
18 የካቲት 2024
ኢትዮጵያዊው ኪያ ጀማል ሮጎራ የዓለም አቀፉ የብስክሌት ማዕከል ተወዳዳሪ ሆኖ በቱር ደ ሩዋንዳ ለመሳተፍ ኪጋሊ ተገኝቷል።
ቱር ደ ሩዋንዳ በየዓመቱ የሚደረግ በአፍሪካ አሉ ከሚባሉ የብስክሌት ውድድሮች ቁንጮው ሲሆን፣ ዓለም ያወቃቸው ብስክሌተኞች ይሳተፉበታል።
በቱር ደ ፍራንስ 10 ጊዜ ተወዳድሮ 4 ጊዜ ያሸነፈው እንግሊዛዊው ክሪስ ፍሩም ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ለመሳተፍ ሩዳንዳ መጥቷል።
ፍሩም የፈረንሳዩን ውድድር ሲያሸንፍ ኪያ ገና ታዳጊ ነበር። ውድድሩን ይመለከት የነበረው በቴሌቪዥን መስኮት ነው። በዘንድሮው የቱር ደ ሩዋንዳ ውድድር ግን ሁለቱ ብስክሌተኞች ለአንድ ዋንጫ ይፋለማሉ።
በዘንድሮው 16ኛ የቱር ደ ሩዋንዳ ውድድር ብሔራዊ ቡድኖችን ጨምሮ 20 አንጋፋ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 5 ተወዳዳሪዎችን ይዘው ይሳተፋሉ።
ድሬ ዳዋ ተወልዶ ያደገው ኪያ በምህጻሩ ዩሲአይ ለተሰኘው ዓለም አቀፍ ብስክሌተኞች የሚታቀፉበት ማዕከልን ወክሎ ይወዳደራል።
ኪያ፣ እንዲሁም ሦስት ጊዜ ቱር ደ ፍራንስ ላይ የተሳተፈው እና ለመጨረሻ ጊዜ ውድድሩን የሚያደርገው ፅጋቡ ግርማይ፣ የኤርትራው ሻምፒዮን አወት አማን፣ አልጄሪያዊው አዩብ ፎርኮስ እና ሩዋንዳዊው ሺያካ ዣንቪዬ የማዕከሉ ተወዳዳሪዎች ናቸው።
በቱር ደ ሩዋንዳ ለመወዳደር ከመጡ 6 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ይገኙበታል።
- አገሩን በብስክሌት እያስጠራ ያለው ፅጋቡ2 ጥቅምት 2017
- “የአፍሪካ የብስክሌት ንጉሥ” የተባለው ኤርትራዊው ቢኒያም ግርማይ15 ሀምሌ 2023
- በተመኘው ዩኒቨርሲቲ ለመማር 4ሺህ ኪሎ ሜትር በብስክሌት የተጓዘው ወጣት21 መስከረም 2023
“ሙሉ ትኩረቴን ወደ ብስክሌት አድርጊያለሁ”
ኪያ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ተፈትኖ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን ከፍተኛ ውጤት አግኝቶ ነበር።
ነገር ግን በወቅቱ የአሜሪካው የብስክሌት ቡድን ኢፍኤ ኤዱኬሽን ሊያስፈርመው ስላቀደ ከዩኒቨርሲቲ እና ከብስክሌት አንዱን መምረጥ ነበረበት።
“የ12ኛ ክፍል ፈተና በጥሩ ውጤት ነው ያለፍኩት። 418 [ከ500] ነበር ያመጣሁት። ነገር ግን ምርጫ ማድረግ ነበረብኝ” ይላል።
“ከአሜሪካ ቡድን [ኢኤፍኤፍ] ኮትራክት መጥቶልኝ ነበር። እዚህ ደግሞ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደርሶኝ ነበር። ከልጅነቴ ጀምሮ ዓላማዬ ፕሮፌሽናል ብስክሌተኛ መሆን ስለነበረ ሙሉ በመሉ ትኩረቴን ወደዚህ አድርጊያለሁ።”
ነገር ግን ሁለተኛው ዲቪዚዮን ስፖንሰር በማጣቱ ምክንያት ሲፈርስ የጣሊያኑ ማልቲኒ ላምፓዳሪ ክለብ ተቀበለው።
በሩዋንዳው ውድድር ዓለም አቀፉን የብስክሌተኞች ማዕከል ወክሎ ይወዳደር እንጂ ቀጥሎ የሚያመራው ወደ ጣሊያኑ ክለብ ነው።
ወጣቱ ብስክሌተኛ ስፖርቱን እንዲህ አብዝቶ ሊወደው የቻለው በአባቱ ምክንያት እንደሆነ ይናገራል።
“ብስክሌት የጀመርኩት በአባቴ ምክንያት ነው። አባቴ ጀማል ሮጎራ በሞስኮው [1980] ኦሊምፒክ ተሳትፏል። ሦስት ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮንም ነበር። ይሄ ምክንያት ሆኖኛል።”
ጀማል ሮጎራ፣ ዘርእጋብር ገብረሕይወት፣ ጥላሁን ወደልሰንበት እንዲሁም ሙሴ ዮሐንስ፤ በአውሮፓውያኑ 1980 ሞስኮ ላይ በተካሄደ የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ብስክሌተኞች ናቸው።
