EthiopianReporter.com

ሳሙኤል ቦጋለ

February 14, 2024


ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ

በተከታታይ ለሁለተኛ ዓመት ከወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እየቀነሰ መሆኑን፣ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አፈጻጸም ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት ከተገኘው ከፍተኛ የወጪ ንግድ ገቢ 4.1 ቢሊዮን ዶላርቢሆንም ከዚያ በኋላ የተጠበቀውን ያህል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገባት ያልቻለው የወጪ ንግድ፣ ዘንድሮም አፈጻጸሙ ዝቅ ማለቱ ታውቋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከምትልካቸው አጠቃላይ ምርቶች ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት አቅዳ እየሠራች ቢሆንም፣ በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ውስጥ ግን መገኘት ከነበረት 2.4 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ የተገኘው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

መንግሥት ባለፉት ስድስት ወራት ለማግኘት ካቀደው ውስጥ 900 ሚሊዮን ዶላር በላይ (36 በመቶ) ዝቅ ያለው የወጪ ንግድ አፈጻጸምን፣ ‹‹አገሪቱ ካላት ዕምቅ አቅምና ካለው የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት አንፃር ብዙ መሥራት›› እንዳለበት፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገልጸዋል፡፡

ማክሰኞ የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች በወላይታ ሶዶ ከተማ የዓመቱን የመጀመርያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ገምግመዋል፡፡ ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት ተጨማሪ ሥራዎች ተሠርተው የወጪ ንግድ ገቢው መስተካከል ይኖርበታል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ የተገኘውን 4.1 ቢሊዮን ዶላር ዕሳቤ በማድረግ በ2015 በጀት ዓመት 5.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስገኝ አቅዶ ሲሠራ የነበረው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንደተገኘ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡

በዘንድሮ በጀት ዓመትም በተመሳሳይ ከዕቅዱም ሆነ ዓምና ከተመዘገበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያንስ በግማሽ ዓመቱ የወጣው ሪፖርት ያሳያሉ፡፡

ከዘንድሮው ግማሽ ዓመት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ ቡና 571 ሚሊዮን ዶላር በማስገባት ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሆነው የገቢ ሽፋን ሲይዝ፣ አበባ 225 ሚሊዮን ዶላር፣ ጥራጥሬና የቅባት እህል ከ285 ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ እንዲሁም ጫት ከ89 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማስገባት የግብርና ምርቶች አብላጫውን የገቢ መጠን መሸፈናቸው ታውቋል፡፡