
18 የካቲት 2024
ናትናኤል በኃይሉ ተወልዶ ያደገው በነጭ ማር ምርት በምትታወቀው አዲግራት፣ ትግራይ ክልል ውስጥ ነው።
ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በኤሌክትሮ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተመርቋል።
የተማረበትን ሙያ እና የልጅነት ህልሙን ማገናኘት ሲፈልግ ወደ አእምሮው ብቅ ያሉት ‘ትጉሆቹ ንቦች’ ናቸው።
የንቦች ነገር ሁሌም ይመስጠዋል፤ በኅብረት ይሠራሉ፤ በሕብረት ያመርታሉ። ታታሪነታቸው ከየትኛውም ነፍሳት የተለየ ነው።
እናም የመጀመሪያ ድግሪውን በተማረበት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በንቦች ላይ የሚያደርገውን ጥናት እና ምርመር አጠናክሮ ቀጠለ።
ንቦች ስምንት ኪሎ ማር ተመግበው አንድ ኪሎ ሰም ያዘጋጃሉ ይላል ናትናኤል።
አክሎም ንቦች የማር እንጀራ ለማዘጋጀት ረዥም ጊዜ ይወስድባቸዋል። የማር እንጀራው ካልተዘጋጀ ደግሞ የማር ምርት የለም።
ናትናኤል የትጉሆቹ ንቦችን ሥራ ለማገዝ ዓላማ አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል። እንዴት አድርጎ?
ምቹ የአየር ንብረት እና የተፈጥሮ ደን ያላት ኢትዮጵያ በዓመት 500 ሺህ ቶን የሚጠጋ ማር ለማምረት አቅም እንዳላት የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
ነገር ግን አገሪቱ ካላት እምቅ ሃብት አንጻር እየተመረተ ካለው ጋር ሲታይ 12 በመቶው ብቻ ነው።
በዘመናዊ መንገድ ንብ የሚያንቡም ቢሆኑ እንኳን፣ ምርቱን ከሰበሰቡ በኋላ የማር እንጀራውን ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲጠቀሙበት ስለማይመከር ንቦች በተደጋጋሚ የማር እንጀራ በማምረት ጊዜያቸውን ያጠፋሉ ይላል የሜካኒካል ኢንጂነርኒግ ባለሙያው።
ንቦች የማር እንጀራ የሚሠሩት በሆዳቸው የታችኛው ክፍል የሚገኙ ዕጢዎች የሚያመነጩትን ሰም ተጠቅመው ነው።
የማር እንጀራ እጅግ የተራቀቀ የምህንድስና ጥበብ እንደሆነ የሚያስረዳው ናትናኤል፣ ንቦች ያላቸውን ቦታ ያለምንም ብክነት ለመጠቀም ቦታውን ባለስድስት ጎን በሆኑ ቅርጾች ይከፋፍሉታል ይላል።
ይህም ጠንካራ ሆኖም ብዙ ክብደት የሌለው እንዲሁም በአነስተኛ ሰም ብዙ ማር የመያዝ አቅም ያለው የማር እንጀራ ለመሥራት ያስችላቸዋል።
በዚህ አስደናቂ ጥበብ በሚታይበት የነፍሳቱ የግንባታ ንድፍ የተመሰጠው ናትናኤል የማር እንጀራውን በ3ዲ [በባለሦስት አውታር] ሕትመት ቢሰራላቸው የተሻለ የማር ምርት መሰብሰብ እንደሚቻል አቅዶ ወደ መሥራት ጀመረ።
- “የከተማ መስፋፋት የኢትዮጵያን ብዝሀ ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል” ዶ/ር መለሰ ማርዮ22 ግንቦት 2019
- በኢትዮጵያ ለአንበጣ የተረጨው ፀረ ተባይ እንዴት 76 ቢሊዮን ንቦች ላይ ጉዳት አደረሰ?13 ግንቦት 2023
- ያለ ንብ ማር፣ ያለ ላም ወተት ማምረት ይቻላል?14 ግንቦት 2021
የማር እንጀራን በ3ዲ
የማር እንጀራ የሚያዘጋጁት ሠራተኛ ንቦች ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 18 ቀን ነው።
ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ፣ ሰም ለማምረት የሚያስችል ‘ኢንዛይም’ በአካላቸው ውስጥ የያዙት እነርሱ በመሆናቸው እንደሆነ ናትናኤል መረዳቱን ለቢቢሲ ገልጿል።
“ማር ማምረት ለንብ ከባዱ ሥራ ይመስለናል” የሚለው ናትናኤል፣ ከዚያ ይልቅ የማር እንጀራውን ለመሥራት ከፍ ያለ ጊዜ እንደሚያጠፉ ይናገራል።
የማር እንጀራ ለማምረት ከሦስት እስከ አራት ወር እንደሚፈጅባቸ፣ ነገር ግን በ3ዲ ህትመት ከፕላስቲክ የሚያመርተው የማር እንጀራ ይህንን ያስቀርላቸዋል ይላል።
“ልፋታቸውን ለመቀነስ አርተፊሻል የማር እንጀራ ሠርቼያለሁ” የሚለው ናትናኤል፣ በ3ዲ ህትመት የሠራው ሰው ሠራሽ የማር እንጀራ፤ ንቢቱ ማር ለማምረት የምትወስደውን ጊዜ ለማሳጠር፣ በቅድሚያ የማር እንጀራውን አዘጋጅቶ ወደ ዘመናዊ ቀፎ በማስጋባት ሞክሮታል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ወደ 59 ሺህ ቶን ማር አንደምታመርት የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ሲያሳይ፣ ከዚህም ውስጥ ደግሞ 93 በመቶ የሚሆነው የሚመረተው በባህላዊ መንገድ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ያላት እምቅ ሃብት እና በተግባር እያገኘች ያለው የማር ምርት አልተገናኙም።
ናትናኤል ይህንን ልዩነት ለማጥበብ የእርሱ የምርምር ውጤት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያምናል።

የ3ዲ ህትመት
የ3ዲ [የባለሦስት አውታር] ህትመት በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ጥናት እና ምርምር የሚደረግበት ዘርፍ ነው።
ይህንን የህትመት ዓይነት በመጠቀምም የተለያዩ ነገሮች ማምረት እንደሚቻል ናትናኤል ያስረዳል።
ናትናኤል 3ዲ ማተሚያዎችን የሚሸጥ ‘ሮቦክስ’ የሚባል የሥራ ፈጠራ ጀማሪ (ስታርት) አፕ ኩባንያ አለው።
በዚህ ድርጅቱ በኩልም የ3ዲ ህትመቶችን ይሠራል።
ናትናኤል ማር አምራች አካባቢ ተወልዶ እንደማደጉ የንቦችን ሥራ የማቅለል ሃሳብ ቢኖረውም፣ ተፈጥሯዊው የማር እንጀራ ግን የራሱ የሆነ ልኬት እንዳለው አስተውሏል።
የማር እንጀራው ዐይን ባለ ስድስት ጎን ነው የሚለው ናትናኤል፣ እያንዳንዱ ጎን ደግሞ ልኬቱ ተመሳሳይ ሆኖ የሚሠራ ነው።
ስለዚህ የ3ዲ ህትመቱን በፕላስቲክ ሲሠራ እነዚህን ሁሉ መጠንቀቅ ነበረበት።
ንቦች የማር እንጀራውን እየሠሩ ቅርጹን ባለ ስድስት ጎን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ማሩ እንዳይፈስ፣ በተወሰነ መጠን ዘንበል እንደሚያደርጉት ጨምሮ ያስረዳል።
ይህንን አጥንቶ የማር እንጀራ በ3ዲ ማተም የቻለው ናትናኤል፤ በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ውስጥ ባስቀመጣቸው አምስት የንብ ቀፎዎች ውስጥ ሙከራውን አካሂዷል።
ንቦቹም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማር ምርት በመስጠት ውጤታማ መሆናቸው መፈተሹን ይናገራል።
ናትናኤል ከዩኒቨርስቲው ተመርቆ ከወጣ ሦስተኛ ዓመቱ ቢሆንም፤ አሁንም የምርመር ሥራዎቹን በዚያው በዩኒቨርስቲው ውስጥ እንደሚሰራ ጨምሮ ይናገራል።
ናትናኤል በምርምር ውስጥ ሌላ ያካተተው ነገር የማር ምርቱን ለመሰብሰብ ቀፎውን መክፈት እንዳያስፈልግ ማድረግ ነው።
