
18 የካቲት 2024, 09:04 EAT
ጃፓን በርካታ ወጣቶች ጦር ሠራዊቷን እንዲቀላቀሉ ለማበረታታት በሚል በወታደሮቿ የፀጉር ቁርጥ ደንብ ላይ ለውጥ ማድረጓን አስታወቀች።
በዚህም ጃፓንን ጨምሮ በበርካታ የዓለም አገራት ጦር ሠራዊቶች ውስጥ ወታደሮች ፀጉራቸውን በአጭር እንዲከረከሙ የሚያዘውን ደንብ በመለወጥ አዳዲስ ምልምሎች ፀጉራቸውን እንዲያሳድጉ ተፈቅዶላቸዋል።
ጃፓን ይህንን ለውጥ ያደረገችው በዙሪያዋ ካሉት ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ በኩል ወታደራዊ ስጋት በተፈጠረበት በአሁኑ ወቅት የወታደሮች እጥረት ስላጋጠማት ነው።
በጃፓን ሠራዊት ውስጥ ወንዶች በጎን እና በጎን ያለው ፀጉር ሙልጭ ብሎ ተላጭቶ መሃል ላይ ያለው በአጭሩ እንዲቆረጥ፣ ሴቶች ደግሞ አጭር ፀጉር ብቻ እንዲኖራቸው ነበር የሚጠበቀው።
ነገር ግን ከሚመጣው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ይህ ደንብ ላልቶ የጃፓን ወታደሮች የብረት ቆብ በሚያደርጉበት ጊዜ አስቸጋሪ በማይሆን ሁኔታ ረጅም ፀጉር እንዲኖራቸው ይፈቀዳል።
- የወሊድ መጠን በመቀነሱ ጃፓን አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠነቀቁ24 ጥር 2023
- ሰሜን ኮሪያ አሜሪካንን እና ደቡብ ኮሪያን ለማስጠንቀቅ የሚሳኤል ሙከራ አደረገች19 የካቲት 2023
- በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሠፈራቸውን የመሠረቱ ኃያላን አገራት17 ግንቦት 2023
የጃፓን የመከላከያ ሚኒስትር ሚኖሩ ኪሃራ “አገራችን አሳሳቢ የሠራተኛ ኃይል እጥረት በገጠማት በአሁኑ ጊዜ፣ ከግሉ ዘርፍ ጋር ተፎካክረን አዳዲስ ምልምሎችን ለማግኘት የሚደረገው ፉክክር በእጅጉ በርትቷል” በማለት ለውጥ የማድረግ አስፈላጊነትን ተናግረዋል።
ይህ የጃፓን የምልምሎችን ቁጥር ከፍ የማድረግ ፍላጎት የመነጨው ቻይና በአካባቢው እያካሄደች ባለው ፈጣን የወታደራዊ አቅም ግንባታ እና የሰሜን ኮሪያ እየሰፋ በመሄድ ላይ ባለ የሚሳኤል እና የኑክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራሞች ምክንያት ነው።
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ጃፓን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የመከላከያ በጀቷን በከፍተኛ ሁኔታ እንደምታሳድግ ብታሳውቅም፣ ሠራዊቱ በበቂ ሁኔታ ምልምል ወታደሮችን ለማግኘት በእጅጉ ተቸግሮ ከአቅም በታች እየተንቀሳቀሰ ነው ተብሏል።
ጃፓን ታይምስ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በአገሪቱ ካለው የወሊድ ምጣኔ ከመቀነሱ እና በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ዝቅተኛ ክፍያ እንዲሁም በሠራዊቱ ውስጥ አለ የሚባለው ወሲባዊ ጥቃት በምልመላው ላይ እንቅፋት ፈጥሯል።
የጃፓን የመከላከያ ሚኒስቴር ካለፈው ዓመት ጀምሮ ምልመላን ለማበረታታት ለውጦችን እያደረገ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ንቅሳት ያለባቸው ሰዎች እንዳይመለመሉ የሚገድበውን ደንብ ለማንሳት እያጤነ መሆኑ ተገልጾ ነበር።
በሰውነታቸው ላይ ንቅሳት ያለባቸው ሰዎች በአገሪቱ ካለው ያኩዛ ከተባለው የወንጀለኞች ቡድን ጋር የተያያዙ ናቸው ስለሚባል በጃፓን ውስጥ ንቅሳት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ተብሎ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል።
አሁን ግን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ንቅሳት ያለባቸው ሰዎች የወንጀለኛው ቡድን አባላት ናቸው መባሉ ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ በምልመላውም ላይ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።