
18 የካቲት 2024, 10:47 EAT
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ እንቅፋት ሆነውባቸው እንደነበር ከከሰሱ በኋላ የአዲስ አበባ ቆይታቸውን አቋርጠው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ተዘገበ።
ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን ተከትሎ ሶማሊያ ተቃውሞዋን በማሰማት በሁለቱ አገራት መካከል ውዝግብ መፈጠሩ ይታወቃል።
በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ከሻከረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ኅብረትን ስብሰባ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ በስብሰባው ላይ እንዳይገኙ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ሙከራ ተደርጎባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ለሁለት ቀናት ተካሂዶ ዛሬ እሁድ የሚያበቃውን የኅብረቱን የመሪዎች ጉባኤን ሳያጠናቅቁ አቋርጠው ወደ ሞቃዲሾ ቅዳሜ ምሽት መመለሳቸውን የቱርክ ዜና ወኪል አናዱሉ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ እና ልዑካቸው የመሪዎቹ ስብሰባ በጀመረበት ቅዳሜ ዕለት ከሆቴላቸው ለመውጣት እና ወደ አፍሪካ ኅብረት ጊቢ ለመግባት በሞከሩበት ወቅት በታጠቁ የፀጥታ ኃይሎች መከልከላቸውን ጉባኤውን ከተሳተፉ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት ተናግረው ነበር።
- የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ አፍሪካ ኅብረት ስብሰባ “እንዳልገባ ለመከልከል ሙከራ ተደርጓል” ማለታቸውን ኢትዮጵያ አስተባበለች17 የካቲት 2024
- ሶማሊያ ውስጥ ቢያንስ ሰባት ኢትዮጵያውያን ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ተገደሉ6 የካቲት 2024
- ግብፅ ሶማሊያን እደግፋለሁ ማለቷን ተከትሎ ሶማሊላንድ ‘የውጭ ጣልቃ ገብነት’ እንደምትቃወም ገለጸች23 ጥር 2024
በሶማሊያው ፕሬዝዳንት የቀረበውን ክስ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ለቢቢሲ በጽሁፍ በሰጠው ምላሽ እንደ አስተናጋጅ አገር ኢትዮጵያ ለእንግዶቹ ደኅንነት ኃላፊነት እንዳለበት በመግለጽ፣ የሶማሊያ ልዑካን በመንግሥት የተመደቡላቸውን የፀጥታ ሠራተኞች አንቀበልም ማለታቸውን ገልጿል።
በተጨማሪም የፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ጠባቂዎች የጦር መሳሪያ ታጥቀው ወደ አፍሪካ ኅብረት ቅጥር ጊቢ ለመግባት በሞከሩበት ወቅት በኅብረቱ የፀጥታ አካላት መከልከላቸውን በማመለክት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬዝዳንቱን እና የልዑካኑን ደኅንነት ከመጠበቅ ባሻገር በስብሰባው ላይ እንዳይገኙ እና ኅብረቱ ጊቢ እንዳይገቡ እንዳልከለከለ አሳውቋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አዲስ አበባ ላይ ገጠመኝ ያሉትን ክስተት ተከትሎ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሁኔታው የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ደንብን የሚጥቀስ መሆኑን በመግለጽ፣ የአፍሪካ ኅብረት ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግ እና ኅብረቱ መቀመጫው ያለበትን አገር ሁኔታ ማጤን ሊያስፈልገው እንደሚችል አመልክቷል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ ለአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ዋነኛ ዓላማቸው በኢትዮጵያ ተፈጸመ ያሉትን የሉዓላዊነት ጥሰት ለማንሳት እንደሆነ ተገልጾ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ በአዲስ አበባው ቆይታቸው “ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መሬት መውሰድ ትፈልጋለች። ይህንንም ለማመቻቸት በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሶማሊላንድ ውስጥ ይገኛሉ” በማለት የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን እና ኢትዮጵያ ውዝግቡን እያባባሰች ነው ሲሉ ከሰዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ የባሕር ጠረፍ የማግኘት እና በምላሹ ለሱማሊላንድ እውቅና ለመስጠት የደረሰችው ስምምነት “ሕገመንግሥታዊ ያልሆነ፣ ሕገወጥ እና ተቀባይነት የሌለው” በማለት የሌላ አገርን ግዛት የመጠቅለል እርምጃ ነው ብለውታል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ነጻ አገርነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለውን እና ሶማሊያን ያስቆጣውን የመግባቢያ ሰነድ የፈረሙት ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ነበር።