ስለዚህ በ3ዲ የተመረተው የማር አንጀራ ላይ ቀጭን ቱቦ በማስገባት እና ከታች ሳህን መሳይ ነገር በማካተት ማር መሰብሰብ የሚፈልገው ግለሰብ፣ ይህንን ሳህን ከውጪ በመሳብ ብቻ ምርቱን ማግኘት ይችላል ይላል።
ይህም የማር ምርቱን በቀላሉ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን፣ በምርት ስብሰባ ወቅት ይሞቱ የነበሩ ንቦችን መታደግ እንዳስቻለ ይጠቅሳል።
ሰምን እያቀለጡ ማተም
ሰም ለተለያዩ ምርቶች ግብዓትነት ያገለግላል።
የመዋቢያ ምርቶች፣ ሳሙና፣ እንዲሁም ምግብ ሳይበላሽ እንዲቆይ ይረዳል።
ማር ራሱ ረዥም ጊዜ እንዲቆይ የሚያደርገው ንቦች በማር አንጀራው፣ ሰሙ፣ ላይ ምርታቸውን በማምረታቸው እንደሆነ ናትናኤል ያስረዳል።
ናትናኤል የማር አንጀራውን በፕላስቲክ ከማምረት ይልቅ ከሰም ማምረት እንደሚቻልም በጥናቱ ማረጋገጡን ጠቅሷል።
ናትናኤል ለ3ዲ ህትመት የተጠቀመው ፕላስቲክ፣ ለምግብ መያዣነት የሚመከር መሆኑን እና ማር ሲመረትበትም ምን ጉዳት እንደማያስከትል ማረጋገጡን ይጠቅሳል።
ንቦቹ ከፕላስቲክ የተሠራ የማር እንጀራ ላይ ማር ሲያመርቱ፣ ምንም ዓይነት እንከን አለመመልከቱን ገልጾ፣ በፕላስቲክ ህትመቱ ወቅት የተፈጠሩ ክፍተቶች ግን አስቀድመው መድፈናቸው አስተውሏል።
አሁን ደግሞ አዲስ የ3ዲ ማተሚያ ማሽን በመሥራት እና ሰምን በማቅለጥ የማር እንጀራ ማተም መቻሉን እና “የንቦቹን ሥራ ማቅለሉን” ይናገራል።
ናትናኤል የፈጠራ ሥራውን እስካሁን ለገበያ እንዳላቀረበ እና በሂደት ላይ መሆኑንም ጨምሮ አስረድቷል።
የንብ ምርት ወቅታዊ ነው የሚለው ናትናኤል፣ ምርታማ በሚባል አካባቢ እና ዘመናዊ ቀፎ በሚጠቀሙ አናቢዎች ዘንድ በዓመት ሦስቴ፣ ካልሆነ ግን ሁለት ጊዜ ምርት ይሰበሰባል።
ንብ አናቢዎች በ3ዲ የታተመ የማር አንጀራን ቢጠቀሙ ተጨማሪ አንድ የምርት ጊዜ ይኖራቸዋል ሲል የእርሱ የፈጠራ ሥራ ምን ያህል ጥቅም እንዳለው ይናገራል።
ወደፊት. . .
ይህ የናትናኤል ፈጠራ ከሄይፈር ኢንተርናሽናል እውቅና እና የ3ሺህ 500 የአሜሪካ ዶላር ሽልማት አስገኝቶለታል።
ናትናኤል ሕጻናትን የሮቦቲክስ ኮርሶችን ለማስተማር በሚል በመሠረተው ሮቦክስ የተሰኘ ድርጅቱ በኩል የፈጠራ ሥራውን ለማስፋት አቅዶ እየሠራ ነው።
ናትናኤል የተሻሻሉ ዘመናዊ ቀፎዎችን አምርቶ ለመሸጥ እና ማር ለማምረት ዕቅድ አለው።
እስካሁን የሠራቸው የፈጠራ ሥራዎችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ 50 ንብ አናቢዎች የሚያገኙት የማር ምረት በ40 በመቶ እንዲጨምር ማድረግ አስችሏል።
ናትናኤል ወደፊት ለማር ምርት ምርምር የሚሆን ቦታ በመፈለግ ላይ ነው።
የኢንጂነሪንግ ዕውቀትን ተጠቅሞ የማር ምርት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን መቅረፍ የሚል ዕቅድ ያለው ናትናኤል፤ ቀፎ ላይ ተገጥሞ ስለንቦች አጠቃላይ ሁኔታ የሚያጠና የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) ሥርዓት መሥራቱን እና ይህን የምርምር ሥራውን ማጠናከር እንደሚፈልግ ይናገራል።
“የንቦችን ደኅንነት መጠበቅ እፈልጋለሁ” የሚለው ናትናኤል ተመራማሪዎችንም ሆነ ንብ አናቢዎችን የሚያግዝ፣ በቀፎ ውስጥ ስለሚገኙ ንቦች ሙሉ መረጃ የሚሰበስብ መሳርያ ላይ እየሠራ መሆኑን ይናገራል።