
18 የካቲት 2024, 08:10 EAT
የታዋቂው የፈረንሳይ መጽሄት ‘ኤል ኤክስፕረስ’ ስመጥር የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ፊሊፕ ግሩምባች ለ35 ዓመታት ያህል ለሶቭየት ኅብረት ሲሰልል እንደነበር በመጨረሻ ይፋ አድረጓል።
ግሩምባች ለበርካታ አስርት ዓመታት በሥራው በፈረንሳይ ሕዝብ ዘንድ ከፍ ያለ ስም ያለው ሰው ነበር።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንቶች፣ ተዋናዮች እንዲሁም ታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ቅርብ ጓደኞቹ ነበሩ። በጋዜጠኝነት ሙያው የአንቱታ ስፍራ ከተሰጣቸው መካከል ግሩምባች አንዱ ነው።
በተጨማሪም በፈረንሳይ ውስጥ ስኬትን ከተጎናጸፉት የህትመት ውጤቶች ዋነኛ የሆነውን መጽሄት በመምራት እና አቅጣጫ በማስቀመጥም ይታወሳል።
በአውሮፓውያኑ 2003 ሕይወቱ ሲያልፍም የአገሪቱ የባህል ሚኒስትር ዣን ዣክ አይላጎን “በፈረንሳይ ሚዲያ ውስጥ አይረሴ ከነበሩ እና ከተከበሩ ሰዎች አንዱ ነበር” ሲሉ ስለ ግሩምባች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ግሩምባች ከታዋቂ ጋዜጠኛነቱ ባሻገር ሌላም ሕይወት ነበረው። በዚህም በተደራቢነት ለሶቪየት የስለላ ተቋም ኬጂቢ ሰላይ ሆኖ ሲሠራ ነበረ።
የሽፋን ስሙም “ብሮክ” ይባላል።
የግሩምባች ምሥጢራዊ ሕይወቱን በተመለከተም በአውሮፓውያኑ 1992 በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶችን ከሶቪየት ቤተ መዛግብት አሾልኮ በማውጣት ለብሪታንያ ባስረከበው የሶቪየቱ የስለላ ከፍተኛ ኃላፊ ሳቪሊ ሚትሮኪን ማኅደር ውስጥ በሰፊው ይገኛል።
ኬጂቢው ከፍተኛ ባለሥልጣን ስም “የሚትሮኪን ማኅደር” በሚል በተሰየመው በዚህ የመረጃዎች ጥንቅር ግሩምባች በስለላ ተቋሙ ውስጥ የነበረውን ሚና ያሳያል።
ይህም ኋላ ላይ በራሱ ቫሲሊ ሚትሮኪን እና ክርስቶፈር አንድሪው ወደ መጽሐፍ ተቀይሯል።
በሺዎች ከሚቆጠሩት እነዚህ ሰነዶች መካከል ለሶቪየት ኅብረት ሲሰልሉ የነበሩ ምዕራባውያንን የሚገልጹ መረጃዎች ተካተውበታል።
የኤል ኤልክስፕረስ የማኅበራዊ ጉዳዮች አርታኢ እና የግሩምባችን ምሥጢራዊ ሕይወት በማጋለጥ ‘ግሩምባች ኤክሶፖዜ’ የሚለውን ጽሁፍ ከጻፉት ደራሲዎች መካከል አንዱ የሆነው ኤቲን ዤራርድ የሚትሮኪን ፋይሎች ውስጥ የኤል ኤክስፕረስ ስም እንደተጠቀሰ ለመጀመሪያ ጊዜ የነገረው ባልደረባው ነበር።
ሰነዶቹ ላይ ለኬጂቢ የሚሰልል ብሮክ የተሰኘ ስም ተጠቅሷል። ብሮክ ተብሎ የተጠቀሰው ግለሰብ ደግሞ ከግሩምባች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ የሕይወት ታሪክ ዝርዝሮች በሰነዶቹ ውስጥ ተካቷል።
እነዚህም መረጃዎች ዤራርድ የበለጠ ሰነዶቹን እንዲመረምር መነሻ ሆነው።
“የበለጠ ሰነዶቹን ስመረምር የግሩምባች ስም በሩሲያ ቋንቋ ሰፍሮ እንዲሁም አንዳንድ ፎቶዎችንም ተያይዘው አገኘሁ” ሲልም ዤራርድ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሁኔታው ያሳሰበው ዤራርድ “ብሮክ በእርግጥ ግሩምባች መሆኑን ለማረጋገጥ ከፈረንሳይ የስለላ ድርጅት ጋር ተገናኘሁ ከዚያም በኋላ ሁኔታዎች ተቀየሩ” ሲልም ገልጿል።
- ‘የድመት ነፍስ አለው’ የሚባለው የሐማስ ወታደራዊ ኮማንደር ዴይፍ ማን ነው?18 ጥቅምት 2023
- የእስራኤል የስለላ ተቋማት መጠነ ሰፊውን የሐማስ ጥቃት እንዴት ሳይደርሱበት ቀሩ?8 ጥቅምት 2023
- የሩሲያ ሰላዮች ናቸው የተባሉ አምስት ሰዎች ለንደን ውስጥ ፍርድ ቤት ቀረቡ26 መስከረም 2023
ለመሆኑ ግሩምባች ማን ነበረ?