ገና ልጅ ሳለ አባቱ ብስክሌት ይገዙለት እንደነበር እና ከትምህርት በኋላ ብስክሌት መንዳት ይወድ እንደነበር ያወሳል።
10 ዓመት ሲሞላው ግን አባቱ በስጦታ ያበረከቱለትን ብስክሌት ይዞ መወዳደር ጀመረ።
ኪያ ከአባቱ ቀጥሎ ወደ ፕሮፌሽናል የብስክሌት ውድድር ያስገባው ቱር ደ ፍራንስ የተሰኘው የዓለም ትልቁ የብስክሌት ውድድር ነው።
“ፕሮፌሽናል የመሆን ሐሳብ የመጣልኝ ቱር ደ ፍራንስን ማየት ከጀመርኩ ወዲህ ነው እንጂ መጀመሪያ እንዲሁ ለጤና ነበር የምነዳው” ይላል።
ዘንድሮ ከኪያ ጋር የተፋጠጠው ክሪስ ፍሩም በአውሮፓውያኑ 2013፣ 2015፣ 2016 እና 2017 የቱር ደ ፍራንስ ቢጫ ማሊያ* አሸናፊ ነው።
ፍሩም በ2013 የመጀመሪያውን የቱር ደ ፍራንስ ድል ሲቀዳጅ ኪያ የ10 ዓመት ታዳጊ ነበር።

“የግድ ሊሳካልኝ ይገባል”
ኪያ፤ በቱር ደ ፍራንስ ከ23 ዓመት በታች ውድድር ሊሳተፍ አምስት ቀናት ሲቀሩት ጉዳት ስለደረሰበት ሳይሳተፍ ቢቀርም ይህ ሕልሙን ከማሰስ አላስቀረውም።
“ብስክሌት ከባድ ስፖርት ነው” የሚለው ኪያ በተለይ መውደቅ ከባድ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ይናገራል።
“ብዙ ለፍተህ መጨረሻ ላይ እንዲህ ስትሆን ያበሳጫል። ነገር ግን ብስክሌት ፍቅሩ ከባድ ነው። የብስክሌትን ፍቅር የሚያውቀው ያውቀዋል። ብትሰበርም ለመመለስ ነው ፍላጎትህ። አንዴ የገባሁበት ስለሆነ ወደኋላ መመለስ የለም፤ የግድ ሊሳካልኝ ይገባል ብዬ ነው የማስበው እንጂ ለማቆም አስቤ አላውቅም።”
ኪያ በቱር ደ ሩዋንዳ መሳተፍ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ያስረዳል። በተለይ “ትልልቅ የሚባሉ ክለቦች ዐይናቸውን ሊጥሉብህ ይችላሉ” ይላል።
“ማዕከሉ ይህንን ዕድል ሰጥቶናል። ይህንን ለመጠቀም ጠንክረን እንሠራለን።”
የወደፊት ዕቅዱ ቱር ደ ፍራንስ ላይ መሳተፍ እንደሆነ የሚናገረው ኪያ በዚህ ታላቅ ውድድር ላይ ታሪክ መጻፍ ይሻል።
“መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ስቴጅም* ቢሆን ማሸነፍ ነው። ቱር ደ ፍራንስ ላይ አፍሪካዊ ያላደረገውን ባደርግ፤ ታሪክ ብጽፍ ደስ ይለኛል።”
ከቱር ደ ፍራንስ ውጪ ሌሎችም ትልልቅ ውድድሮች የመሳተፍ ዕቅድ አለው።
“የዓለም ሻምፒዮና በጣም የምወደው ውድድር ነው። ቢኒያም ግርማይ [ኤርትራዊው ብስክሌተኛ] ሁለተኛ ሲወጣ እንደሚቻል አሳይቶናል። በሚቀጥሉት ሁለት ሦስት ዓመታት ይህን ማሳካት እፈልጋለሁ።”
ቢኒያም ግርማይ በአውሮፓውያኑ 2022 ጂሮ ዲ ኢታሊ በተሰኘው አንጋፋ የብስክሌት ውድድር ስቴጅ በማሸነፍ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ሆኗል።
ኪያ የተሳተፈባቸው ውድድሮች፡
- ጋና 2023 – የአፍሪካ ቻምፒዮና የግል የሰዓት ውድድር 1ኛ
- ኢትዮጵያ 2022 – የጎዳና ውድድር 1ኛ
- ኢትዮጵያ 2022 – የግል የሰዓት ውድድር 1ኛ
- ጋቦን 2023 – በቱር ጋቦን በአንደኛ ስቴጅ* 6ኛ
- በ2023 36 ቀናት ውድድር በማካሄድ 4519 ኪሎ ሜትር በመጋለብ 64.75 ነጥብ
_____
* ስቴጅ፡ የብስክሌት ውድድር ብዙውን ጊዜ በርካታ ቀናት ይወስዳል። የእያንዳንዱ ቀን አሸናፊ የስቴጅ አሸናፊ ይባላል
* ቢጫ ማሊያ፡ በቱ ደ ፍራንስ እና በቱር ደ ሩዋንዳ የሁሉንም ስቴጆች በድርም በአነስተና ሰዓት ላጠናቀቀ የሚሰጥ የክብር ማሊያ ነው። ቢጫ ማሊያ የውድድሩ አሸናፊ የሚያደርገው ማሊያ ማለት ነው።