
15 የካቲት 2024, 18:14 EAT
በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የኦፓል ማዕድን ለማውጣት ቁፋሮ ላይ ሳሉ ዋሻ ተንዶባቸው መውጫ ያጡ ሰዎች ሳምንት ሲሆናቸው፣ የነፍስ አድን ጥረቱም እንቅፋት እንደገጠመው ተነገረ።
ለቀናት ሰዎቹን ከዋሻ ውስጥ ለማውጣት ጥረት ቢደረግም ከዋሻው አናት ላይ ያለ አለት እና ድንጋይ የነፍስ ማዳን ጥረት በሚያደርጉት ላይ ሊናድ ይችላል የሚል ስጋት በማስከተሉ ቁፋሮው ተስተጓጉሏል።
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ምሽት ማዕድን ለማውጣት ሲሞክሩ ነበር የተባሉ ማዕድን አውጪዎች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም የተለያዩ ምንጮች ሰዎቹ ከስምንት አስከ 20 ሊደርሱ ይችላሉ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቤተሰብ አባሎቻቸው ከዋሻው መውጣት ሳይችሉ ቀናት የተቆጠረ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን እና ቀኑ እየገፋ ሲሄድ በሕይወት የመውጣታቸው ነገር አጠያያቂ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።
አስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ በዋሻው ውስጥ የተቀበሩትን ሰዎችን ለማውጣት በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር ውስጥ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ጥረት ቢያደርጉም ማዕድን አውጪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
ሰዎቹን ሕይወት ለማትረፍ የሚደረገው ጥረት ውጤት አለማስገኘቱ እና አዝጋሚ በመሆኑ ተስፋ የቆረጡ ያሉትን ያህል የአካባቢው ነዋሪ የሚችለውን በማድረግ ላይ መሆኑን የማዕድን አውጪዎች ማኅበር ሊቀመንበር ለቢቢሲ ተናግሯል።
ዋሻው የተናደባቸው ሰዎች ወዳሉበት ጉድጓድ ለመድረስ አስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ አስከ 80 ሜትር የሚደርስ ቁፋሮ ከተደረገ በኋላ ቁፋሮው ከሚካሄድበት ስፍራ በላይ ያለ አፈር ሊናድ ይችላል በሚል ስጋት ቁፋሮው እንዲቆም ተደርጓል።
በዋሻው ውስጥ መውጫ አጥተው ከሚገኙት ሰዎች መካከል 28 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድሙ እንደሚገኝ የገለጸው ክንድዬ ተስፋዬ ለቢቢሲ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ እንደተናገረው ሊናድ ይችላል በተባለው የዋሻው ክፍል ምክንያት ቁፋሮው ቆሟል።
በናዳው ዋሻው ውስጥ ተቀብረው የሚገኙትን ሰዎች ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ቤተሰቦች ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም፣ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይረስ በሚል ስጋት ጥረቱ ተቋርጧል።
“ከናዳ ስር ተቀብረው ቀናት ያለፋቸውን ወጣቶች ጋር በመድረስ ሕይወታቸው ሊተርፍ ይችላል በሚል በተስፋ የሚጠባበቀው ቤተሰብ በከባድ ጭንቀት ውስጥ ይገኛል” ብሏል ክንድዬ።
ጉድጓዱ ተንዶ ማዕድን አውጪዎቹ በዋሻ ውስጥ ከተቀበሩ በኋላ የአካባቢው ሕብረተሰብ ባደረገው ጥረት አስከ 80 ሜትር የሚደርስ ቁፋሮ በማካሄድ ሕይወት ለማትረፍ ጥረት መደረጉን ነዋሪዎች እና የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ገልጸዋል።
“መውጫ ወዳጡት ወጣቶች ለመድረስ እስከ 150 ሜትር ድረስ መቆፈር ያስፈልጋል፤ ባለፉት አምስት ቀናትም ግምሽ ያህሉን መቆፈር ቢቻልም ሌላ ናዳ ይከሰታል በሚል ስጋት ቁፋሮው ቆሟል” ብሏል ክንድዬ።
በማዕድን አውጪዎቹ ላይ አደጋው የደረሰው በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው 018 አለኋት ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ውስጥ ቆቅ ውሃ በተባለ ስፍራ ላይ ነው።
- በደቡብ ወሎ በኦፓል ማዕድን ማውጫ የተቀበሩ ሰዎችን ለማውጣት የሚካሄደው ቁፋሮ መቋረጡ ተገለጸ14 የካቲት 2024
- በደቡብ ወሎ ማዕድን ሲያወጡ ናዳ የተጫናቸውን በርካታ ሰዎች የማውጣት ጥረት አራተኛ ቀኑን ያዘ12 የካቲት 2024
- በደቡብ ወሎ በኦፓል ማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች ሦስት ቀን ሆናቸው11 የካቲት 2024
የዞኑ እና የወረዳው አስተዳዳሪዎች ከቀናት በፊት ለቢቢሲ እንደገለጹት አካባቢው ገደላማ በመሆኑ እና ከዚህ ቀደም የኦፓል ማዕድን ለማውጣት የተቆፈሩት ዋሻዎች የመደርመስ አደጋን ሊፈጥሩ ስለሚችሉ የነፍስ አድን ሥራውን በሚፈለገው ሁኔታ ለማካሄድ አልተቻለም።