ግሩምባች ትውልዱ በፈረንሳይዋ መዲና ፓሪስ በአውሮፓውያኑ 1924 ነው።
ከአይሁድ ቤተሰቦች የተወለደው ግሩምባች በአውሮፓውያኑ 1940 ናዚ ጀርመን ፈረንሳይን በወረረበት ወቅት ከእናቱ እና ከወንድሞቹ ጋር አገሪቱን ለቆ ሸሸ።
ግሩምባች ወዲያውኑ የአሜሪካ ጦርን ተቀላቅሎ በአልጄሪያ ከነበረው የትግል እንቅስቃሴ ጋር በመጣመር በአውሮፓውያኑ 1943 በውጊያ ውስጥ ተሳትፏል።
ከዚያም ጦርነቱ ከተቋጨ በኋላ የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪልን ተቀላቀለ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ የፈረንሳይ መንግሥት በኢንዶ- ቻይና ጦርነት ላይ እየወሰደ የነበረውን እርምጃ በመቃወም ሥራውን ለቀቀ።
በአውሮፓውያኑ 1954 የኤል ኤክስፕረስ መሥራች ጂን ጃኩስ ሰርቫን ሺሬይበር ግሩምባችን ቀጠረው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ግሩምባች በ20ኛው ክፍለ ዘመን ስመ ጥር ከተባሉ የፈረንሳይ ታላላቆችም ጋር ጓደኝነት መሠረተ።
በአውሮፓውያኑ 1960 ሐሰተኛ ግድያን አቀነባብረዋል በሚል ስማቸው ጠፍቶ የነበረውን የወቅቱን ሴናተር ፍራንሷ ሚትራን ስም እንዲታደስ ካደረጉት መካከል ግሩምባች ቀዳሚው ነው።
ፍራንሷ ሚትራን በኋላም የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ለመሆን በቅተዋል። የፈረንሳይ ኃያሉ ፖለቲከኛ ሰርቫን ሽሪበር፣ ፕሬዝዳንት ቫሌሪ ጊስካርድ ደ ኢስታንግ፣ እንዲሁም ለወራት ፈረንሳይን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ፒየር ሜንዴስ ከቅርብ ጓደኞቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
የአገሪቱ ታላላቅ ፀሐፊዎች እና ተዋናዮች ከግሩምባች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው። በርካቶቹ በሠርጉ ላይ ታድመዋል፣ አብረው ማዕድ ተቋድሰዋል፣ ሌላም ሌላም።
በዚሁ ሁሉ የጠበቀ ግንኙነታቸው ውስጥ ሁሉም የማያውቁት ጉዳይ ቢኖር የኬጂቢ ሰላይነቱን ነበር።
ግሩምባች ለምን የኬጂቢ ሰላይ ሆነ? የሚለው ደግሞ በርካቶች የሚያነሱት ጥያቄ ነው።
መጀመሪያ ላይ ወደ ኬጂቢ የሳበው የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም እንደሆነ የሚትሮኪን ሰነድ ግምቱን ያስቀምጣል።
ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ በሰላይነት ለመቀጠል ምክንያቱ በአውሮፓ የኮሚኒዝም ሥርዓት እንዲሰፍን ሳይሆን ከግል ጥቅሙ ጋር የተገናኘ ነው ይላል። ይህም በፓሪስ ውስጥ ቤት ለመግዛት በቂ ገንዘብ ለማግኘት እንደሆነም ነው የሰፈረው።
በሚትሮኪን ሰነዶች መሠረት ግሩምባች ለኬጂቢ ለሰጠው አገልግሎት በአውሮፓውያኑ 1976 እስከ 1978 መካከል ባለው ወቅት የአሁኑን 250 ሺህ ዩሮ የሚስተካከል ገንዘብ እንደተከፈለው ነው።
በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ውስጥ ባሉ ሌሎች ሦስት አጋጣሚዎች በፈረንሳይ ውስጥ ካሉ 13 ከፍተኛ የሶቪየት ሰላዮች አንዱ በመሆን ተጨማሪ ጉርሻ አግኝቷል።
ሆኖም በትክክል የትኞቹን ተልዕኮዎችን ተወጥቷል ለሚለው ግልጽ መረጃ የለም።

የሚትሮኪን ሰነዶች እንደሚያሳዩት በአውሮፓውያኑ 1974 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኬጂቢ በቀኝ ክንፍ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች መካከል አለመግባባት ለመፍጠር ያቀዱ የፈጠራ ፋይሎችን ለግሩምባች መሰጠቱን ነው።
