና ኮፍያ ማድረግ እንዲሁም የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን የሚከለክለው ውሳኔ የተላለፈው በቅርቡ ሞቃዲሾ ውስጥ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በተገኙበት በተካሄደ የደኅንነት ስብሰባ ላይ መሆኑ ተነግሯል።
ሶማሊያ ለአስርታት ባለመረጋጋት እና በደኅንነት እጦት ውስጥ የቆየች ሲሆን፣ ለዚህም ዋነኛው ተጠያቂ አል ሻባብ የተባለው ታጣቂ ቡድን ነው።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ባለው በዚህ ታጣቂ ቡድን ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻ የከፈቱ ሲሆን፣ አል ሻባብም በበኩሉ ሞቃዲሾን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚፈጽማቸውን ጥቃቶች አጠንክሯል።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለትም በዋና ከተማ ሞቃዲሾ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ተፈጽሞ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና የባህሬን ወታደራዊ መኮንኖችን ጨምሮ አምስት ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ቡድኑ መፈጸሙን በመግለጽ ኃላፊነቱን መውሰዱ ይታወቃል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ስር በሚገኘው ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ ላይ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ከተገደሉት ከፍተኛ መኮንኖች መካከል በሶማሊያ ኤምሬቶች ካላት ተሳትፎ አንጻር ወሳኝ ሚና የነበራቸው ኮሎኔል ሞሐመድ አል ማንሱር አንዱ መሆናቸው ተዘግቧል።