ስምንት አባላቱ በናዳው ተቀብረው እንደሚገኙ የገለጸው በአካባቢው የሚገኘው የወርቅ ዋሻ የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር ተስፋዬ አጋዥ፣ ሊናድ ይችላል የተባለው የዋሻውን ክፍል በማውረድ ቁፋሮውን ያለስጋት ለማስቀጠል ድጋፍ እንዲገኝ የአካባቢው ባለሥልጣናት ጥረት እያደረጉ ነው ብሏል።
ታናሽ ወንድሙ በዋሻው ውስጥ ከሚገኙት መካከል እንደሆነ የሚናገረው ጌጡ ሞላ እናቱ በከባድ ሐዘን ውስጥ እንደሚገኙ እና ልጃቸው ያለበት ሁኔታ አለመታወቁ የበለጠ እንደጎዳቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።
“እናታችን በጣም እየተጎዳች ነው። ወንድሜ ለሳምንት ያለበት ሳይታወቅ እንደወጣ በመቅረቱ የተፈጠረባት ስሜት ከባድ ነው። እራሷ ላይ ጉዳት እንዳታደርስ እየተጠበቀች ነው።”
ተጨማሪ ናዳ ተፈጥሮ ነፍስ ለማዳን የሚጥሩ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይርስ ለማድረግ ቁፋሮው ከተቋረጠ በኋላ የአካባቢው ባለሥልጣናት ከመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ለማግኘት ሐሙስ ከሰዓት በኋላ መነጋገራቸው ታውቋል።
በጉድጓዱ ውስጥ በናዳ ተቀብረው የሚገኙትን ሰዎች ቁጥር በተመለከተ እርግጠኛ የሆነ አሃዝ ባይኖርም፣ የአካባቢው ማዕድን አውጪዎች ማኅበር ግን ቁጥራቸው ስምንት መሆኑን ገልጿል። ቢሆንም ግን ተጨማሪ ሰዎች በጉድጓዱ ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉበት እድል እንዳለ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ለበርካታ ዓመታት የኦፓል ማዕድን ሲወጣበት የቆየው ዋሻ ጸንቶ የመቆም ጥንካሬው እየተዳከመ በመምጣት በተለያዩ ጊዜያት የመደርመስ አደጋ አጋጥሞ የሰዎች ሕይወት የጠፋ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸው፣ ለቀናት በዋሻው ውስጥ ቆይተው በሕይወት የወጡ ሰዎችም እንዳሉ ይናገራሉ።
አሁን በዋሻው ውስጥ መውጫ አጥተው ከሚገኙት ሰዎች መካከል በትክክል የሚታወቁት ስምንት ወጣቶች የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወርቅ ዋሻ የከበሩ ማዕድናት አምራቾች ማኅበር አባላት ናቸው።
ዋሻው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም. ሌሊት ምሽት ላይ የተናደ መሆኑን የሚናገሩት የአካባቢው ባለሥልጣናት 500 የሚደርሱ ሰዎች በቁፋሮው ላይ በመረባረብ ሕይወት ለማትረፍ ወደ ስፍራው ቢደርሱም በአካባቢው ያለው መልክዓ ምድር አመቺ ባለመሆኑ ስኬታማ ጥረት ማድረግ አልተቻለም ብለዋል።
ወደ ዋሻው የሚወስደው መንገድ ጠባብ በመሆኑ ቁፋሮውን ለማድረግ እና የተቆፈረውን አፈር ለማውጣት ከ50 ያልበለጡ ሰዎች ብቻ መግባት የሚችሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአካባቢው አፈር ጠንካራ ባለመሆኑ በቁፋሮ ላይ ባሉት ሰዎች ላይ ሊናድ ይችላል የሚለው ስጋት እንቅፋት ሆኗል።
ቁፋሮው ከሚካሄድበት ገደል በላይ ተንጠልጥሎ የሚገኘው ኮረብታማ ቦታ በቁፋሮው ምክንያት ወደታች ሊናድ እና ሰዎቹን ለማትረፍ በሚጥሩት ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋት ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ ቁፋሮው ተደናቅፏል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በዋሻው ውስጥ የተቀበሩ ወጣቶች ቤተሰቦች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ነፍስ የማዳን ጥረቱ የሚቀጥል ከሆነ በዋሻው ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ሕይወት ይተርፋል የሚል ተስፋ አላቸው።
ናዳው ተከስቶ ማዕድን ፈላጊዎቹ በጉድጓዱ ውስጥ መውጫ አጥተው ከተያዙ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 7/2016 ዓ.ም. ስምንተኛ ቀናቸው ቢሆንም አስካሁን ስላሉበት ሁኔታ የታወቀ ነገር የለም።
በባህላዊ መንገድ ለበርካታ ዓመታት ለውድ ጌጣጌጦች ማምረቻነት የሚውለውን የኦፓል ማዕድን ሲወጣበት የነበረው ዋሻ ገደላማ በመሆኑ እና መተላለፊያዎቹ ጥንካሬ ስለሌላቸው አደጋን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የአካባቢው ባለሥልጣናት ነዋሪዎችን ሲያስጠነቅቁ እንደነበር ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በምትገኘው ደላት ወረዳ ውስጥ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ በማዕድን ቁፋሮ ወቅት በሚያጋጥሙ የናዳ አደጋዎች ምክንያት ቢያንስ 50 ሰዎች መሞታቸውን የማዕድን አውጪዎቹ ማኅበር ሊቀመንበር ለቢቢሲ ገልጿል።