ግሩምባች ከፓለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ ከመሪዎች እና ከቡድኖች ጋር እንዲገናኝ አቅጣጫ እንደተሰጠው የሚገልጽ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ግን ሶቭየት ኅብረትን በስለላው ምን ያህል ረድቷል የሚለውን ለመረዳት ብዙም መረጃ የለም።
ምናልባትም በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኬጂቢ ከጋዜጠኛው ጋር ያለውን ግንኙነት ያቋረጠበት ምክንያትም ይህ ሊሆን ይችላል። በሚትሮኪን ሰነዶች መሠረት በፓሪስ የሚገኙ የኬጂቢ ሌሎች ወኪሎች ግሩምባችን “ቅንነት” የሌለው ሰው አድርገው ይመለከቱት እንደነበር ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ግሩምባች መረጃ የመሰብሰብ ችሎታውን እንዲሁም የስለላ ብቃቱንም እንዳጋነነ ይሰማቸው እንደነበረ ሰፍሯል። ኬጂቢም በአውሮፓውያኑ 1981 ግሩምባችን አሰናበተው።
ግሩምባች ለ35 ዓመታት ስለነበረው የስለላ ሕይወቱ ለማወቅ በአውሮፓውያኑ 2000 ቲየሪ ዎልተን የተባለ ጋዜጠኛ ሊያናግረው ቢሞክርም ውድቅ አድርጎታል።
ግሩምባች መጀመሪያ ላይ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ስላለፈው የስለላ ታሪኩ ያመነ ቢመስልም፣ በኋላ ላይ ግን ዎልተን የሚጽፍ ከሆነ ክስ እንደሚመሠርት አስፈራርቶታል። ዎልተን ፕሮጀክቱን እርግፍ አድርጎ ቢተወውም ግሩምባች ስለ ሕይወቱ ለመናገር ምክንያት ሆኖታል።
ባለቤቱ ኒኮል ለኤል ኤክስፕረስ እንደተናገረችው ከዎልተን ጉብኝት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሕይወቱ ያለፈው ባለቤቷ ስለ ሰላይነት ሕይወቱ እውነቱን ነግሯታል።
“ከመጋባታችን በፊት ለኬጂቢ ይሠራ እንደነበር ነገረኝ” ስትልም ለመጽሄቱ ተናግራለች።
በአሜሪካ ጦር ውስጥ እያለ በቴክሳስ ያየው ዘረኝነትን በመጸየፍ ከሶቭየት ኅብረት ጋር በትብብር ለመሥራት ምክንያት እንደሆነው እንደነገራት ነው የገለጸችው።
“ወዲያውኑ ማቆም ቢፈልግም ዛቻ ስለደረሰበት መቀጠሉንም ገልጾልኛል” ብላለች ኒኮል ለ ኤል ኤክስፕረስ መጽሄት።
ዤራርድ በበኩሉ ስለ ቀድሞው የመጽሄቱ ዋና አዘጋጅ እውነቱን ለማውጣት ምንም ችግር እንዳልነበረበት ያስረዳል።
“በእርግጠኝነት ሥራዬን እየሰራሁ እንደሆነ ተሰምቶኛል። ምርመራውን ማካሄድ የእኛ ሥራ ነው ምክንያቱም በቀጥታ እኛን የሚመለከት ጉዳይ ነው። ምቾት የማይሰጡ እውነቶችንም መናገር ጭምር” ሲል አስረድቷል።
ጽሁፉን ለማዘጋጀት ሦስት ወራት ፈጅቷል። ጽሁፉ ከወጣ በኋላም በፈረንሳይ የሚገኙ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ታሪኩን ዘግበውታል። ግሩምባች ለበርካታ አስርት ዓመታት በፈረንሳይ ሚዲያ ላይ የነገሰ ታላቅ ሰው ነበር።
አንዳንዶች ግሩምባች የመጽሄቱ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት ሶቪየትን የሚደግፉ መልዕክቶች አስተላልፎ ይሆን በሚልም የቀድሞ ቅጂዎቻቸውን ተመልክተዋል። ነገር ግን ይህ የመሆን ዕድሉ ኢምንት እንደሆነም መጽሄቱን ማየት ይቻላል።
ግሩምባች ዋና አዘጋጅ በሆነበት በ1950ዎቹ መጽሄቱ ግራ ዘመም የነበረ ቢሆንም፣ በኋላም በእሱ አመራር ሊብራል ወይም ለዘብተኛ የሚባል ዕይታ ነበረው።
መጽሄቱ ራሱ እንደዘገበው የግሩምባች የስለላ ሥራ ፈጽሞ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት አልነበረም። “የስለላ ተግባሩ ከመጽሄት አዘጋጅነቱ ጋር ፍጹም እንዳይገናኝ ጥንቃቄ አድርጓል” ሲልም ዤራርድ ያስረዳል።
“ለዚህም ነው ሽፋኑ ሳይታወቅ ለረዥም ጊዜ የቆየው” ሲልም ገልጿል።