
18 የካቲት 2024, 09:30 EAT
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በራሳቸው ድርጅት የተመረተ እና በስማቸው የሚጠራ የስኒከር ጫማ ምርትን ይፋ በማድረግ ለገበያ አስተዋወቁ።
በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው ምርጫ ላይ በድጋሚ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመሆን ለዕጩነት እየተፎካከሩ ያሉት ትራምፕ፣ ፊላዴልፊያ የስኒከር ጫማ ወዳጆች በተሰበሰቡበት ማዕከል ውስጥ ተገኝተው ነው አዲሱን ምርት ያስተዋወቁት።
“ትራምፕ” የሚል ስያሜ ያለው እና 399 ዶላር የሚያወጣው ይህ ባለወርቃማ ቀለም ስኒከር ጫማን ለማስተዋወቅ የቀድሞው ፕሬዝዳንት መድረክ ላይ ለንግግር ሲወጡ ከተሰበሰቡት ሰዎች የድጋፍ እና የተቃውሞ ጩኸት ተሰምቷል።
ዶናልድ ትራምፕ የራሳቸው ተቋም ምርት የሆነውን ይህንን ስኒከር ጫማን ይፋ ያደረጉት፣ ያላቸውን የንብረት ዋጋ መጠን በማጋነን ለኒው ዮርክ ግዛት አሳውቀዋል በሚል ክስ ጥፋተኛ ሆነው ቅጣት ከተጣለባቸው ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
- ትራምፕ በማጭበርበር ክስ 354 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነ17 የካቲት 2024
- ትራምፕ በስም ማጥፋት ክስ 83.3 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነ27 ጥር 2024
- ፑቲን ከትራምፕ ይልቅ የባይደንን ፕሬዚዳንትነት እንደሚመርጡ ተናገሩ15 የካቲት 2024
ትራምፕ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የሃብታቸውን መጠን ከፍ አድርገው አሳውቀዋል ያሉት ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ 355 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ቅጣት እንዲከፍሉ ወስነውባቸዋል።
በሚቀጥለው ዓመት ኅዳር ላይ በሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ የሪፐብሊካን ፓርቲን በመወከል ከወቅቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ይፎካከራሉ ተብለው የሚጠበቁት ትራምፕ ባለፉት ዓመታት ተደራራቢ ክሶች ቀርበውባቸው ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ነው።
በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ሃብት ያፈሩት ትራምፕ በቅርቡ የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ላይ ናቸው። አዲሱ የስኒከር ጫማ ምርት በትራምፕ ስር በሚገኝ ኩባንያ የሚመረት ሲሆን፣ ድርጅቱ በድረ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ጫማውን አሁን ይፋ ማድረጉ ትራምፕ ለመመረጥ ከሚያደርጉት ዘመቻ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብሏል።
ይሁን እንጂ ትራምፕ አብዛኞቹ ወጣቶች በተሰበሰቡበት ጫማውን የማስተዋወቂያ መድረክ ላይ ሆነው በሚቀጥለው ምርጫ ሁሉም ወጥተው ድማጻቸውን እንዲሰጡ አጽንኦት ሰጥተው ጥሪ ሲያቀርቡ ተሰምተዋል።
ባለወርቃማ ቀለሙ ስኒከር ጫማ ከኋላው በአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚገኙት ዓይነት መስመሮች ያሉት ሲሆን፣ ምርቶችን በቅርስነት ለሚሰበስቡ ሰዎች በሚሆን መጠን በውስን ቁጥር ብቻ ለገበያ መቅረቡ ተገልጿል።